ከምሥራቅ እስያ አገራት ተአምራዊ ዕድገት ጀርባ

ከምሥራቅ እስያ አገራት ተአምራዊ ዕድገት ጀርባ

ዛሬ ያለው ዓለም ያደግ ያላደገ፣ አንደኛ ዓለም ሁለተኛና ሦስተኛ ዓለም ወይም ሰሜናዊውና ደቡባዊው ዓለም ብሎ በተለያዩ ጎራዎች መፈረጅ የተለመደ ነው። የዚሀ ክፍፍል ዋና ማጠንጠኛው ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑን ነው። ነገር ግን በዚያ ቦታ ያልተገለጸው ሌላ ዐዲስ ቡድን በቅርቡ ተፈጥሯል፣ ይኸውም የምሥራቅ እስያ አገሮችን፥ በተለይ አራት አገራትን የሚያጠቃልልና “ኢንዱስትሪን የተቀላቀሉ ዐዳዲሶቹ አገራት” ወይም “newly industrializing countries (NICs)” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አገራት ናቸው። አገራቱም ሆንግ ኰንግ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ እና ታይዋን ናቸው። ዕድገታቸውም “ተአምር” ተብሎ ተወድሷል። የእነዚህ አገራት ብልጽግና በብዙ መልኲ ዓለምን ማኅበረሰብ፣ በተለይ ልህቃኑን ከማስደመሙም በላይ የመወዛገቢያ አጀንዳም ሆኗል። አገራቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሦስተኛው ዓለም ወይም ያላደጉ ተብለው በተፈረጁ አገራት ተርታ የሚሰለፉ ነበሩ። ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የድህነት አመዳቸውን አራግፈው በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ብልጽግና እየገሰገሱ ይገኛሉ። ዕድገታቸውን ተአምር ያስባለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም ከ1960 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ሃያ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ተከታታይነት ያለውን ዕድገት በማስመዝገብ የድህነትን መንደር ጥለው የሄዱት። በ1950ዎቹ አካባቢ የእነዚህ አገራት (በተለይ ታይዋን) የውጪ ንግዳቸው 90% የግብርና ምርቶች የሚሸፍን ሲሆን በ1990ዎች አካባቢ ወደ 10% ዝቅ ብሎ ከመቶ 90 እጁ ባለቀላቸው የፋብሪካ ምርቶች ተተካ። ሲንጋፖርና ሆንግ ኰንግ ስናይ በ1960ዎች አካባቢ የምርት ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ በሰው ጒልበት ላይ የተመሠረተ (Labour intensive) ሲሆን በ1970ዎች አካባቢ የሰው ጒልበትን በቴክኖኖጂ በመተካት ከፍተኛ እምርታን አስገኝተዋል።

ዕድገቱ ከማስደመሙና “ተአምር” ተብሎ ከመወደሱ ባሻገር የመከራከሪያና የመወያያ አጀንዳም ሆኗል። አከራካሪነቱ የሚመነጨው አገራቱ የሄዱበትን የዕድገት ጎዳና ላይ የተሠሩ ጥናቶች ጋር የተያያዘ ነው። ‘እነዚህ አገራት ምን አድርገው ነው በዚህ ፍጥነት ሊያድጒ የቻሉት? ሌሎች አገራት የነሱን ፈለግ ቢከተሉ በተመሳሳይ ደረጃ ይሳካላቸው ይኹን?’ ወዘተ…  የሚሉት ጥያቄዎች የዓለምን ማኅበረሰብ (በተለይ ልህቃኑን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ፖለቲከኞችን) ትኲረት የሳበ አጀንዳ ሆኗል። ከዚህ የተነሣ በጒዳዩ ላይ ብዙ የጥናት ሥራዎች ተሠርተዋል። አንዳንዶቹ ዕድገቱን ከምዕራባውያን እርዳታ ጋር ያያይዙታል። አገራቱ ከተለያዩ ለጋሽ አገራት ያገኙትን ዕርዳታ በሚገባ በመጠቀም ዕድገት ሊያስመዘግቡ ችለዋል የሚል ነው።

ሌሎቹ ደግሞ የጃፓን የዕድገት ፖሊሲ ጋር ያያይዙታል። እንደሚታወቀው ጃፓን ከምዕራቡ ዓለም ወደ ኋላ ቀርታ ለረጅም ዘመናት እንደ ኢትዮጵያ ዝግ ፖሊሲን የምትከተል አገር ነበረች። ነገር ግን በአንድ ወቅት ላይ ከአውሮፓ አገራት ጋር ባደረገቸ ጦርነት በመሸነፏ ትልቅ ትምርህት አግኝታ የተዘጒ በሮቿን ከፋፍታ ከአውሮፓ ጋር ለመተካከለ ጥረት ማድረግ ጀመረች። በአጭር ጊዜ ውስጥም ኃያልነቱን ተጎናጸፈች። የሷ ዕድገት ቀጥታ በኮሪያና በታይዋን ላይ ተንጸባርቋል የሚል አቋም ነው ከጃፓን ጋር የተያያዘው መላምት። ሌሎቹም ከኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ጋር ያያይዙታል። ግማሹ ለዘብተኛ ሲሆን ግማሹ ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት ቊጥጥርና ጣልቃ ገቢነት የተደረገበት ነው። ሌሎች ጥናቶች ደግሞ ለውጡን በመሬት ፍትሐዊ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይሞግታሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የምርት ሂደቱ እምርታ ከውጪ ባስገቧቸው ቴክኖሎጂዎች ያመጣው ተጽዕኖ እንደሆነ ያትታሉ።

እኔ ትኲረት ማድረግ የፈለግኲት ግን የማኅበረሰቡ ባህል ላይ የተመሠረተው ሙግት ላይ ነው። ይህ አቀራረብ በቀጥታ የሚገናኘው ከኮንፉሺየስ ሃይማኖታዊ አስትምህሮ (ፍልስፍና) ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን የመረጥኲበት ምክንያት የአንድ ማኅበረሰብ ባህል ወይም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በሥልጣኔ ወይም በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ለማሳየት ነው። ምን ያህል የተሻሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቢቀረጹ የማኅበረሱ አስተሳሰብ ፖሊሲውን ለመተግበር የማይመች ቢሆን ወይም በተጻራሪነት የሚቆም ቢሆን የለውጥ ጒዞው መሰናክል እንደሚገጥመው ምንም ጥርጥር የለውም። በኛ አገር አውድም ይኸ ጒዳይ በብዙ መንገድ ተንጸባርቋል። የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ጒዞ የተሰናከለው በዚህ መንገድ ይመስለኛል። ሆኖም ግን እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥናቶችና ትግሎች የተደርጒ አይመስለኝም። አብዛኛውን ጊዜ ላለማደጋችን ተጠያቂ የምናደርገው ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ብቻ ናቸው ብለን ስላመንን ሥዓቶችን ለመቀያየር ብዙ ትግሎችን አካሂደናል። ከፖለቲካ ባሻገር በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኲረት ሲደርግ ብዙውን ጊዜ የተለመደ አይደለም። የፖለቲካ ሥርዓት ቢስተካከል ግና የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ካልተዘጋጀ አሁንም የተሻለ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አላምንም።

የኮንፉሺየስ አስተምህሮና የሥራ ባህል

ኮንፉሻውያን (Confusianism) በቻይና ውስጥ 2,500 ዓመታትን የዘለቀ ሃይማኖታዊ ፍልስፍና[1] ነው። ሃይማኖቱ ስሙን ያገኘው ኮንፉሺየስ ከተባለውና ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ551 እስከ 479 ዓ.ዓ ድረስ ኖሯል ተብሎ ከሚታመን ሰው ነው። ምንም እንኳን ኮንፉሺየስ ከሞተ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ጥሎት ያለፈው አሻራ ለዛሬው ማኅበረስ ጠቃሚ እሴት ሆኖ ተገኝቷል። የኮንፉሺየስ ሃይማኖት በደረሰባቸው እንደኔ ኮርያ፣ ሲንጋፖር፣ ቻይናና ጃፓን አካባቢዎች ባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ባህል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። በአንድ በኲል ኮንፉሺየዝም ሃይማኖት ሲሆን በሌላ በኲል ግን የሕይወት ፍልስፍናም ነው። የሕዝባዊት ቻይና መንግሥት እስከተመሠረተበት እሰከ 1911 ዓ.ም ደረስ ኮንፉሺየስ የቻይና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ ለ2000 ዓመታት ዘልቋል[2]

ሃይማኖቱ በዋናነት ትኲረት የሚያደርገው ውስጣው ሰብዕና ግንባታ (inner virtue), የግለሰቦች ግብረ ገባዊ ሕይወትና ማኅበራዊ መስተጋብር ውህደት (Harmony) ላይ ነው። እነዚህ እሴቶችን ሁለት ቦታ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የጀመጀመሪያ አምስቱ መስተጋብራዊ ተዋረድ (Hierarchical relations) የያዘ ሲሆን እነዚህም ገዢና ተገዢ፣ አባትና ልጅ፣ ባልና ሚስት፣ ታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች እና ጓደኛና ጓደኛ ግንኙነቶችን የሚያጠቃልል ነው። በእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለው መስተጋብር በመከባበር ላይ የተመሠረት ነበር፣ ተገዢዎች (ሕዝብ) ለገዢዎቻቸው (መንግሥት) መታዘዝ አለባቸው፣ ልጅ ለአባቱ ፍቅር (filial piety) ማሳየት አለበት፣ ሚስት ለባሏ መገዛት፣ ባል ደግሞ ሚስቱን መወደድ፣ ታናሽ ወንድም ለታላቅ መታዘዝ ታናሽ ደግሞ ታላቁን የማክበር ግዴታ ይኖርበታል፣ ጓደኛሞችም እርስ በርስ መከባበር ይኖርባቸዋል። ይህ የግንኙነት ሰንሰሌት ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠሪያ ምሶሶ ነው። የኮንፉሺየስ አስተምህሮ ዋና ግብ ተደርጎ የሚወሰደው እራሴን በሥነ-ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ፣ የራስን ቤት በወጒ ማስተዳደርና ለመንግሥታዊ ሥልጣን ተገቢውን አክብሮት መስጠት ናቸው። ይህ በማኅበር መካከል የሚፈጠረውን መስተጋብር የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግለሰቦች ሊኖራቸው የሚገቡ አምስት የሥነ-ምግባር እሴቶች ተብለው የሚጠቀሱት አሉ፣ እነዚህም፦

ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም መሆን፣ ወይም ማደረግ (Benevolence)፣ ቅድስና (righteousness)፣ ብልጽግና (prosperity)፣ ጥበብና (Wisdom) ታማኝነት (Trustworthness) ናቸው።  እነዚህ አስትምሮዎች የኮንፉሺየስ ሃይማኖት ምሶሶዎች ሲሆኑ የግለሰቦችን ውስጣዊ ማንነት ላይ የሚያተኲሩ ናቸው። ሁሉትንም የአስተምህሮ መሠረቶች አንድ ላይ አዋህደን ብንመለከታቸው አንድ ማኅበረሰብ በጋራ ለመኖር የሚያስፈልጒ ጠንካራ እሴትን ይፈጥራል። ግለሰብ የራሱን ማንነት በመልካምነት እንዲገራ፣ ለራሱ ቤተሰብ ክብርና መልካም ስም የሚታገል፣ እንዲሁም ለበላይ ባለ ሥልጣናት ተገቢውን ክብር የሚሰጥ ከሆነ በአጠቃላይ በሰው ልጆች መካከል ጠንካራ ሕብረት የፈጠራል። ባጭሩ ግን ስንመለከት ትምህርቱ ግለሰቦች ከራሳቸው ጋር እንዲሁም ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ተገቢ ተግባቦት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩ፣ እንዲደማመጡና ለጋራ ብልጽግና አብሮ መቆም እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል።

