
ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የማስረከብና መከላከያ በመቀሌ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ስራ በዚህ ሳምንት እንደሚከናወን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው የፌዴራል መንግሥት የልዑካን ቡድን በመቀሌ የነበረውን ቆይታ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ ማቅረቡን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ በ2ኛው የናይሮቢ የሰላም ስምምነት መሠረት ህወሓት የታጠቃቸው ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግስት የማስረከብ ስራ እስከ ሀሙስ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በመቀሌ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ማብራሪያውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል የተጀመረው አገልግሎት የማቅረብ ሥራ እንዲፋጠን መመሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በመመሪያው መሠረትም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ የሚያደርገውን በረራ በነገው ዕለት እንደሚጀምር እና ኢትዮ ቴሌኮምም በቅርቡ አገልግሎት የሚጀምርበትን ቀን ይፋ እንደሚያደርግም አማካሪው አስታውቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በትናትናው እለት በመቀሌ ቆይታ አድርጎ መመለሱ ይታወሳል።
በቆይታውም ከህወሓት አመራሮች እና ከመቀሌ ከተማ ከተውጣጡ የህብረሰተብ ክፍሎች ጋር በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሀት እና የፌደራል መንግሥቱ መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር አየር መንገዱ መደበኛ በረራውን ያቋረጠው።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው በዚህ ጦርነት የባንክ፣ ቴሌኮሙንኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችም የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌ ገብቶ ከቆየባቸው ጥቂት ወራት በስተቀር ተቋርጠው መቆየታቸው ይታወቃል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት መሰረት ህወሀት እና የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል።
ይሄንን ስምምነት ተከትሎም መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ዳግም በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
ከነዚህ መካከልም አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ሲሆን ከነገ ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ከአዲስ አበባ መቐለ መደበኛ በረራውን እንደሚጀምር አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለትም በአፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግሥት ልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ አምርቶ ከተለያዩ አመራሮች እና የህዝብ ወኪሎች ጋር ተወያይቶ መመለሱ ይታወሳል።
በውይይቱ ወቅትም የባንክ፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮሙንኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡ ተገልጿል።