(ባህልና ክርስቲና)
ክፍል-፩
የክርስቲና እምነት የኮንሶን ባህል አጥፍቷል የሚለው እጅግ የተጋነነ ድሚዳሜ መነሻው ዶክተር ሻኮ ይመስለኛል። ዶር ሻኮ “Traditional Konso Culture and the missionary Impact” ብለው ባሳተሙት መጣጥፍ ላይ ሚሽነሪዎች በኮንሶ ባህል ላይ ያሳረፉት ተጽዕኖ የደረሰበት ድሚዳሜ እና ታታሻ “ባህልና እሴት ለመንከባከብ ሃይማኖት ስጋት ወይስ ዕድል” ብሎ ያቀረበው ሐሳብ ይመሳሰላል፡፡ ሁለቱም ለኮንሶ ባህል መሸርሸር የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን ተወቃሽ ያደርጋሉ፡፡ የሁለቱም ስህተት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት አስተምህሮን በወጉ ካለመረዳት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ ዶሩ አንዳንድ ሃይማኖቱን የተቀበሉ ሰዎች ቀድሞ ሲያደርጉት የነበረውን አንዳንድ ድርጊቶችን በማቆማቸው ምቾት ይነሳው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ዶር ሻኮ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ እምብዛም የማያስጨንቅ መሆኑን የምንገነዘበው የክርስቲና መሠረታዊ ሐሳብ ወንጌል የተባለውን መልዕክት ባህል አውዳሚ ብሎ መውሰዱ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሚሽነሪዎች ሲያቀነቅኑት የነበረውን መሪ ሐሳብ “You live in Darkness and suffer under devil until you have been saved by Christ” የሚለውን “Spearheaded by this motto, it leaves no free area in the Konso culture which is not interfered with” ብለው ገልጸውታል ከላይ በተገለጽው መጣጥፍ፡፡ “..no free area…” የተባለው ሐሳብ እጅግ የተጋነንና ከእውነታው ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ገለጻ ነው።
ታታሻም ቀጣዩ ትንቅንቅ በሚለው መጽሐፉ “ባህልና እሴት ለመንከባከብ ሃይማኖት ስጋት ወይስ ዕድል” ብሎ ባቀረበው ሐሳብ ላይ ተመሳሳይ ትችቶችን ሰንዝሯል፡፡ ሰሞኑ ደግሞ ታምራት ጨንፋ ለዚሁ የኮንሶ ባህል መሸርሸር ተጠያቂ ያደረገው ቤተ ክርስቲያኗን ነው።
በተለይ ታምራት ሰሞኑን እያነሳቸው ባሉ ነጥቦች ላይ ቀጥታ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት ነገሩን ከሥረ መሠረቱ መፈተሹ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
መጀመሪያ “ባህል ጠፋ” ስንል ምን ማለታችን ነው? ይንን ለመረዳት ባህል የሚለው ቃል ትርጉሙን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃለት ባህል የሚለውን ቃል የሚፈታው፦
“ሀሪሶት፣ የሕብረተሰብ አነጋገር፣ ልማድ፣ እምነት፣ ጠባይ፣ ግበረገብ፣ ዘዴ፣ ህግ፣ ወግ፣ ብሂል፣ ትውፊት፣ ሥነ ቃል፣ ሥርዓት…. “[1] ብሎ ነው፡፡
እንግዲህ መዝገበ ቃላቱ የተወሰኑትን ለመዘርዘር እንጂ ሙሉ ዘርዝሮ አልጨረሰም፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ሃይማኖቱ ያጠፋቸው የትኞቹን ነው? ለምሳሌ የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ክፍል ኡዋ ወይም ኮንፋን አይለብስም? ዳማ አይበላም? በበሬ አያርስም? ካብ አይክብም? ሠርግ አይሰርግም? ለቅሶ ቤት አይደርስም? ኮንሰኛ አያወራም? ተረት አይተርትም? እነዚህ ነገሮች ባህል አይደሉም?፣ ይህንን የምትከለክል ቤተ ክርስቲያን የለችም፡፡ የእንግሊዝኛ መዝሙሮችን ወደ ኮንሰኛ ቋንቋ መቀየር ባህልን ማሳደግ ነው ወይስ ማጥፋት? መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኮንኛ መቀየርስ ከባህል ጋር እንዴት ይታያል? ከጥንቆላ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቊሶች ስለማይጠቀሙ፣ ድርብ ጋብቻን ስለሚያስቀሩ፣ የአምልኮት መልክ ያላቸውን ባህላዊ ሥርዓቶች ላይ ስለማይሳተፉ ባህልን ያወድማሉ ተብለው የሚከስሱ ከሆነ ክሱ አግባብ አይደለም፡፡
