
ማሰብን ማሰብ መጀመር አለብን!
አሳብ ብቻውን በቂ አይደለም። አሳቡ የሚመጣበት የአስተሳሰብ መንገዳችን መፈተሽ አለበት። ስለዚህ ከአሳቦቻችን በበለጠ፣ ስለአስተሳሰባችን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በአሳብ ጉዳይ “የትም ፍጪው፣ ዱቄቱን አምጪው” አይሠራም። አሳባችን ብቻ ሳይሆን አሳቡን ያስገኘንበት የአስተሳሰብ መንገድም ሊታሠብበት ይገባልና።
ስለሚያሳስቡን ሁኔታዎች፣ ሰዎች ሁለት ዓይነት ናቸው ይባላል። እነሱም ፕሮአክቲቭ (Proactive) እና ሪአክቲቭ (Reactive)/ግስበታዊ ናቸው። አር ኮቬይ የተባሉ የአመራር ጥበብ ምሁር ስለውጤታማ ሰዎች ልማዶች በጻፉት መጽሐፋቸው እነዚህን ሁለት ዓይነት ሰዎች ቆንጆ አድርገው ይገልጿቸዋል። ፕሮአክቲቭ የሆኑ ሰዎች፣ ምናባቸውን ወይም ዓይነ ልቦናቸውን ተጠቅመው፣ መለወጥ በሚችሏቸው የህይወት ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮርና አስቀድመው በማሰብ ለውጥን የሚፈጥሩ ናቸው። ለውጥ ድንገት የሚመጣባቸው ሳይሆኑ፣ ለውጥን የሚፈጥሩና ለውጥንም አስቀድመው መተንበይና ለሚያስከትላቸው አሉታም ሆነ አዎንታ ውጤቶቹ የሚሰናዱ ናቸው። ለምሳሌ መለወጥ የሚችሏቸውን የግል ጤናቸውን፣ የልጆቻቸውን ሁኔታ፣ የሥራቸውን ሆኔታ፣ የቤተሰባቸውን ወይም የሚኖሩበት ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግሮችን በትኩረት አስበው መፍትሔ የሚያመጡ ናቸው እንጂ በረባው ባልረባው፣ በአሳብ አይብሰለሰሉም፣ አይብከነከኑም።
ሪአክቲቭ የሆኑቱ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በማይቆጣጠሯቸው የህይወት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ፣ በህይወታቸው ላይ አሁናዊና ቀጥተኛ ተጽዕኖ በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ከማተኮራቸው ጋር ተያይዞ ያልተጠባበቁት ሁኔታ በህይወታቸው ውስጥ ሲከሰት፣ በሚሰጡት ያልታሰበበት ስሜታዊ ምላሽ የህይወትን ሚዛን መጠበቅ የማይችሉ ናቸው። ለምሳሌ ከግል ጤንነታቸውና ከቤተሰባቸው ደህንነት ይልቅ የሚያስጨንቃቸው የአየር ንብረት ለውጥ ወይም የአገራቸው ብሔራዊ ዕዳ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ነገሮች በቀጥታ መቆጣጠር ባይችሉም አብዛኛውን የአዕምሯቸውን ጉልበት በነሱ ላይ ይጨርሳሉ። ይህ ደግሞ ከንቱነትና ትክክለኛ ያልሆነ የአስተሳሰብ መንገድ ነው።
ለራሳችንም ሆነ በዙሪያችን ላይ ባሉ ሰዎች ላይ አዎታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን አሳቦች ለማመንጨት ማሰብን እንዴት ማሰብ እንዳለብን አስቀድመን ማሰብ ይኖርብናል። አስተሳሰባችንን ማስተዳደር መቻል አለብን። የመጣልንን አሳብ ሁሉ ሳናብላላውና ጉዳቱና ጥቅሙ ሳንመዝን መዘርገፍ አይገባም። የአስተሳሰብ መንገዳችን መፈ’ተሽ አለበት። በምን ገፊ ኃይል ተነሳስተን እንደምንጽፍ ወይም እንደምንናገር አስቀድመን የማሰብ ዕድሉን ካገኘን፣ አሳቦቻችን የጠሩና የሚገነቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ፕሮአክቲቮች እንጂ ሪአክቲቮች ልንሆን አይገባም። የአስተሳሰብ መንገዳችንን መፈተሽና ማጥራት ስንጀምር፣ በእኛ ተጽዕኖ ሥር ያሉና ልንለውጣቸው የምንችላቸውን ጉዳዮች እንለያለን። ይህን ማድረግ ከቻልን ደግሞ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አሳቦችን ማፍለቅ እንጀምራለን። በሚረባና በማይረባ አሳብ መሃከልም እንለያለን። ስለዚህ ማሰብን ማሰብ መጀመር አለብን እንላለን። በቸር ይግጠመን!
አስተሳሰብን ማስተዳደር – መንገድ ፩
በትላንትናው ዕለት “ማሰብን ማሰብ መጀመር አለብን” በሚል ርዕስ አጭር ጦማር መለጠፋችን አይዘነጋም። ስለ አስተሳሰብ መንገዳችን ማሰብ እንደሚገባን ያሳሰብንበት ነው። ሆኖም ግን በአንዳንድ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ “ስለማሰብ ማሰብ የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ ሳይነሳ አይቀርም። ተግባራዊ እርምጃን የሚጠይቁ ጉዳዮች ሲነሱ፣ “እንዴት?” ወሳኝ ጥያቄ ነው። ዛሬ አስተሳሰባችን ለማስተዳደር ከሚረዱን መንገዶች አንዱን ልጠቁማችሁ ብቅ ብያለሁ።
አስተሳሰብን እንደሚገባን ለማስተዳደር ወይም ሐሳባችንን ለማመንጨት የምንከተለውን ስልት የተሻለ ለማድረግ ከሚረዱን ዋነኛ መንገዶች አንዱ፣ የሐሳብ ጽዳት ማከናወን ነው። ባልጸዳ አዕምሮ ቁም ነገር ለማሰብ መሞከር ተገቢ አይደለም። ይህም ሲባል፣ ማሰቢያችን የጸዳ እንዲሆን ውስጣችንን ወይም ልባችንን (subconsciousሳችንን) ከአላስፈላጊ ቅራቅምቦ አሳቦች ማጽዳት ነው። ቅራምቅቦ እንደሚታውቁት በተለያዩ ጊዜያት ወደ መኖሪያ ቤ/ቦታችን ይዘናቸው የምንገባቸው ቁሳቁሶች ናቸው። ወደ ቤታችን የወሰድናቸው “ይጠቅሙናል” በሚል እሳቤ ቢሆንም እንዳሰብነው የማንጠቀምባቸውና ግልጋሎት ሳይሰጡ ቤታችንን የሚያጣብቡና አቧራ የሚስቡ ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ ለህይወታቸው ወሳኝ በሆኑና ባልሆኑ ቁሳቁሶች መካከል የማይለዩ ሰዎች ሁሉንም “ይጠቅሙናል” በሚል ስለሚሰበስቡ፣ ሳያስቡት ቤታቸው በቅራቅንቦ የተሞላና የሚፈልጉትን ነገር ቶሎ ፈልገው የማያገኙበት ሊያደርግባቸው ይችላል።
የሰው ልጅ አዕምሮም ተመሳሳይ ጠባይ አለው። በሚጠቅመን እና በማይጠቅመን አሳብ መካከል ሳንለይ አሳብ ስለሆነ ብቻ ወደ ውስጣችን እንዲዘልቅ ካደረግን፣ የአስተሳሰብ መንገዳችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እስኪኖረው ድረስ፣ ማሰቢያችንን ሊያጨናንቀውና በአሳብ አቧራ ሊሞላው ይችላል። ስለዚህ የአስተሳሰብ መንገዳችንን የጠራ ለማድረግ፣ ወደ ውስጣችን የምንፈቃዳቸውና አዕምሯችንን የምንሞላባቸው አሳቦችን መፈተሽና አላስፈልጊ ሆነው ያገኘናቸውን ቶሎ ቶሎ ከአዕምሮ ጓዳችን ማስወገድ ወይም ማስወጣት ያስፈልጋል። አዕምሯችን ውስጥ ነጻ ቦታ ሳይኖር ቆንጆ ቆንጆና ጠቃሚ አሳቦችን ማምረት ወይም ማመንጨት አይቻልም። በአሳብ ቅራቅንቦ የተጨናነቀ አዕምሮም ደግሞ ንጹህና በጎ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ አሳቦችን ማምረት አይችልም። አስቀድሞ የሞላን ነገር ነው እንደ ግብዓት ሆኖ በአስተሳሰባችንን ተብላልቶ ሐሳብ ሆኖ በንግግሮቻችን እና በጽሑፎቻችን በኩል የሚገለጠው፤ “ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን አፉ ይናገራል” እንዲሉ።
ስለዚህ ስለአስተሳሰብ መንገዳችን ማሰብና አስተሳሰባችንን ራሱ በአግባቡ ለማስተዳደር ከተነሳን፣ የመጀመሪያ እርምጃችን ማሰቢያችንን ወይም አዕምሯችንን ከቆሻሻና አላስፈላጊ አሉታዊ አሳቦች ማጽዳት የመጀመሪያው እርምጃ ነው እንላለን። በቸር ይግጠመን።
አስተሳሰብን ማስተዳደር – መንገድ ፪
ዛሬ አስተሳሰብን ለማጥራትና ጥራት ያላቸውን አሳቦችን ለማፍለቅ የሚረዳውን ሌላኛውን ዘዴ፣ ስልት ወይም መንገድ ጠቁማችኋለሁ። የምጠቁማችሁ የጠራ የአስተሳሰብ መንገድ እንዲኖረን፣ የሐሳብ ትራፊክ መቀነሻ ዘዴን ነው። እሱም አርምሞ ነው።
አርምሞ ማለት በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ከራስ ጋር በዝምታ ጊዜ የመውሰድ ልምምድ ነው። ከከባቢያዊ ጫጫታና ከአዕምሯዊ የውስጥ ጫጫታ ራሳችንን የምናሳርፍበትና የራስ የሆነ ጊዜ በቀን ውስጥ መፈለግ ሲሆን፣ ጥራት ያላቸውና በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠር የምችሉ አሳቦችን ለማፍለቅ በእጅጉ የሚረዳን ልምምድ ነው። አዕምሯችን በ24 ስዓት ውስጥ በስሜት ህዋሳት በኩል የት የለለ መረጃዎችን ያስገባል። እነዚህ መረጃዎች ደግሞ በአዕምሯችን ተብላልተው ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸው ማለት ነው። ሰው የአርምሞ ጊዜ ለራሱ መመደብ ካልቻለ፣ በየጊዜው ወደ ውስጥ በማሰብ፣ አሳቦቹን ለማጥለል በምክንያታዊ መረጃና በስሜታዊ መረጃ መካከል መለየት አይችልም። ሁልጊዜ በደመነፍስ ስሜታዊ መረጃዎችን እየተከተለ ይኖራል። ከዚህም የተነሳ በምክንያት ላይ ያልተመሠረቱና ትክክል ያልሆኑ ብዙ አመለካከቶችና የአስተሳሰብ መንገዶችን ሊያዳብር ይችላል። አርምሞ ሰዎች ከውጭ በማየት፣ በመስማት፣ በማንበብ፣ ወይም በሌላ የስሜት ህዋስ ያስገቡትን መረጃ ለመገምገም ዕድል ስለሚሰጥ፣ የጠለለና የጠራ ሐሳብን እንድናመነጭ ይረዳናል።
ሌላኛው የአርምሞ ፋይዳ፣ አዕምሯዊ ጫጫታዎችን ለማርገብና የጠራ አስተሳሰብ ለማዳበር ይረዳናል። ብዙ መረጃዎችን በስሜት ህዋሳቶቻችን በኩል እንደምናስገባ ሁሉ፣ ከነዚህ መረጃዎችም ሆነ እንዲሁ በራሱ አዕምሯችን ብዙ አሳቦችን ያመነጫል። የስነ ልቦና ባለሙያዎች በሰዎች ላይ ባደረጓቸውን ጥናቶች፣ አንድ ሰው በቀን ውስጥ እስከ 6 ሺህ 200 ያህል የተለያዩ አሳቦችን ሊያመነጭ ይችላል። አስቡት! መቼስ እነዚህ ሁሉ አሳቦች ጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም። አርምሞ ከአዕምሯችን የሚፈልቁ አሳቦችንም ለመገምገም ዕድል ይሰጠናል። ሆኖም ግን አርምሞ በልምምት የሚመጣ እንጂ፣ ሰው ዝም ስላለ ብቻ አስተሳሰቡን መቆጣጠርና ማጥራት ይችላል ማለት አይደለም።
በተለይ አሁን ባለንበት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን፣ ማህበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀም በራሱ እንደ አደንዛዥ ዕጽ ሱስ አስያዥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ሰዎች ከራሳቸው ጋር ብቻ የሚያሳልፉት ከእንቅልፍ ውጭ የሆነ ጊዜ የላቸውም። ይህ ደግሞ ሰዎች ባተሌና ተቅበጭባጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። አዕምሯቸው ከነቃበት ጊዜ ጀምሮ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎቹ በኩል ለሌሎች ሰዎች አሳብ ያለ ፋታ ስለሚጋለጥ፣ ለራሳቸው ጊዜ ሳያገኙ ይመሻል፣ ይነጋል! ከዚህም የተነሳ ራሳቸውን አዳምጠው ስለማያውቁ፣ በወሳኝ የህይወት ጉዳዮች እንኳን የጠራ የራስ አቋምና አሳብ የሚባል ነገር ላይኖራቸው ይችላል። በቀላሉ ለመንጋ አስተሳሰብም ተጋላጭ ይሆናሉ።
ስለዚህ አስተሳሰብን በሚገባ ለማስተዳደርና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ አሳቦችን ለማመንጨት አርምሞ ወሳኝ አስተሳሰብን የማስተዳደሪያ መንገድ ነው። አርምሞን ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ውስጥ ቢያንስ 30 ደቂቃ ለብቻ ከራስ ጋር ብቻ በተመቻቸ ቦታ መሆንን ይጠይቃል። ውሏችን ውስጥ ያጋጠሞኑን ሁኔታዎች በዝምታ ለማጤንና ውስጥንም ለማዳመጥ ዕድል ይሰጠናል። ያስገባናቸውን አሳቦች ለማበጠርና ለማጥራትም ይጠቅመናል። አርሞምን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ የአስተሳሰብ መንገድ እንድናዳብር ተጋብዛችኋል። በቸር ይግጠመን!
#መተሳሰብ፣ #መቀባበልና #መቻቻል #ያቃተን #ለምን?
ወቅታዊ ሁኔታችንን ስንመለከት እንደ ማህበረሰብ መገፋፋት የበዛበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ሰላምና እረፍት ርቆናል። ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት እየተቧደኑ በተካረረ ሁኔታ ሲገፋፉና ከፍ ሲልም ሲጠፋፉ በአገራችን መመልከት የተለመደ ሆኗል። በዘር መጨፋጨፉም የቀደሙ የፖለቲካ አካሄዶች ትፋት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ላይ ደግሞ በተለይ ለአገር አቀፍ ምርጫ እየተንደረደርን ባለንበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች በፖለቲካ ርዮተ አለም ልዩነት ምክንያት የሰዎች መጠላላትና መገፋፋት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። የዚህ ጦማር ዓላማ ለዚህ መጠላላት፣ መገፋፋትና አለመተሳሰብ የሚዳርጉንን ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች በዛሬው ሐሳቤ ወደ እናንተ ለማድረስና በጋራ እንድንጸልይም ለመጠየቅ ነው። አንባቢ ሆይ፣ ጸሎት በማድረሱ በኩል እንድትተባረ/ሪኝ አደራ እላለሁ።
መተሳሰብ እንዲያቅተን ያደረገው የመጀመሪው ምክንያት ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት አስተሳሰባችንን እየመራ ስለሚገኝ ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ላይም ሆነ በዜና አውታሮቻችን የምንሰማቸው ወሬዎች፣ ስሜትን በእጅጉ የሚነኩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ ቆም ብሎ በምክንያት ለማሰብና ማመዛዘን እስካንችል ድረስ በስሜት ጎርፍ ጠርገው ስለወሰዱን ነው። መረጃዎቹ ስሜትን የሚነኩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ ምንጫቸውንም ሆነ ተዓማንነታቸውን ሳንመረምር እንደወረደ እየተቀበልናቸው ስሜታዊ እያደረጉን እና ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው የተገለጸ ሰዎችን ስብዓዊ ፍጡርና እና ሰው መሆናቸውን ወደ መርሳት እያደረሰን ይገኛል። ሌላው ደግሞ [በተለይ በፖለቲካው ዓለም] ርዮተ ዓለሙን የተቀበልነው ሰው፣ የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች በራሳችን የህሊና ሚዛን ሳንመዝናቸው እንደ ወረዳ መቀበላችን ያስከተለብን ዕዳ ነው። የምንደግፈውና ሐሳቡን የገዛነው ፓርቲ ሌሎችን ጭራቅና ከሰውነት ተራ የወጡ አድርጎ ሲስላቸው፣ እኛም በደፈናው ሆ ብለን የፖለቲከኞቹን አሳብ በስሜት በመከተል ላይ እንገኛለን። ምንም እንኳን ሰዎቹ ጓደኞቻችን፣ ጎረቤቶታችንና የቅርብ ሰዎቻችን ቢሆኑም፣ ስለሰዎቹ ከሰማናቸው ትርክቶች የተነሳ ከእነርሱ ጋር ያለንን መስተጋብር ማቀብና እነርሱን ማግለል ውስጥ እንገባለን። ይህ ሁሉ የሚሆነው በስሜታዊነት ተገፋፍተን የልቡና ዓይናችን ነገሮችን አጥሮቶ እንዲያይ ዕድል በመንፈጋችን ነው። ስሜታችን ምክንያነታዊታችንን ስላሸነፈው እና ማሰቢያችን ላይ ስለዘጋበት ነው። ፈጣሪያችን እና አምላካችን ሆይ፣ ከእንስሳት የሚለየንን ምክንያነታዊነታችንን መልስልን፤ ስሜቶታችንን ተቆጣጥረን ወደ ልቦናችን የምናስገባቸውን አሳቦች ሁሉ በሰጠኸን አዕምሮ በምክንያት ፈትሸን፣ የሚገ’ውን በጎ አመለካከት እንድናዳብርም እርዳን። አሜን!
ሁለተኛው መቀባበል ያለመቻላችን ወይም የመገፋፋታችን ምክንያት በሌላ ሰው ቦታ/ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ አለመቻላችን ነው። ፈረንጆች ኤምፓትሲ (empathy) ይሉታል። በእዝነ ልቦና ለአፍታ ያን ሌላ ሰው ሆኖ ከዚያ ሰው አንጻር ሁኔታዎችን ለማስተዋል፣ በስሜት ደረጃ ለመረዳት እና ለመገንዘብ የመሞከር ፍላጎትና ሂደት ነው። አሁን ብዙ መገፋፋት እንዲኖር እያደረገ ያለው አንዱ ምክንያት ሰዎች የራሳቸውን ስሜት ብቻ እንጂ የሚጋጯቸው ወይም የሚጠሏቸው ወይም የሚጣሏቸው ሰዎችም ልክ እንደ እነሱ ስሜት፣ ፈቃድና አሳብ ያላቸውና ሰዎች መሆናቸውን ይዘነጉታል። ራሳችን፣ ስሜታችን፣ ፍላጎታችን እና ፈቃዳችንን መፈለግ ላይ ብቻ የሚናተኩር ከሆነ፣ ለሌላ ማንኛውም ሰው ደንታ ቢስ እንሆናለን። ይህ ደግሞ መተሰሰብን ያጠፋል። ቀጥሎም ደግሞ ማህብራዊ አንድነትና አብርሆትን ያፈርሳል፤ በጉልበት ወደ መገፋፋትና መጠላላትም ያመራል። ነገር ግን እንደምንም ቆም ብለን፣ “ያም ሰው እኮ ስሜት አለው፤ ፍላጎት አለው። ለምን አለመረጋጋትና ብስጭት ውስጥ ገባ? ስሜቱን የረበሸውና ብስጩ ያደረገው ሁኔታ ይኖር ይሆን? ወደዚህ ሁኔታ ውስጥ አብረን ከመግባታችን በፊት ያጋጠመው አሉታዊ ክስተት ይኖር ይሆን?” የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ ብንችል፣ ለዚያ ሰው የሚራራ አንጀት ይኖረናል። እውነተኛ ሰብዓዊነታችንም ይገለጣል። ነገሮችን ከማጦዝና ከማባባስም ይልቅ፣ ነገሮች የሚረጋጉበትን መንገድ መፈለግ እንጀምራለን። በንዴትና በቁጣ ስሜት ውስጥ እንኳ ብንሆን፣ በሌላ ሰው ጫማ ውስጥ ሆኖ ነገሮችን ለማስተዋል መሞከር፣ በምክንያታዊነት የሚመራው ሰብዓዊነታችን እየጎላ፣ በስሜታዊነት የሚመራው አውሬነታችን እየቀነሰ ይሄዳል። ፈጣሪያችን እና አምላካችን ሆይ፣ ሰው አድርገህ ስትፈጥረን እርስ በርሳችን እንድንተሳሰብና እንድንረዳዳ ነውና በግጭቶችና በሐሳብ ልዩነቶች ወቅት፣ በሌላ ሰው ቦታ ሆነን ሁኔታዎችን ከሁሉም አንጻር መረዳት የምንችልበትን ማስተዋልና ልምድ አብዛልን። አሜን!
ዛሬ ላካፍላችሁ ያሰብኩት ሦስተኛውና የመጨረሻው መቻቻልን እንዳንችለው ያደረገን ምክንያት፣ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ አለመስጠት ነው። የሰው ልጅ ሰው ሆኖ ከመፈጠሩ በተጨማሪ የተለያዩ ማንነቶችን ከባህል፣ ከአስተዳደግ፣ ከኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ከትምህርት ሁኔታ፣ ከዕድሜ … ወዘተ አንጻር ሊያገኝ ይችላል። ከምንም በፊት ግን መሠረታዊ ማንነቱ ሰውነቱ ወይም ሰብዓዊነቱ ነው። ሰው በጾታ ወንድና ሴት ከመባሉ በፊት ሰው ነው። ወንድ ሰው፤ ሴት ነው። ሰው ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ቀይ ወዘተ ከመባሉ በፊት ያው በመሠረታዊነት ሰው ነው። ሰው የተለያዩ ቋንቋዎችን ከመናገሩ በፊት ያው በመሠረታዊነት ሰው ነው። ሰው የተማረ ወይም ያልተማረ፤ ደሃ ወይም ሀብታውም፣ ታዋቂ ዝነኛ ወይም የማይታወቅ ከሆኑ በፊትም በመሠረታዊነት ያው ሰው ነው። አሁን አሁን በተለይ ከዘርና ከብሔር ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ብዙ ችግሮች መንስኤ እየሆነ የሚገኘው ሰውን ከሰውነቱ በፊት በሌሎች ማንነቶቹ ለማወቅ ያደርግናቸው ጥረቶችና ትኩረቶች ናቸው። የእኛ ዓይነት አስተሳሰብና አመለካከት ሳይኖረው ሲቀር፣ የእኛ ቡድን አባል ስላይደለ፣ ሰውነቱ ከእኛ ሰውነት ያነሰ እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን። ስለዚህ ጉዳት ቢደርስበት ህመሙ አያመንም። ይህ ደግሞ በሽታ ነው። ህሊናው ሙት ያልሆነ ሰው፣በአስተሳሰብ ከርሱ የተለየ ሆኖ የተገኘን ሰው፣ በጾታ፣ በፖለቲካ አመለካቱ፣ በብሔሩ ወይም በቆዳ ቀለሙ ከርሱ ያነሰ እንደሆነ ቆጥሮ ሰውነቱን አያሳንሰውም። በእነዚህ ማንነቶቹ ላይ ተመሥርቶ አሳንሶ በመመልከት ጉዳት የሚያደርስበት ከሆነ እራሱም እንደዚያ ሰው፣ ሰው መሆኑን ረስቷል ማለት ነው። ሰውን ከምንም በላይ በሰውነቱ መቀበልና ዋጋ መስጠት፣ ሌሎች ሰዎች እንደእኛ በማያስቡበትና የተለየ አመለካከት በሚኖራቸው ጊዜ እንዳንጠላቸውና እነርሱን በጉልበት ለማስወገድ እንዳናስብ መግቻ ልጓም ይሆነናል። መገፋፋትን ለመቀነስ፣ መተሳሰብን ለመጨመርና ለመቀባበል በመጀመሪያ ደረጃ ሰውን በሰውነቱ መቀበልና ዋጋ መስጠት ከሌላ ከየትኛውም ማንነቱ መቅደም አለበት። እኩል የሆንነውም በሰውነታችን ብቻ ስለሆነ ነውና። ፈጣሪያችን እና አምላካችን ሆይ፣ መሰሎቻችንን የሰው ልጆች ከምንም በላይ በሰውነታቸው ብቻ ቅድሚያ እንድንቀበላቸው እርዳን። የልዩነትና ያለመቀባበል ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች ማንነቶች ሰውነቱን በሚሸፍኑብን ጊዜ እንደ እኛው ሰው መሆናቸውን እንገነዘብ ዘንድ የልቡና ዓይኖቻችንን አብራልን። አንተ ፈጣሪያችን ለሰው ልጅ የሰጠኸውንም ዋጋ እንድናስታውስ እባክህን እርዳን። አሜን!