Animal Farm
እንግሊጣራዊ የልቦለድ ደራሲ፣ ፖለቲከኛና ጋዜጤኛ ጆርጅ ኦርዌል የተባለ ታዋቂ ደራሲ በ1940ዎች ዓ.ም አካባቢ Animal Farm የተሰኘ አሊጎሪያዊ ልቦለድ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር፡፡ ጆነስ የተባለ ሰው የሚያረቧቸው የተለያዩ እንስሳት መካከል Old Major የሚባል አንዱ የሽማግሌ እንስሳ የሆነ ሕልም እንዳየ ሌሎች እንስሳትን ሰብስቦ ያወጋቸዋል፡፡ ያየው ሕልም አስጨናቂ የሰው ልጅ አገዛዝ የተወገደበትና እንስሳት በሙሉ በነፃነት የፈለጉትን የሚያደርጉበት ዘመን እንደሚመጣ የሚያሳይ ትንቢታዊ ህልም ነበር፡፡ Old Major ህልም ብቻ ሳይሆን የእስሳቱን ወኔ የሚያነሳሳ የነፃነት መዝሙርን አለማመዳቸው፡፡
Beasts of England, beasts of Ireland,
Beasts of every land and clime,
Hearken to my joyful tidings
Of the golden future time.
Soon or late the day is coming,
Tyrant man shall be o’erhrown
And the fruitful fields of England
Shall be trod by beasts alone.
…..
በጆነስ አገዛዝ የተማረሩ እንስሳት በቅርብ ወይም በሩቅ፣ ብቻ አንድ ቀን፣ ሰው የተባለ አስጨናቂ ገዢ ከምድርቱ ተወግዶ እንስሳት ብቻ በነፃነት የሚኖሩበት ዘመን እንደሚመጣ በብርቱ ይናፍቁ ጀመር፡፡ የእንስሳቱ ቅሬታ ከልክ በላይ እንለፋለን፣ የልፋታችን ዋጋ ግን ባግባቡ አንበላም የሚል ነው፡፡ “ጓዶች” አለ Old Major የተባለው ሽማግሌ እንስሳ፡፡ “ጓዶች፣ የዚህ ሕይወት ትርጉሙ ምነድን ነው? እናስብ እስቲ፣ ኑሮአችን ትርጉም አልባ፣ አድካሚና አጭር ነው፡፡ የሚሰጠን ምግብ ሕይወታችንን ብቻ ለማቆየት የሚረዳን ነው፣ ከኛ መካከል አቅም ያላቸው ሁሉ እስከ መጨረሻ እስትንፋሳቸው ድረስ እንዲሠሩ ይገደዳሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት ሲያቅተን በቅጽበት ያለ ርህራሄ እንታረዳለን፣ በእንግሊጣር ምድር ያለ ማንኛውም እንስሳ ደስታና እረፍት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቅም፡፡ በእንግሊጣር ምድር ነፃ የሆነ እንስሳ የለም፡፡ የእንስሳት ኑሮ ትርጉም የለሽና ባርነት ነው፣ ሐቁ ይኸው ነው” (ገጽ10-11)፡፡
Old Major ይህንን ህልም ካጫወታቸው በኋላ ወዲያውኑ ሞተ፡፡
አንድ ቀን አቶ ጆነስ ሰክሮ እንስሳቱን ሳይመግብ ተኛ፡፡ ይህንን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አብዮት አስነሱ፡፡ ቀንድ ያለው በቀንዱ፣ መራገጥ የሚችል በእግሮቹ፣ የሚናከስ በጥርሶቹ፣ የሚቧጭሩ በጥፍራቸው… እያንዳንዱ በሚችለው አቅም ሁሉ ተረባርበው ገዢያቸውን አባረሩ፡፡ ከዚያን ነፃ የሆነች የእንስሳት ዓለም አወጁ፣ ከዚያ በፊት Manor Farm ብሎ የሚጠራውን የእንስሳት ማረቢያ ቦታ Animal Farm ብለው ሰየሙ፡፡ በመጨረሻም ሁሉም እንስሳት የሚተዳደሩበት ሰባት ትዕዛዛት(ሕግጋት) አወጡ፡፡ ሥርዓቱ animalism ይባላል፡፡
የ animalism ሕግጋት እነዚህ ናቸው፡፡
1. በሁለት እግሮች የሚሄድ ማንኛውም ነገር ጠላት ነው
2. በአራት እግሮች የሚሄድ ወይም ክንፍ ያለው ሁሉ ወዳጅ ነው
3. ልብስ አትልበስ
4. በአልጋ ላይ አትተኛ
5. አልኮል አትጠጣ
6. ማንኛውም እንስሳ ሌላኛውን እስሳ መግደል የለበትም(አትግደል)
7. ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፡፡
በመፈንቀለ ጆነስ ጊዜ አብዮቱን የመሩ ሁለት እንስሳት(አሳማዎች) አሁን የእንስሳቱን ማህበረሰብ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያዎች ወራት Old Major ያየውን ነፃ የአራዊት ዓለም ያገኙ መሰላቸው፡፡ ሁሉም እንስሳ ነፃ ነው፡፡ ከልክ በላይ መልፋት የለም፣ የሚበሉትም እያንዳንዱ እንደየአቅሙ የሚደርሰውን ነው፡፡ ማንኛውም እንስሳ ተፈጥሮ በሚፈቅደው መሠረት ይሠራል፣ ከዚያን ያርፋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየእሁድ እየተገናኙ ስለ ቀጣይ ሕይወታቸው ይወያያሉ፡፡
ከቆይታ በኋላ የድሮ ባለቤታቸው አቶ ጆነስና ጓደኞቹ አቅም አደራጅተው እንደገና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ሊመልሱአቸው መጡ፡፡ በዚያን ጊዜ ስኖውቦል በተሰኘ መሪያቸው ጥበብ በነ ጆነስ ላይ በከፈቱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ድል ተቀዳጁ፡፡ ጦርነቱን የ battle of Cowshed ጦርነት ብለው ሰየሙ፡፡
ከድል በኋላ ስኖውቦል የተሰኘ መሪያቸው የእንስሳትን የጉልበት ሥራ የሚቀንስና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭላቸውን windmill የተሰኘ ፕሮጀክት ቀየሰላቸው፡፡ ሆኖም ግን በጦርነቱ ዘመን አብሮት ሲመራ የመነበረው ናፖሊዮን የተሰኘ ሌላኛው እንስሳ በብርቱ ይቃወመው ጀመር፡፡ ስኖውቦል የሚያቅርባቸውን እያንዳንዱን ሐሳብ ይቃወማል፡፡ በተለይ windmill ፕሮጀክት ምክንያት ስኖውቦልን አምርሮ ይቃወመው ነበር፡፡ በመጨረሻ የ windmill ፕሮጀክት መሠራት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን በስኖቦልና በናፖሊዮን መካከል በተፈጠረው የተካረረ ክርክር ላይ የእንስሳት ማህበረሰብ ድምጽ እንዲሰጡ ተሰበሰቡ፡፡ ስኖውቦል ቆሞ የ windmill ፕሮጀክት አስፈላጊነት ለእንስሳቱ ለማውራት እንደጀመረ ከየት መጡ ሳይባል አስፈሪ ውሾች እየከነፉ መጡና ስኖውቦል ላይ ተረባረቡ፣ ስኖውቦልም ሽሽት ጀመረ፡፡ ባልጠበቀው መንገድ ስኖውቦል ከእንስሳት ሰፈር በአስፈሪ ውሾች ተባርሮ ዳግም ላይገኝ ጠፋ፡፡ ውሾቹ ናፖሊዮን በስውር ያሳደጋቸው ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ለእያንዳንዱ ጥፋት ስኖውቦልን ተወቃሽ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ስህተት ሲፈጠር ስኖውቦል በስውር መጥቶ እንዳደረገ ናፖሊዮን ያስወራል፡፡ የችግሮቻቸው ምክንያት ተባርሮ የጠፋው ስኖውቦል ተወቃሽ ሆነ፡፡
ከዚያ በኋላ ናፖሊዮን በውሾች እየታጀበ የመሪነቱን ሥፍራ ለብቻ ተቆጣጠረ፡፡ ከዚያ በፊት አምርሮ ሲቃወም የመነበረውን የ windmill ፕሮጀክት እንዲሠራ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ አሳማዎች ከሌሎች እንስሳት የመሪነትን ሚና ስለሚጫወቱ የተለየ ምግብ መመገብ እንዳለባቸው አሳመናቸው፡፡ በተለይ ወተትና አፕል ተለይቶ ለአሳማዎች ብቻ እንዲሰጥ ተወሰነ፡፡ “ለእናንት ደህንነት ብለን ነው ወተትና አፕል የምንበላው እንጂ ወድደን አይደለም” ይላሉ አሳማዎቹ፡፡ አልጋ ላይም መተኛት ምንም ክፋት እንደሌለው በተናጋሪያቸው በ Squealer በኩል አስተላለፈ፡፡ በአጭሩ ሰባት ትዕዛዛት አንድ ባንድ እንደገና እየታረሙ ናፖሊዮንን በሚያስደስት መልክ ተዘጋጁ፡፡ ናፖሊዮን አልጋ ላይ እንዲተኛ ለማድረግ ትዕዛዙ “አልጋ ላይ አትተኛ” የሚለው “አልጋ ላይ በልብስ አትተኛ” በሚለው አስተካከሉ፡፡
ባጠቃላይ ትዕዛዞች እንደሚከተለው ተስተካክለዋል፡-
በአራትት እግር የሚሄዱ ጥሩ ናቸው፣ በሁለት እግር የሚሄዱ የበለጠ ጥሩ ናቸው (Four legs good, two legs better), አትግደል የሚለውን “ያለ ምክንያት አትግደል”፣ አልኮል አትጠጣ የሚለውን “ከመጠን በላይ አትጠጣ” ወደሚለው ቀየሩት፡፡ ሁሉም ትዕዛዛት ጠፍተው በመጨረሻ
“ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፣ ነገር ግን አንዳንድ እንስሳት የበለጠ እኩል ናቸው” (All Animals are equal but some animals are more equal than others) የሚለው ትዕዛዝ ብቻ ቀረ፡፡
ታርኩ የሚያልቀው አሳማዎችና ሌሎች ሰዎች በጋራ ተሰብስበው ሲጠጡ የቀሩት በመስኮት እየተመለከቱ የሚሆነው ማመን ሲያቅታቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ልቦለዱ የሩሲያን አብዮትና የሶሻሊዝምን መፈረካከስ የሚያሳይ አሊጎሪ ቢሆንም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታርክ ቁልጭ አድርጎ የሚየሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
• በትግል ጊዜ እንተባበራለን፣ ከድል በኋላ መነካከስ እንጀምራለን፡፡ በተለይ የሥልጣን ጥማት በሚፈጥረው መናቆር እስከ መገዳደል እንደርሳለን፡፡ ደርግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ እነ ሌ/ጄነራል አማን አንዶምና አጥናፉ አባተ የተገደሉበትን ምክንያት ያጤኗል፡፡ በዶር ዓቢይና በለማ መካከል የተፈጠረው ልዩነት…. ወዘተ
• ኢሕአዴግም ሥልጣን ላይ ሲወጣ በስውር የገደላቸው የበረሃ ጓዶች ስንት ናቸው፣ እነ ታምራት ላይኔ ለምን ዘብጢያ ወረዱ?
• ሥልጣን ሲወጡ ሕግ ማውጣት፣ እየቆየ ሲመጣ ያወጡትን ሕግ መጣስ፣ አሊያም እንደ ኢሕአዴግ በሌሎች አዋጆች ሕጉን ሽባ ማድረግ
• ሕዝብም በመሪዎቹ እየተታለለ መኖር
• ግፈኛ ባለሥልጣናትን ለመጣል መረባረብ፣ በወደቁት ግፈኞች ፈንታ የተሻለ ራዕይ ያላቸው መሪዎች ሳይሆን ሌሎች ጉልበተኞች ወደ ሥልጣን እንዲወጡ መፍቀድ
• ለጥፋቶች ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አሊያም ያለፉት ሥርዓቶችን ተጠያቂ ማድረግ
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ይህንን አካሄድ “እንዘጭ! እንቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመጨረሻ ሕግ፡- “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ እኩል ነው፣ ነገር ግን ባለ ሥልጣናትና ዘመዶቻቸው የበለጠ እኩል ናቸው” ወይም “ሕዝብ ከባለሥልጣን በታች ነው፡፡”