አሁን ወደ ታምራት ሐሳብ ልምጣ፡
በመጀመሪያ ሐሳቡን ከሥነ-ሙግት (Logic) አንጻር እንፈትሽ፡
ታምራት አቶ ካርሞ ቂሣ ምስክርነት ጋር በተያያዘ ያነሣው ሐሳብ ነው። “ከሰይጣን ኃይል ነጻ ልትወጣ ትችላለህ ግን ማድረግ የሚያስፈልግህ አንድ ነገር አለ፡፡ ለሰይጣን በመገበር በዘመንህ ሁሉ የሰይጣን ባሪያ እንዳትሆን የእርሱን ዕቃ በሙሉ ከቤትህ ማውጣት ያስፈልግሃል” የተባለውን ምስክርነት እንደ መነሻ አድርጎ የሚሺነሪዎች ሥራ “ጸረ-ባህል” ብሎ ፈርጇል።
“ስለዝህ በግዘው ሰይጣን የሚገለገልባቸው ቁሳቁሶች የተባሉት 100% ሙሉ በሙሉ የኮንሶ ባህላዊ ቁሳቁሶች፣አልባሳት እና ገጣገጦች እንደሆኑ ግልፅ ነው። ስለዝህ ፊሊክስ ኡላቭሶን የመጀመሪያው ሚስዮናዊ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ፀሬ ኮንሶ ባህል ክርስቲና ያስፋፉ ግለሰብ ናቸው ብል ማጋነን ሳይሆን እውነት ነው።
የዚህ ሐሳብ ትልቁ ችግር ጥቅል ፈረጃ ነው። ቁንጽል ድርጊትን ዋቢ ጠርቶ ትልቅ ድሚዳሜ ላይ መድረስ ነው። የዚህ ሙግት ሕጸጽ በሥነ-አምክንዮ ሕግ Hasty Generalization ይባላል። የሙግቱ አወቃቀር እንደዚህ ይመስላል።
ካፍትሌ መላጣ ነው፣
ካፍትሌ የኮንሶ ልጅ ነው፣
ስለዚህ ኮንሶዎች መላጣዎች ናቸው።
በቂ ናሙና ሳይወስዱ በአንድ ወይም በጥቂት ናሙና መላውን ሕዝብ መፈረጅ ስህተት ነው። የታሜም ስህተት ይኸው ነው።
ካርሞ ቂሣ የሰይጣን ዕቃዎችን አቃጠለ፣
ሰይጣኑ የተገለገለባቸው ዕቃዎች የኮንሶ ባህላዊ ቁሳቊሶች ናቸ፣
ስለዚህ ካርሞ የኮንሶን ባህል አቃጠለ፡
ባህል በጣም ሰፊ ነገሮችን ስለምያጠቃልል፣ በነዚህ ተቃጠሉ በተባሉ ዕቃዎች ሊመዘን አይችልም። “Culture refers to the cumulative deposit of knowledge, experience, beliefs, values, attitudes, meanings, hierarchies, religion, notions of time, roles, spatial relations, concepts of the universe, and material objects and possessions acquired by a group of people in the course of generations through individual and group striving[2]”
ታዲያ ይኸ ሁሉ ነገር በአንድ ድርጊት ጠፋ ብሎ መደምደም ድፍረት አይሆንም?
አሁን ደግሞ በምስክርነቱ ላይ ስለቀረበው ሐሳብ ተገቢነት ላይ እንወያይ።
ሰውዬው አቃጠለ የተባልው ዕቃ ምን ዓነንት ቢሆን ነው? ብዙውን ጊዜ ከሰይጣን የሚሰጡ ትዕዛዞች እኔም በተወሰነ መልኲ ስለማውቃቸው ለባህላዊ ቅርስነት የሚበቁ ናቸው ብሎ መደምደም እጅግ አስቸጋሪ ነው። በትንሽ ጨርቅ የተጠቀለለ ነገር፣ ወይ የሞተ ነገር መቅበር፣ ወይም ጥቃቅን የሆኑ ዕቃዎችን ምስጢራዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ መደበቅ ሊሆን ይችላል። አልፎ አልፎ እንደ ዛፍ፣ ድንጋይ ወይም ከተፈጥሮ ነገሮች አንዱን ላይ መሰዋዕት ማድረግ ነው። ታዲያ እነዚህ ቊሶች ባይቃጠሉ እንኳን በጊዜ ሂደት መጥፋታቸው የሚቀር አይሆንም።
ግን ለምን ተቃጠሉ? መቃጠላቸው ስህተት ነው? ታምራትም እንዳለው ሰይጣን ሰው ውስጥ እንጂ ዕቃ ውስጥ ስለማይኖር ሰይጣኑን አባርሮ ዕቃውን መጠቀም አይቻልም?
ክፍል ፪ን ያንብቡ!
[1] ሃብሩ ዘርጋው፣ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ (2010) አዲስ አበባ
[2] https://people.tamu.edu/~i-choudhury/culture.html