
በኮንሶ ዞን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እየተከሰተ ያለውና እስከ አሁንም መፍትሔ ያልተበጀለት የመብራት መቆራረጥና የኃይል መዋዠቅ በባንኮች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉን የካራት ከተማ ከንቲባ አቶ ፍሬዘር ኮርባይዶ ለኮንሶ ዜና በሰጡት መረጃ አስታወቁ።
በኮንሶ ዞን የሚገኙ ሁሉም ባንኮች ከመብራት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ለጀነሬተር የሚያወጡት የነዳጅ ወጪና በኃይል መዋዠቅ ምክንያት የተቃጠሉ ኮሚፕዩተሮችና ሌሎች የሥራ መሣሪዎች ዝርዝርና የደረሰው ኪሳራ የገንዘብ ተመን ከባንኮቹ ለጽ/ቤታቸው በደረሰው መሠረት ከፍተኛ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።
ከንቲባው ወደ ኃላፊነት በመጡበት ወቅት የመብራቱን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ መብራት ኃይል አርባምንጭ ዲስትሪክት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንና በዚያን ጊዜ በኮንሶ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የኃይል መቆራረጥ መንስኤው፣ መሥርመሩ ከከንባ መሥመር ጋር በአንድነት መሆኑ ያስከተለው የኃይል ሥርጭት ችግር እንደሆነ እንደተገለጸላቸው አስታውሰዋል።
በዚያን ጊዜ ከዲስትሪቱ ጋር በነበራቸው ውይይት በቅርቡ የኮንሶን መሥመር ከከንባው በመለየት ለብቻው ማድረግ እንደመፍትሔ እንደታሰበ ተስፋ እንደተገባላቸውም ተናግረዋል። “ይሁንና እስከ አሁንም ድረስ መፍትሔ ባለማግኘቱ የኮንሶ የመብራት ችግር እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በመብራት መቆራረጥና ኃይል መዋዠቅ ከፍተኛ ኪሣራ እያስተናገዱ ካሉ ባንኮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካራት ቅርጫፍ፣ ለመብራት ኃይል አርባምንጭ ዲስትሪክት ቅርጫፍ ጽ/ቤት ጥቅም 21፣ 2015 ዓ.ም በጻፌው ደብዳቤ ቅሬታውን መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካራት ቅርጫፍ በኩል የቀረበው የቅሬታ ደብዳቤ፣ በመብራት ኃይል አርባምንጭ ዲስትሪክት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።የኢትዮጵያ መብራት ኃይል አርባምንጭ ዲስትሪክት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጥቅምት 28፣ 2015 በጻፈው ደብዳቤ የቀረበውን ቅሬታ፣ “የስም ማጥፋት ዘመጃ ነውና በአስቸኳይ መቆም አለበት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካራት ቅርጫፍም በአስቸኳይ ይቅርታ መጠየቅ አለበት” ብሏል።
አቶ ገረመው ወንድምሁነኝ በተባሉ የዲስትሪክት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ስም የወጣው ደብዳቤ ብዙ ስድብ መሰል ቃላቶች የታጨቁበትች ደብዳቤ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ መናገገሪያ ሆኗል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደብዳቤውን፣ “ከአንድ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ለሌላ የመንግሥት መሥሪያት ሊጻፍ የማይገባና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚጓድለው፣ ከአንድ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሊወጣ የማይገባ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።