ልክ የፕሮቴስታንት የሥራ ባህል በአውሮፓና በአሜሪካ የተፈጠረውን የካፒታሊዝም ሥርዓት ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል ተብሎ እንደሚታመን ሁሉ የኮንፉሺየስ ሃይማኖት ባለባቸው እንደ ቻይናና ጃፓን ባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወት ጥናቶች ያሳያሉ። ነገር ግን የኮንፉሺየስ ከአውሮፓ የሚለየው የአውሮፓ የሥራ ባህል የግል ሀብት ማከማቸት ላይ የሚያተኲር ሲሆን ኮንፉሺያኒዝም ግን ትኲረቱ የማኅበረሰብ ጥቅማ ማስቀድም ላይ ያተኲራል[3]። ፍልስፍናው የአሜሪካ ፕረዚደንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ “አገራችሁ ምን እንዳደረገችላችሁ ሳይሆን ምን እንዳደረጋችሁላት ጠይቁ” ያለው ዓይነት የሚመስል ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ከአገሩ በሚያገኘው ሳይሆን በሚያበረክተው አስተዋጽዖ ነው ስኬቱ የሚለካው።

ባህሉ ከልማት ጋር እንዴት ይገናኛል?

ከላይ እንዳየነው የኮንፉሺየስ ሃይማኖት ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር ከመፍጠሩም በላይ በግለሰቦች ባህሪይ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዕ ማሳደር ችሏል። አሁን ደግሞ ይህ ማኅበራዊ እሴት የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮችን የልማት ጒዞ እንዴት እንደረዳ እንመልከት።

የመጀመሪያው ሐሳብ በኮንፉሺየስ ሃይማኖት “ዓለማዊና መንፈሳዊ” የሚባል ክፍፍል አለመኖሩ ነው። ከተሐዲሶ በፊት አውሮፓ ውስጥ ሲተገበር የነበረውና ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየው ክርስቲና ሕይወትን ዓለማዊና መንፈሳዊ በማለቱና ዓለማዊ የተባለውን በመናቅ ወደ መንፈሳዊ ብቻ በማድላቱ በልማት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳመጣ ብዙ ምሁራን እንደሚስማሙበት አይተናል። በኮንፉሺየስ ሃይማኖት ግን ለሥራ ከፍተኛ ትኲረት የሚሰጥና የሚሠሩትንም የሚያበረታታ ነው። እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የተጣለበትን ኃላፊንት የመወጣት ግዴታ ስለሚጥልበት ሁሉ በየፊናው ይታትራል። ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው እሴት ደግሞ የማኅበረሰብን ብልጽግና የሚያመጣ ተግባር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ነው።

Follow what is of profit to the people and profit them.

Confucius.

ሁለተኛውና ወሳኙ የኮንፉሺየስ ሃይማኖት አስተዋጽዖ ለበላይ ባለሥልጣን ያላቸው አመለካከት ነው። ይህንን ሐሳብ ለማብራራት እንዲረዳን ልማት ሊያመጣ የሚችል የመንግሥትና የሕዝብ መስተጋብ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የሚያስረዱ ሌሎች ሥራዎችን በስሱ ለመመልከት እንሞክር።

ታዋቂው ‘የፍቅር እስከ መቃብር’ ልቦለድ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?” በሚለው መጽሐፋቸው ለሃይለስላሴ መንግሥት አንድ አዲስ የአስተዳደር ሥርዓት አስተዋውቀው ነበር። ይኸውም እንደ ምዕራቡ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እንዴ ምሥራቊም አምባገነን ያልሆነ አማካይ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት ከሦስት የማይበልጡ ፓርቲዎች ለአሥር ዓመታት የሚሠሩበትን የኢኮኖኖሚ ፖሊሲ ያወጡና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ ያቀርባሉ። ሕዝቡ የተሻለ ነው ያለውን ይመርጣል። ፖሊሲው የተመረጠለት ፓርቲ ለቀጣዩ አሥር ዓመታት ድረስ ያለ ምንም ተቀናቃኝ ያቀደውን ዕቅድ ተግባራዊ ያደርጋል ማለት ነው። ምርጫ በመኖሩና የሥልጣን ዘመኑ እስከ አሥር ዓመት በመገደቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመስላል፣ አሥር ዓመት እስኪሞላ ድረስ ምንም ዓይነት ተቃወሞም ሆነ መሰናክል የተከለከለ በመሆኑ ከፊል አምባገነን ይመስላል።

ይህንን የመሰለ የመግሥት አማራጭ ያቀረበበት ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ያላደጉ አገሮች ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢሆን በጊዜው ተቃውሞ እየተነሣ ስለሚያስቸግር የተመረጠው መንግሥት ያቀደውን በውጒ ሳይተገብር ተቃውሞውን እየተከላከለ ልማቱን ይተዋል የሚል ነው። ሌላው በአራት ወይም አምስት ዓመታት ምርጫ የሚደረግ ከሆነ አንደኛው መንግሥት ያቀደውን የልማት ዕቅድ ገና ለመተግበር ሲሞክር የሥልጣን ዘመኑ ስለሚያልቅበት ልማት አይመጣም የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። ሙሉ በሙሉ አምባገነን እንዳይሆን ደግሞ ሥልጣኑ ገደብ ስለማይኖረው የሕዝብን ጥቅም ይዘነጋል። ያደጉ አገራት ጠንካራ ተቋማትና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ስላላቸው በየአራት ወይም አምስት ዓመታት መንግሥታቸውን ቢቀያይሩ ብዙ ችግር አያመጣባቸውም ነው ክርክሩ።

ከዚህ አንድ ጥሩ ሐሳብ መውሰድ እንችላለን። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የሚኖረው መስተጋብር በልማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚያሳይ ሐቅ አለ። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግኙነት ጤናማ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልማት ማምጣት እንደማያስቸግር እንዲንገነዘብ ያደርገናል።

በእነዚያ አገራት የተፈጠረውም ይኸ ይመስላል። የኮፉሺየስ ሃይማኖት ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት መታዘዝ አለበት ብሎ ስለሚያስተምር፣ አስተምህሮውም እንደ ባህል በሕዝብ ውስጥ ዘልቆ ስለገባ ጥሩ የልማት ዕቅድ ይዞ የመጣው መንግሥት ወዲያውኑ ውጤታማ ሊሆን ችሏል። ምክንያቱም የመንግሥት ትልቁ ትኲረት ያቀደውን ዕቅድ ወደ ተግባር የሚለውጥበትን መንገድ ብቻ ማፈላለግ እንጂ ገና ተቃውሞ ይገጥመኛል የሚል ሥጋት አይኖርበትም። ባህሉ ቀድሞውኑ የሕበረተሰቡን አእምሮ አደላድሎ አዘጋጅቷል ማለት ይቻላል። ስለዚህ አቅማቸውን የሚያውሉት በልማት ላይ እንጂ በሥልጠና፣ ግንዛቤ መፍጠሪያ ወይም በማሳመኛ ጉዳዮች ላይ አይሆንም።

በተቃራኒው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሁሌ መጠራጠር ካለ ልማት አይኖርም። ወደ ሥልጣን የመጣው አካል ቅድሚያ የሚያደርገው የራሱን ደህንነት የማስጠበቅ ጒዳይ ይሆናል። ሕዝብ መንግሥትን የማያምን ከሆነ መንግሥትም ሕዝብን ስለማያምን ትልቁ ትኲረት የሚያደርገው ሥልጣኑን ከአደጋ የሚያስጠብቅበትን ሥርዓት በመግንባት ላይ ነው። ጥሩ ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜም ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል። ከዚህ የተነሣ ከልማቱ ይልቅ ሰዎችን በማሳመን ወይም በማሠልጠን ላይ ጊዜ ያልቃል።

ጆን ስቲዋርት ሚል የተሰኘ እንግሊዛዊ ፈላስፋ “ሳቬጅ” በሚለው ጽሑፉ ያለመተባበር ጣጣ የሥልጣኔ ጠንቅ እንደሆነ አብራርቷል። ፈላስፋው “savage” ወይም አረመኔዎች ብሎ የሚጠራቸው ማኅበረሰቦች እርስ በርስ የመተባበርና በጋራ ሥልጣኔ የመፍጠር አቅም የላቸውም ይላል። እንደ ፈላስፋው አገላለጽ ሥልጣኔ የሚፈጠረው በማኅበረሰብ መተባበርና መደማመጥ ሂደተ ውስጥ ነው።  

We find human beings acting together for common purposes in larg bodies, and enjoying the pleasures of social intercourse, we term them civilize.”

በተቃራኒ ያልሠለጠኑ ማኅበረሰቦች

“… In savage communities each person shifts for himself, except in war (and even then, very imperfectly), we seldom see any joint operations carries on by union of many, nor do savages”

ያልሠለጠነ ማኅበረሰብ ውስጥ ሕግ አይከበርም፣ ፍትሕ አይረጋገጥም፣ ማኅበረሰቡ በትብብር የሚያገኘው አቅም የለውም (ትብብር የለም፣ በጦርነት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር) ፣ ማኅበረሰቡ የአባሉን ሕይወትና ንብረት አይጠብቅም ወዘት. . . ይላል ፈላስፋው።  አለመተባበርና ሁልጊዜ ትግል ውስጥ መኖር የአራዊት ባህሪይ ነው።

ከዚህ እንደምንረዳው ለአንድ ማኅበረሰብ አለማደግ ተጠያቂው ሥልጣን ላይ የውጡ ቡድኖች ብቻ አይደሉም፣ ይልቊን ገዢዎችም ተገዢዎችም እኩል ኃላፊንት አለባቸው። በእርግጥ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ቡድኖች የሕዝብ ነጸብራቅ መሆናቸው የሚካድ አይደለም። መሪዎች ከሕዝብ ነው የሚወጡት። በማኅበረሰቡ ባህልና ሃይማኖት ተጎትጉተው ያደጉ በመሆናቸው ወደ ሥልጣን በሚወጡበት ጊዜ ያንኑን ነው የሚያንጸባርቊት።

የኮንፉሺየስ ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ሥነ-ልቦና ላይ የመቀባበልና የመደጋገፍ ተጽዕኖ ስላሳረፈ ጥሩ የልማት ፖሊሲ የቀረጹ መሪዎች ሳይቸገሩ አገራቸውን ቶሎ ከድህነት ሊያውጡ ችለዋል።

በተቃራኒ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች በሕዝብና በመንሥት መካከል ከፍተኛ ያለመተማመን ሁኔታዎች ስለነበሩ በየዘመናቱ ለውጥ ማምጣት ያሰቡ ሰዎች ተቸግረዋል። ይህ የሆነው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የተፈጠሩ ግንኙነቶች ሸካራዎች ስለነበሩ ነው። መንግሥት ማለት የማይሠሩ ግለሰቦች የተሰበሰቡብት ቡድን፣ ሙሉ በሙሉ በገበሬው ትከሻ ላይ ሸክም የሚያከብድ, ከዚያም አልፎ የሚቀጣ፣ የሚገድል፣ ነጻ የጒልበት ሥራ የሚያሠራ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊንት የሌለበት አካል ነው።

“ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ” የሚባልው ማኅበረሰባዊ ፍልስፍና ራሱ መንግሥታት ከተጠያቂነት በላይ እንደሆኑ ያሳያል። በሌላ በኩል ወደ ሥልጣን የሚወጡ ሰዎች የማኅበረሰቡን ሕይወት የመቀየርና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ግዴታ የተጣለበት አካል ሳይሆን የራሱን ኑሮ ለማደላደልና ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሕዝብን መዝረፍ እንደ ባህል ተወስዶ ይታያል። ለዚህ አቢነት መጥቀስ ቢያስፈልግ “ሲሾም ያልበበላ ሲሻር ይቆጨዋል” በሚለው ማኅበረሰባዊ ይትብሃል ውስጥ ተንጸባርቆ እናገኛለን።

ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያውያን የ “እንቢ” ባይነት ሥነ-ልቦና ለአዳዲስ አሠራሮችና ሕጎች ተገዳዳሪ ሆኖ ታይቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የተለመደ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል። አብዛኞቹ ጦርነቶች ደግሞ ርስ በርስ የተደርጉ ናቸው። ዋና የጦርነት መንስኤ ደግሞ በበጦር አበጋዞች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ ነው። አንዱ ይነግሳል፣ ለሕዝቡ ተገዙልኝ የሚል አዋጅ ያስነግራል። አቅም አለኝ ያለ ማንኛውም ጉልበተኛ ደጋፊዎችን አሰባስቦ የነገሰውን ሰው ሊፋለም ይሸፍታል። በአንድ በኲል ይኸ የእንቢ ባይነት ሥነ ልቦና አገራችን ከውጪ ከተቃጣበት ጥቃት ለመመከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፣ በተለይ ቅኝ ገዢዎችን በመከላከል ረገድ። በሌላ በኩል ግን እርስ በርሳችንም እንዳንደማመጥና እንዳንከባበር ምክንያት ሆኗል። አንዱ በጒልበት ይነግሣል፣ ሌሎቹ ድግሞ የነገሠውን ለመጣል ፍልሚያ ይጀምራሉ።

ሌላው መንግሥት የሚያመጣቸው የለውጥ እሳቤዎች በጥርጣሬ ሲታዩ ተስተውሏል። የሩቅን ትተን በዘመናችን ብቻ ተሞክረው ያልተሳኲ ዘመናዊ የአሠራር ስልቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚሀም ቢፒአር. ቢፒሲ እና ካይዘንን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎች ሌሎች ዓለማት ውጤታማ የሆኑባቸው ስልቶች ናቸው ተብለው እንደ ተሞክሮ የተወሰዱ ነበር፣ ሆኖም ግን ተስፋ እንደተጣለባቸው ሆነው አልተገኙም። ምክንያቱ ምንድን ነው? ለዚሀ ነው የአስተሳስብ ለውጥ ካልመጣ የትኛውም ዘመናዊ አሠራር ቢተገበር ውጤታማ የመሆኑ ጒዳይ አጠራጣሪ የሚሆነው። 


[1] ኮንፉሻውያን (Confusianism) ሃይማኖት ነው ወይስ ፍልስፍና ነው በሚለው ሐሳብ ዙሪያ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ክርክሮች አሉ።

[2] Brenda L. Geren: The Chinese Work Ethic: Significance of Confucianism

[3] https://www.virtuegaming.co.uk/blog/confucian-work-ethic

2 Comments

  1. tesfaye chenfa

    አዎ የአስተሳሰብ ለውጥ በጣም ወሳኝ ነው ። ካልሆነ ግን ህዝቡ ወርቅ ብታነጥፍለት ፋንድያ ነው እያለ አገዛዞችም ለህዝባቸው ያሰቡትን አንዳች ነገር ገብራው ሳያደርጉ እየተተካኩ የዘሮ ድምር ህደቱን እያስቀጠሉ ይቀጥላሉ ።

    • በጣም የሚገርመው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ሳይለወጥ ሳይመጣ ሰዎችንና ሥርዓትን በመቀያየር ለውጥ የሚመጣ ይመስላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *