በአምቡላንስ ከባድ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋዉሩ የተያዙ ግለሰቦች በእሥራት ተቀጡ

በአምቡላንስ ከባድ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋዉሩ የተያዙ ግለሰቦች በእሥራት ተቀጡ

በአምቡላንስ ህግ ወጥ የጦር መሣሪያን ሲያዘዋውሩ የተያዙ ግለሰቦች

ለድንገተኛ የህክምና አገልግሎት መዋል የሚገባውን አምቡላንስ ለከባድ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲጠቀሙበት ተገኝተው የተያዙት ወንጀለኞች፣ በእሥራት መቀጣቸውን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍ/ቤትን ጠቅሶ የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ዘግቧል።

ግለሰቦቹ ጥቅም 4 ቀን 2015 ዓ.ም በኅብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ዘይሴ ወዘቃ ላይ ከሌሊቱ 5 ሰዓት ገደማ በወረዳው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል። በወቅቱ ግለሰቦቹ የጦር መሣሪያውን ሲያዘዋውሩ የነበረው፣ መነሻውን ከአሌ ልዩ ወረዳ አድርጎ ወደ አርባምንጭ አቅጣጫ ሲጓዝ በነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ደ. ሕ. 03692 በሆነ ኮድ 4 አምቡላንስ መኪና ነው።

ህግ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ወንጀል የተሠራበት የህዝብ አምቡላንስ

በድንገተኛ ፍተሻው የተያዙት ከባድ የጦር መሣሪያዎች አንድ ባለመነጽር ስናይፐር ጠብመንጃና አንድ ባለመቶ ጥይት ዝናር ብሬይን ጠብመንጃ መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱም ከባድ የጦር መሣሪያዎችና በግለሰብ ደረጃ ለመያዝ የማይፈቀዱ ናቸው።  

በፖሊስ ድንገተኛ ፍተሻ በአምቡላንስ ውስጥ የተያዙት ከባድ የጦር መሣሪያዎች

በወቅቱ የአንቡላንሱን ሾፌር ጨምሮ 5 ግለሰቦችን ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ትላንት ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ላይ የቀረቡ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቶ መከላከያ ጠበቃቸው ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያና አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን የቅጣት ማክበጃ ተመልክቶ ብይን ሰጥቷል።

ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች በፍርድ ቤት

በዚህም መሠረት አቶ አርካሎ አሳ፣ አቶ አይልጋ ኦይታ፣ አቶ አላዴ አርካሎ፣ አቶ ዋጣሴ ጋልጉሳና አቶ ምሥረቾ ማሙሳ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ እያንዳንዳቸው በ6 አመታት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡና ከእሥራት በኋላ ደግሞ በ10 ሺህ ብር ገንዘብም እንዲቀጡ ፍርዱ ቤቱ ወስኗል።

እንደ ጋሞ መንግስት ኮሚዩንኬሽን መሥሪያ ቤት ከሆነ፣ የፍርዱ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አድማሱ ዘገየ ስለወንጀሉ በሰጡት አስተያየት፣ “ወንጀሉ ማህበረሰቡን ለማገልገል የተሰጠን የህዝብ አምቡላንስን በመጠቀም የተከናወነና የህዝብንና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ጨምረውም፣ “ማህበረሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት፣ ለጸጥታ አካላት በመጠቆም ሰላም ወዳድነቱን ሊያረጋግጥና ደህንነቱን ሊያስጠብቅ ይገባል” ብለዋል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *