
ህዳር 26/2015 ዓ.ም የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ተከሳሿን በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ 02/2006 መሰረት በእርከን 39 ስር በማሳረፍ በሞት እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡ በተከሳሽ ላይ የተወሰነው እስኪፈፀም ድረስ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንድትቆይ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ነሃሴ 26 ቀን 2014 ዓ/ም በለሚኩራ ክ/ከ አራብሳ ኮንዶሚኒዬም እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ በምትሰራበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የሁለት ህፃናትን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ አድርጋለች ሲል በከባድ የግድያ ወንጀል እና እንዲሁም ተከሳሽ የሟቾችን የቤተሰብ ሰነድ ማስረጃዎች ማጥፋት ወንጀል ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በህይወት መኮንን ላይ ተደራራቢ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
ተከሳሽ አስቀድማ ለፖሊስ በፖሊስ ጣያ እና በፍርድ ቤት የሰጠችውን የእምነት ቃል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶ ፍርድ በቤት ቀርባ ወንጀሉን ስለመፈጸሟ ስትጠየቅ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” በማለት ብትክድም ወንጀሉን ስለመፈጸሟ ዐቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ለችሎቱ በማስረዳቱ፣ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በክሱ ዝርዝር የተመለከቱትን ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሽ በተከሰሰችባቸው ከባድ የሰው ግድያ እና ሰነድ ማጥፋት ወንጀል እንድትከላከል ብይን ቢሰጥም የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለት የገለፀች በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም የተሰየመው ችሎትም ተከሳሽ ጥፋተኛ መባሏን ተከትሎ የዐቃቤ ህግን የቅጣት አስተያየትና የተከሳሽን የቅጣት ማቅለያ መርምሮ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም ዐቃቤ ህግ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ወንጀሉ ከባድ ደረጃ ተብሎ እንዲሰላለትና በሞት እንድትቀጣ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ በተከሳሽ በኩልም ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈፅሜ የማላውቅ፣ ወንጀሉን የፈጸምኩት ከእውቀት ማነስና ያልተማርኩ በመሆኔ መሆኑ፣ እጄን ለፖሊስ አምኜ የሰጠው በመሆኔ ከግምት ገብቶ ቅጣቱ ይቅለልልኝ በማለት 5 የቅጣት ማቅለያዎችን ከመንግስት በተመደበላት የተከላካይ ጠበቃ አማካኝነት የጠየቀች ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ማቅለያዋን አልተቀበለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ሌሎች አጥፊዎችን ያስጠነቅቃል በማለት ተከሳሿ በሞት እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