በኮንሶ ዞን በሚገኙ የመካነ ኢየሱስና የአካለ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የአንድነትና የሰላም ኮንፍራንስ ተካሄደ

በኮንሶ ዞን በሚገኙ የመካነ ኢየሱስና የአካለ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የአንድነትና የሰላም ኮንፍራንስ ተካሄደ

የሁለቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለ ሰላም ኮንፍራንሱ ንግግር ሲያደርጉ

ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 25 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ነባር ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አካለ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የአንድነትና የሰላም ኮንፍራንስ መካሄዱን ኮንሶ ዜና ያነጋገራቸው የኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ኮንፍራንሱ በሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት ምዕመናን መካከል ተፈጥሮ ለረጅም ጊዜ የቆየውን እርስ በርስ መጠራጠር፣ ጥልና አንድነት ማጣትን ለማስወገድ ያለመ ነው ተብሏል።

የሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት አንድነት ማጣት ብዙ አሥርት አመታትን ያስቆጠረ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በወቅቱ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የኮንሶ ክፍል የሥራ መሪዎች በነበሩና በቤተ ክርስቲያኒቱ የደቡብ ምዕራብ ሲኖዶስ መሪዎች በነበሩ አካላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መነሻነት መሆኑን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይናገራሉ።

አለመግባባቱ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ባለመቻሉ፣ ከወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተከፈሉ መሪዎችና ምዕመናን በግንቦት ወር 1999 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ነባር ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አካለ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን” ማቋቋማቸው ይታወሳል።

ይሁንና በአመታት መካከል በሁለቱም ኅብረቶች ምዕመናን መካከል መንፈሳዊ አንድነትን ለመፍጠር በተለያዩ መንገዶች ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበርና በአንዳንድ የኮንሶ አካባቢዎችም በሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት ምዕመናን መካከል ዕርቀ ሰላም መደረጉን፣ የመረጃ ምንጮቻችን ጨምረው ተናግረዋል።

ከ2011 ዓ.ም ወዲህም ከሁለቱም ወገኖች በጋራ መጸለይና ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸው በሂደት ለተፈጠረው የአንድነት ኮንፍራንስ ትልቅ ሚና መጫወታቸውም ተገልጿል።

የሰላም ኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች

ትላንት በሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖች መካከል ለተደረገው የሰላም ኮንፍራንስ መሳካት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ቤትም ከፍተኛ ሚና መጫወቱን፣ የዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት መረጃ አመልክቷል። ለዚህም ለጽ/ቤት ከሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የምሥጋና የምሥክር ወረቀት መበርከቱም ታውቋል።

በተመሳሳይ፣ ለሰላም ኮንፍራንሱ ስኬት አስተዋጽዎ ላደረጉ የአብያተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮችም የምሥክር ወረቀት መሰጠቱ ተገልጿል። ሁለቱ የእምነት ተቋማት በጋራ ያዘጋጁት የመተዳደሪያ ደንብም ለሰላም ኮንፍራንሱ ታዳሚዎች ከቀረበ በኋላ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በእማኝነት በተገኙበት መፈረሙም፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ዘገባ ያመለክታል።

የሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖች መሪዎች የጋራ መተዳደሪያ ሲፈራረሙ

የሰላም ኮንፍራንሱ በካራት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፣ የደቡብ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ፣ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁና ሌሎችም የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መከናወኑን ተገልጿል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *