ክፍል ፪
ላቲን ወይስ ግእዝ
ሁለተኛ የመከራከሪያ ነጥብ ኮንሰኛ የሚጻፍበት ፊደል ነው። ላቲን መመረጡ ቅር የተሰኙ እንዳሉ ሁሉ ትክክል ነው የሚሉም አሉ።
በመጀመሪያ መገንዘብ የሚያስፈልገው ዛሬ አማርኛ የሚጻፍበት ፊደል በአብዛኛው ከግእዝ ፊደላት የተወረሱ ናቸው። አማርኛ አብዛኛውን ፊደል ከግእዝ ሲወርስ የራሱ የተወሰኑ ፊደላትን ጨምሮበታል። አማርኛ የጨመራቸው ፊደላት፥- ሸ፣ ቸ፣ ኘ፣ ኸ፣ ዥ፣ ጀ፣ ጨ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከጊዜ በኋላ የተጨመሩ ዲቃላ ሆሄያት የሚባሉም አሉ። ከዚህ የምንረዳው የግእዝ ፊደላት አማርኛንም ጭምር ሙሉ በሙሉ ሊጠቅም እንዳልቻለ ነው፣ ሆኖም ግን አዳዲስ ፊደሎችን በመፍጠር ችግሩን ቀርፈዋል። እንደ ‘ቨ” ያሉ ፊደሎች ደግሞ ከኋላ የተፈጠሩ ናቸው፣ በተለይ ከውጪ የመጡ አንዳንድ ቃላትን ለመወከል።
የኮንሰኛ መጻፊያ “ላቲን” በመሆኑ ቅር ከተሰኙት ጎራ እመደባለሁ። ቅር የተሰኘሁት ዛሬ አይደለም፣ ያኔ ገና ውይይት በሚደረግበት ጊዜ በቋንቋው ላይ ውይይት ያደረጒ ወንድሞች ከሳባ ፊደል ይልቅ ላቲን መምረጣቸውን ለኛ ሲያበስሩ ቅሬታ ፈጥሮብኛል። ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብሎ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ያደረገችውን አስተዋጽዖ ስለማውቅ ነው። እኔም በአጋጣሚ በግእዝ ፊደል የተጻፉ ብዙ የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶችን ማለትም የመዝሙር ደብተሮች፣ ታሪኮችና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም የማንበብ ዕድሉን ስላገኘሁ ነው። ኮንሰኛውን ያስተማረኝ ልጅ ደግሞ ያልተማረ ልጅ ነበር። እንደሱ ያልተማሩ ብዙ የኮንሶ ልጆች ቤተ ክርስቲያን በፈጠረችው ጥሩ አጋጣሚ ያለማወቅ ጭጋጋቸውን ገፍፈው ከዕውቀት ብርሃን ለመቋደስ በቅተዋል። አንደኛ ክፍል ያልገቡ ግና የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስን አቀላጥፈው የሚያነቡ ብዙ የኮንሶ ልጆች እንዳሉ እኔ ራሴ ዐውቃለሁ። የግእዝ ፊደል ቀርቶ የላቲን ሲመረጥ ታዲያ መደንገጤ አልቀረም፣ ምክንያቱም ያ ሁሉ ልፋት ከንቱ የሚያደርግና እንደገና ከዜሮ ስለሚያስጀምር ነው።

ከግእዝ ወደ ላቲን የተደረገው ሽሽት ተገቢ ነው?
ለመሆኑ የኮንሰኛ ቋንቋ መጻፊያ ላቲን መሆኑ ተገቢ ነው? በፍጹም! ይኸንን የምለው ዝም ብዬ ከራሴ ሐሳብ ተነስቼ ሳይሆን የታሪክ መዛግብትን አገላብጬ ያገኘሁት ነው።
እስካሁን የቀረቡ መከራከሪያ (ዎች) በፍጹም የሚያሳምን (ኑ) ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡ ራሱ መስተካከል ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ። እስካሁን እንደ መከራከሪያ የቀረበው ሐሳብ “ኮንሰኛ የኲሽ ቋንቋ በመሆኑ ጠብቆና ላልቶ የሚነበቡ ቃላት ይበዙታል፣ የግእዝ ፊደላት ያንን በአግባቡ መወከል አይችሉም” የሚል ነው። በተቃራኒው “ሥራውን ቀላል የሚያደርግ የላቲን ፊደል ስላለ ለምን እንለፋለን” የሚል ነው። ይኸ ነው እንግዲህ ምክንያቱ፣ ስንፍና ነው! ለመሆኑ አውሮፓ ውስጥ ስንቱ ቋንቋ ነው ያለው? ላቲን እኮ የሮማውያን ቋንቋ ብቻ ነበር። እንዴት ሆኖ ለአውሮፓ ቋንቋዎች ሁሉ ሊሆን ቻለ? እንምንገነዘበው የአሮፓ ቋንቋዎች ላቲንን ተጠቅመው ሲያበቊ ወደ ራሳቸው ድምጾ ለመቀየርም ፊደላቱ ላይ ቅንድ፣ ጭራ፣ ጆር እየጨመሩ ተጠቀሙበት እንጂ ድንበር ተሻግረው ሌላ ፊደል ለመውሰድ አልሄዱም።
ኮንሰኛ በግእዝ ፊደላት መጻፍ ገና “ሀ” ተብሎ የሚጀመር ፕሮጀክት በመሆኑ ችግር መኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው። እኔ ራሴ የማውቀ አንድ ችግር አለ፣ ለምሳሌ Dama (ኲርኲፋ) እና Damma (ዱቄት) ተመሳሳይ አጻጻፍ ስልት አላቸው። ችግሩን ለመፍታት ግን ሙከራ ተድርጓል። የመጀማሪያው ቃል ፈጠን ያለ ጽምጽ ያለው (ጠብቆ የሚነበብ) በመሆኑ በግእዝ ፊደል “ደመ” ተብሎ ይጻፋል። ሁለተኛው (ዱቄት የሚገልጸው) ረጅም ድምጽ ያስከተለው “ዳ” የሚለው ፊደል ስለሆነ በራብዕ “ዳመ” ተብሎ ይጻፋል። ሌሎች ምሳሌዎችን ማየት ይቻላል።
- ማነ (ምንድን ነው?)፥- “ማ” ረጅም ድምጽ
- መነ (ቤት)፥- “መ” ጠብቆ ወይም ፈጣን ድጽም
ሌላው አየርን ወደ ውስጥ ወይም ወደ ውጪ በመሳብ በጒሮሮ ውስጥ የሚፈጠር ድምጽ ለምሳል “ኾንሶ፣ ኾርማ፣ ኾታ…” ወዘተ ውስጥ ያለው የመጀመሪያ ፊደል በአማርኛ ውስጥ አለመኖሩ ነው። በጣም የሚገርመው ይህ ድምጽ ሰሜቲክ በሆነው አማርኛ ውስጥ ባይኖርም በትግረኛ፣ ዐረቢኛና እብራይስጥኛ የመሳሰሉ ሰሜቲክ ቋንቋዎች ውስጥ አለ። ስለዚህ አንዳንዴ ሰሜቲክና ኲሼቲክ መካከል የጥቊርና የነጭ ያህል ግልጽ ድንበር አለመኖሩንም ያሳያል። የኮንሰኛ ቋንቋ በግእዝ ለመጻፍ የሞከሩ ሰዎች ግን በአማርኛ ሲጠራ የ ሀ ድምጽ ያለውን ኸ ተጠቅመው ችግሩን ፈተውታል። ኦሮሚኛ ግን ለዚህ ብሎ ወደ ላቲን ሄዷል።
በዚህ መሠረት ችግሮቹን ለመቅረፍ ሙከራ ተድርጐ ነበር። በዚህ ላይ የመንግሥት እገዛ ቢታከልበት ኑሮ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠር ነበር። ቤተ ክርስቲያን በአቅሟ የሞከረች ሙከራው በቂ ነው ወይስ አይደለም፣ ሌላ ጒዳይ ነው። አማርኛ ራሱ ፊደሉን ከግእዝ ሲዋስ ሙሉ በሙሉ ተስማምቶት አይደለም፣ ስለዚህ ተጨማሪ ፊደሎችን መፍጠር አስፈልጎታል።
ሌሎች ችግሮችም በተመሳሳይ መንገድ ለመቅረፍ መሞከር ይቻል ነበር። የትኛውም ቋንቋ መቶ በመቶ ድምጾቻቸውን በጽሑፍ ይወክላሉ፣ ወይም በንግግርና በጽሑፍ መካከል ምንም ክፍተት የላቸውም ማለት አይቻልም። በጣም አድጓል የሚባለው እንግሊዝኛ ራሱ ብዙ ጠማማ ባህሪያትን ይከተላል።
ለምን ላቲን?
ሁለት ምክንያቶች ይታዩኛል።
1ኛ ኲሸቲክ ቋንቋ ከግእዝ ይልቅ በላቲን ይቀላል የሚል አስተሳሰብ።
2ኛ ፖለቲካዊ ጫና
1ኛ፡ ላቲን ቀላል ነው!
ኮንሰኛን በግእዝ ከመጻፍ ይልቅ በላቲን መጻፍ ቀላል ነው የሚል መከራከሪያ ነው። ይህ አስተሳሰብ በቋንቋ ብቻ የሚገደብ አይደለም፣ አጠቃላይ ለዘመናት የተጣባን ማኅበረሰባዊ ሥነ-ልቦናችን ይመስለኛል። ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ብዙ ማሳያዎችን ለማምጣት እሞክራለሁ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጪ እንዳይገቡ ካገዳቸ ምርቶች መካከል ውሃ እንዳለበት ተሰምቷል። ይህ በጣም ገራሚ ነገር ነው። የውሃ ገንዳ የተባለች አገር ውሃ ከውጪ በብዙ ዶላር import ታደርጋለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረቱ ምርጥ ምርቶች ይልቅ የቻይና ስልባጅ ይበልጥብናል። ገጣሚ መሮን ጌትነት ባንድ ወቅት ላይ ‘ሀገሬ’ በሚለው ግጥሟ፥-
ዕድሜህን ቀርጥፈህ ብቶን ባለ ድግሪ
ማስትሬት ዶክትሬት ብትደክም ብትለፋ
እውነቱን ልንገርህ በሃገሬ ሒሳብ
ከውጪ የመጣ የሶስት ወር ኮርስ ነው ሚዛኑን ሚደፋ።
የሚል ስንኞችን ቋጥራ ነበር። መሮን በግጥሟ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ውስጥ ካለው ይልቅ የውጪውን እንደሚያመልክ ትዝብቷን ገልጸዋለች።
በቀላሉ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶች እንኳን ሳይቀሩ ከውጪ import የማድረግ ልምድ አዳብረናል። ምክንያቱም ብዙ ልፋት አይጠይቅምና። ምን አለፋን! ምን የመሰለ መሬት ይዘን ስንዴን ከውጪ እናስገባለን፣ በከብት ብዛት ከአፍሪካ 1ኛ ሆነን ሰው ሠራሽ ወተት ከውጪ እናስገባለን።
አንድ ቀን በቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ የሰማሁት ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ልብስ ማምረት ላይ የተሰማሩ ወገኖች ያቀረቡት አቤቱታ ነው። በከፍተኛ ጥራትና ልፋት በአቅማቸው ያመረቱት ምርት ሰው ስለማይገዛቸው ወይም ዋጋውን ስለሚያወርድባቸው ከውጪ ነው የመጣው ብለው እንደሚዋሹ ምስክርነታቸውን ስምቻለሁ። የውስጥ ነው ሲባል የናቊት ምርት የውጪ ነው ሲባል ግን ያለ ምንም ማቅማማት ይገዛሉ።
ይህ ጉዳይ ኮንሶ ውስጥም ያለ ይመስለኛል። ለምሳሌ በሽመና ሥራ ላይ የተሰማሩ ዛሬ ኮንሶ ውስጥ አሉ? ለምን ጠፉ ብሎ የጠየቀ አለ? ምክንያቱም ከኬኒያ የሚመጣውን ስልባጅ መቋቋም አይችሉምና ነው፣ የኛ ትብብር ይፈልጋሉ። የሴቶች ልብስም ከኮንሶ ባህላዊ አለባበስ ወደ እስፔፓ የተቀየረው “ለማጠብ ቀላል ስለሆነ” ነው በሚል ነው። ኮንሶ ውስጥ የሚመረተ “ኮንሶ ወይም ኮንሲያ” የተባሉ ሳሙናዎች ከኬኒያ ከሚገባው ጋር ከፍተኛ ውድድር ውስጥ ነው። በራሳችን ምርት የማንኮራና የማንጠቀማቸው ከሆነ አደጋ ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም። የራስ የሆነውን ምርት እያሻሻሉና እያሳደጒ ከመሄድ ይልቅ ከውጪ ጣጣውን ጨርሶ የመጣውን የምንመርጥ ከሆነ ለውጥ አይኖርም።
በፊደል መረጣ ወቅትም የተፈጠረው ይኸው ነው። የሳባ (ግእዝ) አስቸጋሪ ስለሆነ ከውጪ import እናደርግ የሚል መከራከሪያ ሚዛን ደፍቷል። ይህ የስንፍና ምልክት ነው።
2ኛ፥ ፖለቲካዊ ጫና
እነዚህ ነጥቦችን አገናኝተን ሙሉውን ሥዕል ማየት ከቻልን በቋንቋ ላይ ያጠላውን የፖለቲካ ጥላ መገንዘብ እንችላለን።
- የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው?
- ባንድራ ጨርቅ ነው
- የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ታሪክ ነው
- የግዕዝ ፊደላት ለሰሜቲክ ቋንቋ ብቻ የሚመች ነው።
እነዚህ ሐሳቦች ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ የተቀነቀኑ ሐሳቦች ናቸው። የዚህ ዋና ዓላማ እንደ አገር የሚያስተሳስረን የጋራ ማንነቶች እንዳይኖሩን እና በትናንሽ ብሔሮች ተክፋፍለን እንድንባላ የተደረገ የ “ከፋፍለህ ግዛ” ዘዴ ነው። የአክሱም ሥልጣኔ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ብቻ የሚመለከት እንጂ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሀብት እንዳልሆነ ሰብከውናል። ኢትዮጵያውያን ከባንድራ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለመበጠስ ጨርቅ ነው አሉን። ታሪክም (ያው ሁላንንም የማይወክል ነው በማለት) ከ3ሺህ ወደ 100 ዓመት አቀነጨሩት። በቋንቋ ላይ የደረሰውም ተመሳሳይ ነው። “አማርኛ የገዥ መድብ ቋንቋ” በማለት ሰዎች በጥላቻ እንድመለከቱት አድርገዋል።
ይህ በታሪክ ውስጥ የተፈጠረ ስህተት ነው። በተለይ የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች ይህንን ሐሳብ በደንብ አንጸባርቀዋል።
የኦሮሚኛ ፈለግ
እዚህ ጋር ለምን ኦሮሚኛን እንደ ምሣሌ እንደምጠቀም ግልጽ ማድረግ ይኖርብኛል። አንደኛ እኛ አሁን እየወሰድን ያለነው እርምጃ (በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር/ማስተማር) ከኛ ቀድመው ስለጀመሩና ውጤቱም ስለታየ ነው። የመጻፊያ ፊደልን በተመለከተ ከኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አካሄድም ስለነበረ ነው፣ ነገሩን በደንብ ላብራራ።
በመጀመሪያ ደረጃ ኦሮሚኛና አፋ ኾንስ በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ስለሚመደቡ ብዙ ተመሳሳይ ባህሪያትን ይጋራሉ። የኮንሰኛ ፊደል ከግእዝ ወደ ላቲን ሲቀየር የኦሮሚኛን ፈለግ የተከተለ ይመስለኛል። ምናልባትም በኔ ግምት ከግእዝ ይልቅ ላቲንን በመምረጥ ኦሮሚኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ይመስለኛል፣ ለብዙ የብሔርሰብ ቋንቋቆች እንደ ምሳሌ እንዲወሰድ ሆኗል። ስለዚህ ኦሮሚኛ ለምን ወደ ላቲን እንደሄደ የተወሰነ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል።
ግና ኦሮሚኛ ለምን ላቲንን መረጠ?
የላቲንና የግእዝ ፊደላት ፊልሚያ የተጀመረው በኢሕአዴግ ዘመን አይደለም። ትግሉ ከ1830ዎቹ ጀመሮ ኦሮሚኛ አንዴ በላቲን አንዴ በግእዝ እየተጻፈ እስከ ኢሕአዴ ዘመን ዘልቋል። ሙሉ ታሪኲን እዚህ ጋ መዘርዘር አይመችም፣ ግን ጥቅል ሐሳቡን ማስቀመጥ ይቻላል።
አሮሚኛን በላቲን የሚጽፉና የተለያዩ መዘገበ ቃላትን ሲያዘጋጁ የነበሩት አውሮፓውያን ናቸው። አውሮፓውያን በላቲን የተጻፉ ብዙ የኦሮሚኛ መዝገበ ቃላትና የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶችን ሠርተዋል። ዓላማቸው በኦሮሚያ አካባቢ ወንጌል ለመሥራትና ለጉብኝት እንዲያመቻቸውና ከኅበረተሰቡ ጋር መግባባት እንዲያስችላቸው ነው። አንዳንድ መዘገ ቃላት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ሳይመጡ እዚያ አውሮፓ (በተለይ ጀርመን) ሆነው በባሪነት ወደዚያ ከተጋዙ ልጆች መረጃ በመሰብሰብ የተዘጋጁ ናቸው።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የነበሩ የኦሮሞ ልጆች የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ሲጀምሩ የግእዝን ፊደል ነበር የተጠቀሙት። አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ። ይኸውም የአናሲሞስ ነሲብና የአስተር ጋኖ ሥራዎች። እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ልጆች በኣሮሚያ ውስጥ ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን አናሲሞስ ነሲብ በ1894 ዓ.ም የመጽሐፍ ቊድስ ትርጒምንም ሠርተዋል። ‘መጽሐፍ ቊልቊሎ’ በግእዝ ፊደላት የተጻፍ ትርጒም ነው። እነዚህ ሰዎች ትምህርት ቤት ከፍተው በማስተማር በኦሮሚያ ውስጥ ትልቅ መነቃቃትን መፍጠር ችለዋል። በዚህም በግዕዝ ፊደል የተጻፉ ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አበርክተዋል። በወቅቱ የገጠማቸውን አንዳንድ ችግሮች ለመፍጠር ሲሉ አንዳንዱ ፊደላትንም ፈጥረዋል፣ ለምሳሌ ቀንድ ያለው ደ[ዸ] ። ጥረቱ እስከ ጣሊያን ዳግም ወረራ ድረስ የቀጠለ ሲሆን ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ሲመለሱ ግን ሂደቱ ቆመ።
በኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ የኦሮሞ ምሁራን የተቋረጠው ትምህርት እንዲቀጥልና የኦሮሞ ልጆችም አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋቸው እንዲማሩ ጥያቄ ቢያቀርቡ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም። ትልቊ የቅሬት መሠረት የተጣለው ያኔ ነው። ያኔ ይህ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ “ላቲን ግእዝ” እያልን አንጨቃጨቅም ነበር።
ሌላው ኦሮሚኛ ግእዝን ትቶ ላቲንን እንዲመርጥ ትግል ያደረጒት በተማሪዎች ንቅናቄ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸውና የግራ ዘመም ፖለቲከኞች የነበሩት እነ ኃይለ ፊዳ ናቸው። ያ ዘመን ለዘመናት ሲፈራ የነበረው የብሔር ጥያቄ የተነሣበት ዘመን እንደሆነ ይታወቃል። የብሔር ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ልሂቃን “ኢትዮጵያ የብሔርሰቦች እስር ቤት” እስከ ማለት ደርሰዋል። እነዚህ ምሁራን አማራንና ትግራይን እንደ ጨቋኝ ሲያዩ የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የተጨቆኑ ናቸው ብለው ያምናሉ። እነ ኃይለ ፊዳ ከዚህ ተነስተው ነው የላቲን ፊደል እንደሚሻላቸው አስተያየት ያቀረቡት። መነሻቸው የፖለቲካ ቅሬታ እንጂ ግእዝ ኦሮሚኛን በደንብ አይወክልም ከሚል አይደለም። በተለይ ኦሮሞዎች በ16ኛው ክፍለ ዘመን ነው ከውጪ መጥተው ኢትዮጵያን የወረሩት የሚባለው ትሪክት ለብዙ ኦሮሞ ምሁራን ቅሬትን ፈጥሯል። የባእድነት ስሜት እንዲሰማቸውም አድርጓል።
ሲጠቃለል
ኮንሰኛን በግእዝ መጻፍ ችግር መፈጠሩ የማይካድ ሐቅ ነው። ችግሩ ግን የማይፈታ ችግር አልነበረም። ለመፍታትም ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። ሌሎች በተለይ ኦሮሚኛ ወደ ላቲን የሄደው የፖለቲካ ኲርፊያ የፈጠረው እንጂ የኲሼቲክ ቋንቋ በግእዝ መጻፍ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ስለገጠመው አይደለም። በታሪክ አጋጣሚ በግእዝ የተጻፉ ብዙ የኦሮሚኛ ጽሑፎች ይህንን አረጋግጠዋል።
ኮንሰኛ በላቲን መጻፍ አልነበረበትም፣ ሆኖም ግን አንዴ ሆኗልና አሁን ምንም ማድረግ የማይቻል ይመስለኛል። ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ከላቲን ፊደላት ጎን ለጎን በግእዝ የሚጻፉ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ለብዙ የኮንሶ ተወላጆቹ (በተለይ ለገጠሩ ማኅበረሰብ) የሚሰጠው ፋይዳ ቀላል ባለመሆኑ ችላል ሊባል አይገባም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም በሁለቱም ፊደላት እንደሚታተም የተሰማው ዜና እጅግ በጣም መልካም ነው። ወደ ፊት የአገራችን ፖለቲካ ሲረግብና በራሳችን ነገር መኲራት ስንጀምር ግእዝ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ሁሉ የኲራት ምንጭ እንደሚሆን እምነት አለኝ።
ማጣቀሻዎች
- ሪቻርድ ፓንክረስት፥ የኢትዮጵያ ታሪክ በሪቻርድ ፓንክረስት ዕይታ (አሰናኝ ኤርምያስ ሁሴን)
- ተስፋዬ ሮበሌ (ዶ/ር)፡ ሆህያተ ጥበብ ለጸሓፊያን፣ ለተርጓምያንና ለአርታዕያን
- ኃይለ ኢየሱስ መንግስት፡ የልሳነ ግእዝ መማሪያ
- ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማሪያም ወርቅነህ፡ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት
- ተክለ ጻድቅ መኲርያ፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐጼ ልብነ ድንግል እስከ ዐጼ ቴዎድሮስ
- ፍቅሬ ቶሎሳ፡ (ፕ/ር)፡ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ
https://www.youtube.com/watch?v=yQtl8N1zOo8