እስልምናና የሥራ ባህል

እስልምናና የሥራ ባህል

Rise early to make a living, as hard work generates success and reward[1]

በጧት ተነስተህ ሥራ፤ ታታሪነት ስኬትንና ሽልማትን ያስገኛልና ፡፡

ከግሪክ ሥልጣኔ አንሥቶ እስከ ኢንዱስትሪው አብዮት እንድሁም አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ የሥራ ባህል በብዙ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ አልፏል፡፡ የጥንት ግሪካውያን ‘ሥራ የአማልክት ቁጣ ነው’ ብለው ስለሚያምኑ ከእርግማን ጋር ያያይዙታል፡፡ አብዛኛው የሮማውያን ሥልጣኔ ከግሪክ የተኮረጅ እንደመሆኑ መጠን የሥራ ግንዛቤም ከግሪክ በመውረሳቸው ተመሳሳይ እሳቤ ነበር ያራመዱት፡፡ አይሁዳውያንም በተመሳሳይ መልኩ ሥራ የኃጢአት ውጤት ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ የቀደመው የክርስቲና ልምምድም ከሥራ ይልቅ በመንሳዊ ተግባራት ላይ መሳተፍን ስለሚያበረታታ የሥራ ባህልም ትኩረት የተነፈገ ነበር፡፡ ቁሳዊ ሀብት ከማከማች ይልቅ በጾምና ጸሎት ለቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ዝግጅት ማድረግ ላይ የበለጠ ትኩረት ያደርግ እንደነበረ በታሪክ አይተናል፡፡ በሂደት ግን እነዚህ አስተሳሰቦች ላይ አብዮታዊ የለውጥ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል፡፡ በተለይ እነ ማርቲን ሉተር ተነስተው የአውሮፓውያንን ባህል ከነቀነቁ በኋላ ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ ‹‹ሰዎች በሥራቸው እግዚአብሔርን ያገልግሉ›› የሚለው የነ ሉተር አስተሳሰብ ሥራ ጠል የነበረውን የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ልማድ ከሥሩ ነቅንቋል፡፡ በተለይ ከሉተር በኋላ የተነሣው ጆን ካልቭን ከመለኮት ጥሪ ጋር በማያያዙ የሥራ ባህል ላይ ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል፡፡

ሙስሊም ወገኖች ከማኅበረሰቡ መካከል የሚታወቁት በጠንከራ ሠራተኛነትና በሐቀኝነት ነው፡፡ ዳተኛና የሚያምታታ ሙስሊም ማግኘት የተለመደ አይደለም[2]፡፡ ይህ እሴታቸው የሚቀዳው ከሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸው ነው፡፡

እስልማና ገና ከጅምሩ ሥራን በተመለከተ ጠንከር ያለ አቋም ነበረው፡፡ የተረጋጋና ጤናማ ኢኮኖሚ ያለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሥራ ወሳኝ እንደሆነ የሃይማኖቱ ልሂቃን አስተምረዋል፡፡ ነቢዩ እንዳስተማረው “እግዚአብሔር በሰማይና በምድር ጠባቂዎች አሉት፣ በሰማይ ያሉ ጠባቂዎች መላእክቱ ሲሆኑ በምድር ያሉት ደግሞ ለሕይወታቸው ቀጣይነትና ለሌሎች ጥቅም ለፍተው የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡”[3] በእስልምና አስተምህሮ ሥራ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጣ መሣሪያም ነው፡፡ በእስልምና የሥራ ሥነ-ምግባር ሥራ ለሰው ልጅ ነፃነት፣ ለራስ ክብር፣ እርካታና የሕይወት ስኬት የሚያመጣ ተግባር ነው።

በእስልምና የሥራ ባህል (“Islamic Work-Ethic [IWE]”) እንደ ዋና መርሆች ተደርገው የሚቆጠሩ እሳቤዎች አሉ፡፡ እነሱም ትጋት፣ አዎንታዊ የሆነ ውድድር፣ ግልጸኝነት፣ የሞራል ተጠያቂነት ናቸው፡፡

የኢስልምና የሥራ ባህል ጠንካራ እንዲሆን ካደረጉ አስተሳሰቦ መካከል ሕይወትን የሚመለከቱበት እይታ ነው። በክርስቲና የሥራ ባህል ላይ አሉታዊ አስተሳስብ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ተብለው ከሚተቹ ባህሎች መካከል አንዱ የሆነው ሥራን መንፈሳዊና ዓለማዊ ብሎ የመፈረጅ ልምድ በኢስልምና ውስጥ ቦታ የለውም። የአንድ ሙስሊም ዋና ዓላማ በሚሠራው ሥራ አምላኩን ማስደስት ነው። በሁሉም ሥራዎች ፊቱን ወደ እርሱ ያዞራል፣ እርሱን ብቻ ያስባል ዓላማውም መንፈሳዊ ተግባራቱንም ለአላህ ሲል ይፈጽማል “ሕይወቱ ‘መንፈሳዊ’ እና ‘ዓለማዊ’ በሚል ከሁለት አትሰነጠቅም[4]። ከመስኩ ላይ የሚያርስ ገበሬ፣ ፋብሪካ ውስጥ የሚያመርት ወዝ አደር፣ በንግድ ቦታው ላይ ያለ ነጋዴ፣ ቢሮው ውስጠ የተቀመጠ የቢሮ ሠራተኛና የእጅ ባለሙያ የተፈቀዱ ኢስላማዊ ሕግጋትን እስከተከተሉ ድረስ እንደ መንፈሳዊ አምልኮ ሥርዓቶች ማለትም ሶላት ሊቈጠሩ ይችላሉ።

ስለዚህ አንድ ሙስሊም ‘ዓለማዊ’ ነው ብሎ የሚንቀው የሥራ ዓይነት የለም። ይልቊን ሥራውን አምላኩን እንደማምለክ ስለሚቈጥረው በትጋት ይሠራል እንጂ። ከዚህ የተነሣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም ንግድ ቦታዎች ላይ የምናገኛቸው ሙስሊም ወንድሞችና እህቶች በሥራቸው ታታሪነት እንጂ በስንፍናና በሰበበኝነት ብዙ አይታወቊም። ያሉ ካሉም ከሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸው የሚያፈነግጡ ነው የሚሆኑት፣ ምክንያቱም አስትምህሮው ስንፍናን አይፈቅድምና።


[1] Al-Shaybani

[2] ይህ ማለት ግን ከእስልምና ባህል አፈንግጠው የሥነ ምግባር ግድፈት የሚፈጽሙ ግለሰቦች የሉም ማለት አይደለም፣ በአመዛኙ ግን ሙስሊሞች ሐቀኞችና ታታሪዎች ተደርገው ይታመናሉ፡፡

[3] (Al-Mawardi, p.218) Quoted in Abbas J. Ali: Islamic Work Ethic in a Dynamic World

[4] ኢስላምን መረዳት፥ በዶ/ር ዩሱፍ አል-ቀርዷዊ (ትርጉም በሐሰን ታጁ)፡ ነጃሺ ማተሚያ ቤት (2004 ዓ.ም) ገጽ 106

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *