ነገ ዓለም ወደ ትናንሽ ቁርጥራጮች እንደምትቀየር ባውቅ እንኳን ዛሬ አፕል መትከልን አልተውም፡፡
ማርቲን ሉተር
እንደሚታወቀው በማርቲን ሉተር የተቀጣጠለው የአውሮፓ ተሐዲሶ ጉዞ ሃይማኖታዊ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን ፖለቲካና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን በሙሉ የነቀነቀ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡
ታላቋ ሮም ከወደቀችበት ከ476 ዓ. ም ጀምሮ እስከ 14ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ የነበረው ዘመን በተመለምዶ ‘የጨለማ ዘመን’ ወይም መካከለኛው ዘመን ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ ይህ ዘመን የጨለማ ዘመን የተባለበት ምክንያት ምንም ሳይንሳዊ ግኝቶች ያልተገኙበት፣ የጥበብ ሥራዎች ያልተሠሩበትና ታላላቅ መሪዎች ያልተነሱበት ዘመን ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ በዚያ ዘመን የነበረችው ካቶልካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትኩረቷን ወደ ሕንጻ ግንባታ ያዞረች ስትሆን በፖለቲካ ሜዳም የበላይነት ነበራት፡፡ ማኅበረሰቡ ድሃ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቷ ግን ብዙ ሀብት አካብታለች።በዚያ ዘመን የነበረው ተራ ማኅበረሰብ በፊውዳል ሥርዓት የሚተዳደር ነበር፡፡ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ የአስተራረስ ዘዴ የሚከተሉ ሆኖ መሬቱ በከበርቴዎች ተቀራምቶባቸዋል፡፡
በ1517 ዓ.ም ማርቲን ሉተር የተሰኘ የሮም ቄስ ባለ 95 የመቃወሚያ ነጥቦችን ጽፎ በዊትስበርግ አደባባይ ላይ በመለጠፍ ከዚህ በፊት ይፈራ የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ተገዳደረ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ አብዮቱ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የቀጠለ ሲሆን እሱን ተከትሎ ብዙ የለውጥና የነውጥ ሂደቶች በአውሮፓ ምድር ተስተናግድዋል፡፡ ይህም በታሪክ ተሐዲስ (Reformation) ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ይህ ተሐዲስ እንዲሁ ሃይማኖታዊ ዕድሳት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አጀንዳዎችን ያነገበ ነበር፡፡
ይህንን አስመልክቶ አንድ ማክስ ወበር የተሰኝ ጀርመናዊ የሥነ-ሰብ ምሁር የፕሮቴስታንት ተሐዲሶ እንዴት የአውሮፓን ኢኮኖሚ እንደቀየረ ያተተበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀበት ሥራ አቅርቧል፡፡ በለተይ ተሐዲሶው የካፒታሊዝም ሥርዓት በመፍጠር ሂደት የተጫወተው ሚና ቀላል እንዳልነበረ ያትታል፡፡ ማክስ ወበር “The Protestant Ethic and the Spirit of Capitalism” በተባለው መጽሐፉ ተሐዲሶው በምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ፣ የቢሮክራሲና ብሔረ መንግሥት ምሥረታ ለውጥ ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ያብራራል፡፡
‘ተሐዲሶ ምን አድርጎ ነው የአውሮፓን ማኅበረሰብ የሥራ ባህል ሊቀይር የቻለው’ ብለን ከጠየቅን ምላሹ በቀላሉ “የአስተሳሰብ ለውጥ” በማምጣት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ከዚያ በፊት ክርስቲያኖች ስለዚህች ምድር ያላቸው አስተሳሰብ መንታ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ሥራዎችን ‹‹ዓለማዊና መንፈሳዊ ወይም ሥጋዊና መንፈሳዊ›› በማለት ክፍፍል ማድረግ የተለመደ ነበር። ያ አስተሳሰብ ሰዎች ዓለማዊ ሥራ ብለው የሚያስቡትን በግደለሽነት እንዲሠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ የተሐዲሶ አባቶች በተለይ ጆን ካልቭን በኢኮኖሚ መበልጸግ የቅድመ ምርጫ (Predestination) ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው ብሎ በማስተማሩ ሁሉም ክርስቲያን የተመረጠ መሆኑን ለማረጋገጠ ጠንከሮ መሥራት ጀመረ፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚ ብልጽግና በእግዚአብሔር የመመረጥ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ስለሚታመን ነው፡፡ ሥራ ፈቶችና እራሳቸውን መለውጥ ያልቻሉ ሰዎች እንዲጠፉ የተፈረደባቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለዚህ አንድ የተመረጠ ሰው ከአምላኩ ጋር በሚያደርገው የግል ተራክቦ በተጨማሪ ሕይወቱን ትርጉም ባለው መንገድና በዓላማ መምራት የዳነ ሰው መሆኑም ማስመስከር ይኖርበታል፡፡ ካልቭን “ማንም ሰው፤ ሀብታምም ሆነ ድሃ ጠንክሮ መሥራት አለበት ምክንያቱም ሥራ የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸሚያ መሣሪያ ነውና” ብሎ አስተምሯል፡፡ ይህ ማለት በዓለማዊና ሥጋዊ ሥራዎች መካከል ለዘመናት የቆመው የልዩነት ግድግዳ የሚደርምሰ አብዮታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰዎች ከፍጥረተ ዓለም ጋር የታረቁበት ምዕራፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሰው በውድቀት ምክንያት የተበላሸውን ዓለም እንደገና ለማበጀትና በሥነ ፍጥረት ሂደት ውስጥ ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት የእግዚአብሔር መሣሪያ እንድሆን ነው የተጠራው፡፡ ካልቭን ሰዎች ሀብትንና ንብረትን እየተመኙ እንዲኖሩ ወይም ቀለል ያለ ሕይወት እንዲመሩ ሳይሆን አቅማቸውን አሟጥጠው በመጠቀም ምድርቱ የምትሰጣቸውን ፍሬ በላባቸው ዋጋ እንዲያገኙ አበረታትቷል፡፡ ያገኙትን ደግሞ እንደገና ኢንቨስት እያደረጉ የበለጠ እንዲባዛ ማድረግም የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ይህ ለካፒታሊዝም የመሠረት ድንጋይ የጣለ ሐሳብ ነው፤
የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ፈልጎና ውጤታማ ለመሆን መሥራትም የክርስቲያን ግዴታና ኃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ካልቭር ሥራ እግዚአብሔርን የምናገለግልበት መንገድም ነው፣ ጥሪም ነው፡፡ በዚህም በአንዳንዱ ሥራዎች ላይ ብቻ (በተለይ መንሳዊ የተባሉት) ላይ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ ሌሎች ሥራዎችን ማሳነስ እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል፡፡
ይሄ የካልቭን አስተምህሮ በመካከለኛው ዘመን እንቅልፍ ላይ የነበረችውን መላ አውሮፓ የቀሰቀሰ አስተምህሮ ሆኖ አልፏል፡፡ የአውሮፓ ሥልጣኔ ከተኛበት የተቀሰቀሰው ከሞላ ጎደል በእንደዚህ ዓይነት አስተምህሮ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ በአውሮፓ ውስጥ አዲስ የሥራ ባህል ተቀሰቀሰ፡፡ የተሐዲስ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ያሳረፈባቸው አገሮች በኢኮኖሚ ለውጥ ከሌሎች የበለጠ እያደጉ በመምጣታቸው ቀስ በቀስ ሁሉም አውሮፓውያን ወደዚያ አዘነበሉ፡፡ በተለምዶ የፕሮቴስታንት ሥነ ምግባር ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ባህል ሥራ ላይ ያሳደረው፡- የሥራ እርካታን እንደገና እንዲቃኝ፣ ትጋት፣ ሰዓት አክባሪነት፣ ለሥራ ቅድሚያ መስጠት እና የመሳሰሉ ተጽዕኖዎችን አምጥቷል፡፡ ሰሜን አሜሪካ ያለ ፕሮቴስታንት ተሐዲሶ ተጽዕኖ ዛሬ እንደነ ላቲን አሜሪካ ነበር የምትሆነው ብለው የሚከራከሩ ምሁራንም አልጠፉም (Samuel Huntington, 2004a)፡፡
ከዚያ በኋላ ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ ከዘመነ ተሐዲሶ ትንሽ ቀደም ብሎ የተቀጣጠለው የትንሳኤ ዘመን (Renaissance)ን ጨምሮ፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተቀነቀነው ዘመነ አብርሆት (Enlightenment)ና የአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት የተባሉ ተከታታይ የለውጥ ማዕበሎች የምዕራቡን ዓለም ሲንጧት ቆይተዋል፡፡ በእነዚያ ዘመናት ብዙ የለውጥ ሀሳቦች ፈልቀዋል፣ ብዙ አሳቢያንም ተነስተዋል፣ ብዙ ቴክኖሎጂዎችም ተፈብርከዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንት
ፕሮቴስታንት ወይም በተለምዶ ‘ወንጌላውያን’ ተብሎ የሚጠራው የሃይማኖት ክፍል ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠር ይነገራል[1]። ይህ ከሌሎች ሃይማኖቶች አንጻር፣ በተለይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና ከእስልምና ጋር ሲነጻጸር በዕድሜ ትንሹ ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም ሃይማኖቱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላል የሚታይ አይደለም። በተለይ ሃይማኖቱ ሲገባ ሰማያዊ መንግሥት ብቻ በመስበክ ላይ ሳይገደብ ሁለንተናዊውን ሰው ለማገልገል ባደረገው ጥረት ብዙ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን በማቋቋም የደርግ መንግሥት ተነስቶ ተቋማቱን እስኪወርስ ድርስ ብዙ ልማታዊ ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ ነበር። ብዙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችም ከዘመናዊው ትምህርት ጋር የተተዋወቊት በዚህ ሃይማኖት በተፈጠሩ ት/ቤቶች በኲል ነው።
ሃይማኖቱ ማኅበራዊ ተቋማትን በመመሥረት ብቻ የሚታወስ ሳይሆን በሰዎች ሥነ-ምግባር ላይ ያመጣው በጉ ተጽዕኖም ቀላል የሚባል አልነበረም። በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ‘ጴንጤ’ ተብሎ የሚጠራው የወንጌላውያን ክርስቲያን በማኅበርሰቡ በመልካም ምስክርነታቸው እንደሚታወቁ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ጰንጤ አይሰርቅ፣ አይጠጣም፣ በሥራ አይለግምም፣ አያጭበረብርም ተብሎ ይታመን ነበር።
ሆኖም ግን ከ1980ዎች ወዲህ ሃይማኖቱ ከጫና (ስደት) ነጻ ሲሆን ለብዙ ዘመናት የገነባውን መልካም ስም ይዞ መቀጠል አልቻለም። በእነዚህ የነጻነት ዘመናት ወንጌላውያን ያጡት መልካም ስማቸው ብቻ ሳይሆን ማንነታቸውም ጭምር ነው ማለት ይቻላል። የወንጌላውያኑ እውነተኛ ማንነቶች በእምነት ቃል አስትምህሮ የተተካ ይመስላል።
የአውርፓ ፕሮቴስታንት በሥራ ባህላቸው ላይ ያሳረፈው ጒልህ ሚና ከላይ ለማየት ሞክረናል። የፕሮቴስታንት እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ግን የአውሮፓው ፕሮቴስታንት ብዙ የለውጥ ማዕበሎችን አስነስቶ ከረገበ በኋላ ነው። ስለዚህ ሃይማኖቱ አውሮፓን የለወጠውን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ተጽዕኖው ትንሽ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ተቀባይነት ማጣቱ ተጽዕኖው ቀላል እዲሆን ካደርጉ ምክንያቶች መካከል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።
በሌላ በኩል ሃይማኖቱ ራሱ በጰንጠቈስጣዊናና በካሪዝማዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተደባለቀበት ጊዜም ነበር። ጰንጠቆስጢያውያንና ካርዝማውያን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ የጸጋ ሥጦታዎችን መለማመድ ላይ የሚያተኲር ነው። ከዚያም ዐልፎ እግዚአብሔር ገና ምድሪቱን በታላላቅ ጒብኝቶች ይጎበኟታል ብለው የሚያምኑ ናቸው። በኛ አገር አውድ “ኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን” እንደምጠብቃት ሲነገር ሰምተናል። በዚህ ዙሪያም ብዙ የከፍታ ዘመን ትንቢቶችም ተነግረዋል፣ ዝማሬዎችም ተዘምረዋል፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጎበኛታል ተብለናል፡፡ ጉብኝቱ ደግሞ መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንደሆነም ሰምተናል፡፡ ተስፋዎቹን በአጠቃላይ በሁለት ጎራ ልንከታቸው እንችላለን፣ ሰማያዊ በረከቶችና ምድራዊ በረከቶች በማለት፡፡ ሰማያዊ በረከቶች ብዙውን ጊዜ Revival ተብለዋል፡፡
በእርግጥ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንደሚባርክ የሚያምኑት ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። ሁሉም ክርስቲያኖች ይህንን እምነት የሚጋሩ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር እንደሆነች የሚያምኑት ብዙ ሰዎች አሉ።
ችግሩ ከእመነቱ ወይም ከትንቢቱም አይመስለኝም። ተስፋ እውን እንዲሆን ዝጅግታችንን ምን ይመስላል ብለን መጠቀቅ ነው ዋናው ነገር። አሁን የያዝነው መንግድ ወደዚያ ተስፋ ያደርሰናል ወይ? ለመሆኑ የሥራ ትጋታችን ሳይጨምር፣ አስተሳሰባችን ሳይቀየር፣ እግዚአብሔርን እንደሚያውቅ ሕዝብ መኖር ካቃተን በረከቱ እንዲሁ እንደ መና ከሰማይ ዱብ የሚል ነገር ነው?
በተለይ ዛሬ በእምነት እንቅስቃሴ የተቃኘው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት የሥራ ባህላችንን ክፉኛ የሚፈታተን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሰዎች በትጋትና በልፋት ሊያገኙ የሚችሉትን ምድራዊ ሀብቶች ‘በእምነት’ ብቻ ወይም ለሚተነብዩ ሰዎች መሰዋዕት በመስጠት የሚመጣ አድረገው የሚያስተምሩ ሰዎች እንደ አሸን መፍላታቸው ጒዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል። ሰዎች ሥራቸውን አቁመው በተንባዮች መንደር እንዲንከራተቱ የሚያደርግ የስንፍና አስትምህሮዎች በሚዲያዎች ታግዞ ወደየሰው ቤት መግባት ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህ ዓይነት መንገድ የሚመጣ የከፍታ ዘመን ያለ አይመስለኝም። የከፍታ ዘመን በሥራ ትጋትና በኑሮ ንጽህና የሚመምጣ ይመስለኛል። ምክንያቱም የፈጣሪ ሕግ ይህንን ስለሚደግፍ።
የኢትዮጵያ ዕድል
የምዕራቡ ዓለም በዚህ ሁሉ የለውጥ ማዕበል ሲናጥ ኢትዮጵያ ምን እያደረገች ነበር? ከታሪክ እንደምንረዳወው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3ኛው ክ/ዘመን በዓለም ላይ ገናና ከነበሩት አራት ሥልጣኔዎች (ሮም፣ ባቢሎን-ፐርሺያ፣ ቻይና) ውስጥ አንደኛው የአክሱም ሥልጣኔ ነው፡፡ ይህ የሥልጣኔ መመሳሰል እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ ያ ማለት ኢትዮጵያና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም በሥልጣኔ ደረጃ እኩል ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ለረጅም ዘመናትም ጎን ለጎን ሲራመዱ ከርመዋል። አውሮፓውያን ከኢትዮጵያ የተለየ የሕይወት ጎዳና መከተል የጀመሩ ከዘመነ ትንሳኤ (14ኛ ክፍለ ዘመን) ጀምሮ ነው[2]፡፡ ያኔ እርምጃቸው መፍጠን ሲጀምር የኛ ግን ባለበት እየረገጠ ወደ ኋላ ቀረ።
እነዚያ የለውጥ ማዕበሎችን ስናስብ ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግለሰቦች መኖራቸው እሙን ነው። ዘመነ ትንሣኤን ስናስታውስ እነ ሊኦናርዶ ዳቪንቺና ሚካኤል አንጀሎን እናስባለን፡፡ የተሐዲሶ ዘመን የተመራው በእነ ሉተር፣ ጆን ካልቭንና ዚውንግሊን ነው፡፡ ዘመነ አብርሆት ደግሞ በበኩሉ እነ አማኑኤል ካንት፣ እነ ደቭድ ሂሁም፣ ኒቼና ሩሶ የመሳሰሉ ፈላስፎችን አፍርቷል፡፡
ዓለምን ዛሬ በምናያት መልክ የቀረጹት ግለሰቦች ከሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አልተፈጠሩም ወይ? ብለን እንጠይቅ፡፡ ለምን ቀድመን ጀምረን ወደ ኋላ ቀረን? እነሱ ይኸን ሁሉ ርቀት ሲሄዱ እኛ ለምን ባለንበት እየረገጥን ከረምን?
አንዳንድ ምሁራን እንደ ኩሬ የረጋውን የኢትጵያን ባህል ለማናወጥና አዳዲስ የለውጥ ማዕበሎችን ለመፍጠር የሞከሩ ጥቂት ግለሰቦች መኖራቸውን ያወሳሉ፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተነሱ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት የተባሉ ኢትዮጵያዊ ፈላስፎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት የተለመደውና እንደ ባህል ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ አስተሳሰቦች በመጠየቅና በመሞገት አዲስ የባህል አድማስ ለመክፈት ሞክረው ነበር፡፡ ከተሟገቱባቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሥራ ባህል ለውጥ ነው፡፡ ወልደ ሕይወት የሚባለው ፈላስፋ ስለ ሥራ ባህል ያለውን እንመልከት፡-
ለኑሮህ ተስማሚ የሆነውን የእጅ ሥራ ውደድ፡፡ እንድትጠቀምበትም በእርሱ ዕውቀትን አግኝና እርሱ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነውና የእጅን ሥራ በመሥራት አትርፈበት፡፡ያለ እጅ ሥራ ግን የሰው ፍጥረት ሁሉ ይጠፋና ኑሮውም ሁሉ ይፈርሳል፡፡ አንት ግን የእጅ ሥራ ለድሆችና ለሰራተኞች፣ ለአንጥረኞችና ለአናጺዎች፣ እንዲሁም ለገባር ልጆች እንጂ ለታላላቆችና ለከበርቴ ልጆች አይገባም አትበል፡፡ይህ ሐሳብ ከትዕቢተኛ ልብ የሚመነጭ ነው[3]፡፡
እንደዚህ የመሰሉ ብርቱ ተሟጋች ሰዎች በታሪክ ውስጥ ብቅ ብሉም ተሰሚነት ሊያገኙ አልቻሉም። ትልቁ ችግር እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአዳዲስ ሐሳቦች ከልክ በላይ ዝግ መሆናችን ይመስለኛ። ከተለመውና ከምናውቀው ውጪ የተለየ ሐሳብ ሲመጣ ግር ብለን በጋራ የማውገዝ ልምድ አዳብረናል። እነ ዐጼ ቴዎድሮስ ያቀረቡት የዘመናዊነት ፕሮጀክት፣ እነ ምኒልክ የሞከሩት አዳዲስ ቴክኖጂዎች፣ እነ ገብረ ሕይወት ያቀረቡት ኢትዮጵያን የማዘመን እሳቤ “ለውጥ ጥዪ” ባህላችንን ዘልቆ ማለፍ አልቻለም። ዛሬም የለውጥ የተቃውሞ ጒልበታችን አልደከምም።
[1] ሕንጸት፣ ቊጥር 001 (መጋቢት 2006 ዓ.)
[2] ዮናስ ታደሰ፣ ፋሲል መራዊ፣ ብሩህ ዓለምነህ፡ የፍልስፍና ትምህርት ቅጽ 1 (2013 ዓ.ም)
[3] ሐተታ ወልደ ሕይወት (ብሩህ ዓለምነህ፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች ትንታኔ ከነ ሐተታቸው) ገጽ 333