(ባህልና ክርስቲና)
ክፍል-፪
ሰውዬው አቃጠለ የተባልው ዕቃ ምን ዓነንት ቢሆን ነው? ብዙውን ጊዜ ከሰይጣን የሚሰጡ ትዕዛዞች እኔም በተወሰነ መልኲ ስለማውቃቸው ለባህላዊ ቅርስነት የሚበቁ ናቸው ብሎ መደምደም እጅግ አስቸጋሪ ነው። በትንሽ ጨርቅ የተጠቀለለ ነገር፣ ወይ የሞተ ነገር መቅበር፣ ወይም ጥቃቅን የሆኑ ዕቃዎችን ምስጢራዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ መደበቅ ሊሆን ይችላል። አልፎ አልፎ እንደ ዛፍ፣ ድንጋይ ወይም ከተፈጥሮ ነገሮች አንዱን ላይ መሰዋዕት ማድረግ ነው። ታዲያ እነዚህ ቊሶች ባይቃጠሉ እንኳን በጊዜ ሂደት መጥፋታቸው የሚቀር አይሆንም።
ግን ለምን ተቃጠሉ? መቃጠላቸው ስህተት ነው? ታምራትም እንዳለው ሰይጣን ሰው ውስጥ እንጂ ዕቃ ውስጥ ስለማይኖር ሰይጣኑን አባርሮ ዕቃውን መጠቀም አይቻልም?
የኔ መልስ ዕቃዎቹ መቃጠላቸ ተገቢ ነው እላለሁ። ምክንያቶቼ እነዚህ ናቸው።
1ኛ፡ ከውክልና አንጻር
ሰይጣን ቁስ ውስጥ አለመኖሩ እውነት ነው፣ ዕቃው ግን የውክልና ሚና አለው። አንድ ሰሞነኛ ምሳሌ ላምጣ። በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ የተከሰተ ክስተት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ አቀንቃኞች ምልክት የሆነውን የቀስተ ደመና (Rainbow) ምልክት ያለበት አውሮፕላን ይዞ ሲገባ አየር ማረፊያዋን ከልክላ የመለሰችው ለምን ድን ነው? አውሮፕላኑ የጫነው የጀርመን እግር ኳስ ቡድንን እንጂ ግበረሰዶማውያንን አልነበረም አይደል እንዴ? ግን ምልክቱ በሐሳባቸው እንደመስማማት ስለሚቆጠር አላስተናገደቻቸውም፣ በግጥሚያዎች ወቅትም የትኛውም ብሔራዊ ቡድን የነሱ ምልክት የሆነውን Armband እንዳያደርጉ ያገደቻቸው ምልክቱ በሰዎች ሐሳብ መስማማትን ስለሚያመልክት ነው። Symbolism በጣም ወሳኝ ነገር ነው። መስቀለ የክርስቲያን ምልክት እንደሆነ ይታወቃል፣ ጨረቃ ደግሞ ሙስልሞችን ይወክላል። የኢትዮጵያን ባንዲራ ብታቃጥል፣ ኢትዮጵያ አልተቃጠለችም፣ ጨርቅ ነው የተቃጠለው ብሎ በዝምታ የሚያልፍህ ኢትዮጵያዊ አይኖርም።
በ አቶ ካርሞ ቂሣ ሕይወት የተከናወነም ተመሳሳይ ነገር ነው። ሰውዬው ከምስክረነቱ እንደምንረዳው ለዘመናት ከሰይጣን ጋር ጥብቅ ቁርኝት የፈጠረ ሰው ነው። በሰይጣንና በሱ መካከል ስምምነቶች አሉ። ከዚህ በኋላ የሰይጣን ሳይሆን የክርስቶስ ሆናለሁ ካለ መጀመሪያ ከሰይጣን ጋር የነበረውን ውሉን ማፍረስ አለበት። አንዲት ሴት የመጀመሪያ ባሏን ፈትታ ሌላ ሁለተኛ ባል ማግባት ብኖርባት፣ ከመጀመሪያ ባሏ ጋር ያላትን የጋብቻ ውል ማፍረስ አለባት። የዚህ ዓይነተኛ ምልክት የሆነውን ቀሌበት ማስወገድ አለባት። ሰዬው ያለው ቀሌበት ላይ ነው እንዴ? ቀሌበቱ በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል ውል/ቃለ ኪዳን መኖሩን የሚያሳይ ምልክት እንጂ የሰው ፍቅር ቊስ ላይ አያርፍም። ተመሳሳይ ነገር ነው የሆነው። ጠንቋይ እንዲጠቀም የሰጣቸውን ቁሳቁሶች እየተጠቀመ ክርስቲያን ሆኚያለሁ ማለት አይችልም።
2ኛው፣ ከሥነ-ልቦና አንጻር
አንድ ሰው የሆነ ነገር ይጎዳኛ፣ ወይም ከጒዳዩ ጋር በተያያዝ ክፉ ትዝታ የሚቀሰቅስበት ከሆነ ያለው አማራጭ ከነገሩ መራቅ፣ ወይም ከቻለ ማጥፋት እንደሚኖርበት ይመከራል። ለምሳሌ ሱስ ያለበት ሰው ሱሱን ለመተው በሚወስንበት ጊዜ የመጀመሪያ እርምጃ የሚሆነው ያንን ትዝታ የሚቀሰቅስበትን ነገር መራቅ ወይም ማስወገድ ነው። ጫት ሰፈር እየኖሩ ጫትን መቃም አቆማለሁ ማለት አይቻልም፣ የሚያጭስ ጓደኛ ጋር እየዋሉ፣ ከሲጋራ ሱስ ነጻ ወጣለሁ ማለት ዘበት ነው።
አቶ ካርሞ ቂሣ ከሰይጣን ጋር ባለው መስተጋብር ደስተኛ የሆነ ሰው አልነበረም፣ ነጻ መውጣት ይፈልጋል፣ ግና ደግሞ ይፈራል። ፍራሃቱ የሰይጣን ትእዛዝ ባለማክበሩ ምክንያት የሚደርስበት የሰይጣን የበቀል እርምጃ ነው። ስለዚህ ያለው አማራጭ ሙሉ በሙሉ ከሰይጣን ጋር ያለውን ሕብረት ማቋረጥ ይኖርበታል፡ ሰይጣንን እንዲያስታውስ የሚያደርጒ ማናቸውም ነገሮም መወገዳቸውም ከስነ-ልቦና አንጻርም ድጋፍ አለው።
2ኛ ከሕግ አንጻር
ጥንቆላና ከጥንቆላ ጋር የተያያዙ ድርጊቶች የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የሚደግፍ አይመስለኝም። በጥንቆላ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች በማስፈራራትም ይሆን በማታለለ አሊያም ሰይጣናዊ ተጽዕኗቸውን በመጠቅም ኅበረተሰቡን የሚበዘብዙ ከሆነ ድርጊቱ ሕገ-ወጥ ስለሆነ በዚህ ሥራ የሚሳተፉም ሆነ በድርጊቱ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ነጻ መውጣት ይኖርባቸዋል( የታምራት ገለታን ታሪክ ያስታውሷል)
3ኛ፡ በሰዎች ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ
ዛሬ የምንገለገልባቸው ዕቃዎች ነገ በሌላ ነገር ሊተኩ እንደምችሉ ምን ያህሎቻችን እንገነዘባለን? ያኔ የነበሩ ሰዎችም የሚገለገሉባቸው ዕቃዎች እንደማንኛውም ዕቃ ነው እንጂ የሚያዩት፣ ባህላዊ ቅርሶች ናቸው ብለው አይገነዘቡም። ቅርስ የሚሰበስቡት የቅርስ ባለሙያዎች እንጂ ቅርሱን የፈጠሩ ሰዎች አይደሉም። የተሻለ ነገር ሲመጣ ማንም ሰው የቀደመውን እየተወ ወደተሻለው ይሄዳል፣ ይህ ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ነው። የራሴ ባህል ነውና የድሮ ይሻለኛል አይባልም፣ በትራክተር ማረስ እየተቻለ በባይራ ማረስ ማንም አይመርጥም።
ሲጠቃለል
ባህል ከሰዎች ሕይወት ጋር አብሮ የሚያድግ ነገር ነው። እያንዳንዱ ትውልድ ካለፈው ትውልድ መሠረት ላይ ቆሞ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር አለብት እንጂ ትናንት ላይ ተችክሎ ባለበት መርገጥ የለበትም። የዶክተር ምህርት ደበበ መጽሐፍ ላይ እንደተረዳሁት ከሆነ የኮንሶ ባህል ባለበት የመርገጥ ዕጣ ገጥሞታል። ጨቃ፣ አረቄ፣ ዳማ፣ ካብ፣ ኡዋ፣ ኮንፋ፣ ሮካ ወዘተ. . የፈጠረ ትውልድ ነበር፣ ከዚያ በኋላ ሌላ ፈጠራ የለም?
“ባህል ስንል ዝም ብሎ የተቀመጠ ነገር ሳይሆን፣ ሁልጊዜ የምንፈትሸው፣ የምንመረምረው፣ የምንነጋገረው፣ ትርጉም የምንፈልግለት መሆን አለበት፡፡ ይሄም መደረግ ያለበት ባህል ወላድ (Productive) እንዲሆን ነው፡፡ ቆሞ ቀር እንዳይሆን፣ እንደ ኩሬ ውሃ አንድ ቦታ ረግቶ የከረፋ ሽታ እንዳያመጣ ነው፡፡ ባህል ህያው የሚሆነው ወላድ ሲሆን ነው፣ ወላድነቱም የሚገለጸው በየመስኩ፤ በኪነ ጥበብቡ፣ በፍልስፍናው፣ በሳይንሱ፣ በኪነ ሕንፃው፣ በሥነ ጽሑ… ባህሉን የሚተነፍሱ ሰዎን ሲያፈልቅ ነው[1]፡፡
ኮንሶም ለዓለም የሚበቃ ቱባ ባህል እንዳላት የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን ባህል ለራሷ ብቻ ይዛ መቆየት ብዙ የሚያዋጣት ባለመሆኑ ለሌሎች አካባቢዎች የመጋራት ኃላፊነት አለባት፡፡ የዛሬው ትውልድ ባህሉን በሚገባ አውቆ ለሌሎች ካላሸጋገረ የነገው ትውልድ ይረሳዋል፡፡ ፕሮሞት ኮንሶ ይህንን ተግባር እያከናወነ በመሆኑ ሁላችንም ድጋፍ ችረነዋል። በዚያው ልክ ደግሞ ባህል ሲባል የማይጠየቅ፣ የማይመረመርና የማይስተካከል ነው ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ትውልድ ከሌላኛው ትውልድ እየተማረ ከጊዜው ጋር አብሮ መዘመንና ማዘመንም መረሳት የለበትም፡፡
ሚሽነሪዎች በነበሩበት ዘመን ያለውን የኮንሶ ሁኔታ ስለማናውቅ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፡፡ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ግን ባህል በምን ምክንያት እንደሚጠፋ የታወቀ ነው፡፡ የ18ኛ ክፍለ ዘመን አብርሆት (Enlightenment) ፍልስፍና ያመጣው ጣጣ ምንም ዓይነት ባህል ወይም ሃይማኖት አያስፈልግም የሚል ነበር፡፡ የሁሉ ነገር ዳኛ አመክንዮና ሳይንስ ናቸው ተባሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ባህሎችና ነባሩ ትውፊቶች እጅጉን ተናግተዋል፡፡ ሃይማኖቶቹም ተናግተዋል፣ ፈላስፎቹም በአሸናፊነት መንፈስ እግዚአብሔርንም ጭምር ከሰው አእምሮ አስወግደናል አሉ፣ ያኔ እግዚአብሔር የለም ባዮች አሸንፈናል ሲሉ በተቃራኒው በእግዚአብሔር ማመንም ሆነ በድሮ ትውፊቶችና ባህሎች ታማኝነት ማሳየት ኋላ ቀርነት ሆኖ ቀረበ፡፡ ሃይማኖቶችና ባህሎች የሰው ልጆችን የኋሊት የሚያስሩ ደንቃራ ነገሮች መሆናቸው ታመነበት፡፡
ሆኖም ግን ከ1ኛና 2ኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም አስተሳሰቧን ቀየረች፡፡ የሰው ልጅ በሳይንስ እገዛ ባህሪው ተለውጦ ከትናንትናው ይልቅ የተሻለ ይሆናል፣ ዓለም እየተለወጠች የበለጠ ፍትሐዊ እየሆነች ትመጣለች የተባለችው እጅግ አስፈሪ የሞት መድረክ ሆና አረፈች፡፡ ሰው በምክንያት ያልተለወጠ ብቻ ሳይሆን ሰይጣናዊ ባህሪይን ተላበሰ፡፡ ዓለም ባነደደችው የጦርነት እሳት ተለበለበች። ከዚያ በኋላ የጣለችውን ሃይማኖትና ባህል ከወደቀበት አቧራ እያነሳች ማውለብለብ ጀመረች፡፡ 21ኛው ክ/ዘመን የባህልና ሃይማኖት ትንሳዔ የተደረገበት ይመስላል፡፡ ብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ለውይይት ወደ መድረክ ሲወጣ ባህልን አስከትሎ ወጣ፡፡ አሁን አሁን “እግዚአብሔር የለም” ማለት በተራው ኋላ ቀርነት ሆኖ አረፈው፡፡ እንደ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አባባል “በዚህ ወቅት ባለው ሁኔታ እግዚአብሔር አለ የሚል አቋም ያላቸው ፈላስፎች የለም የሚሉትን 3ለ1 እየመሯቸው ነው፡፡”[2] የሃይማኖት መብዛትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ያለው ፈተና ሃይማኖትም ሆነ ባህል አያስፈልግም የሚል ሳይሆን ሁሉም ልክ ናቸው የሚለው ነው፡፡
ሌላው ሞደርናይዜሽን የምንለው ሐሳብ አውሮፓዊ ማድረግ መሆኑን ከተረዳን የባህል ጠላት ከየት እንደሆነ አቅጣጫው አይጠፋንም፡፡
አሁን ትልቁ የባህል ሥጋት ግሎባላይዜሽን እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖቱ ራሱ መች የግሎባላይዜሽንን ወፍራም ክንድ መቀቋቋ ችሎ ነው ለተጽዕኖ የሚበቃው?
[1] ብሩህ ዓለምነህ፤ የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣የዘርዓ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች ትንታኔ ከነ ሐተታቸው (ነሐሴ 2009)፣ አዲስ አበባ ገ.
[2]ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፣ ፍልስምና ፪ (አምላክ፣ ሰውና ሃይማኖት) 2004 ዓ.ም አ.አ፣ ገጽ108