የሳምንቱ አነጋጋሪ አጀንዳ፡ ንጉሱ ቱራ-ኦሬ ከሰማይ ስላዘነበው ዳቦ ጉዳይ፡፡ ንጉስ ቱራ-ኦሬ ዳቦ አዘነበ፣ ለሕዝቡ በነፃ አከፋፈለ፡፡
በመጀመሪያው ቀን ሕዝብ እልል እያለ ‹‹ንጉሱ ቱራ-ኦሬ ሺህ ዓመት ንገስ›› እያለ አሞገሰ፡፡
በሁለተኛው ቀን ሕዝቡ ድጋሜ ዳቦውን ለመውሰድ ሲመጣ ድንጋይ ይዞ መጣ፡፡ እያንዳንዱ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ዳቦ ሰበሰበ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ይዞት የመጣውን ድንጋይ አልጣም፡፡ በአንድ እጁ ዳቦ በሌላኛው እጁ ድንጋይ ያዘ፡፡ ግማሹ ዳቦውን እየገመጠ፣ በሌላኛው እጁ የያዘውን ድንጋይ ለመወርወር ይቃጣ ጀመር፡፡ ግማሾ በዚህ ንጉስ የዘነበ ዳቦ ከምበላ ብሞት ይሻለኛል ብሎ ዳቦውን ሳይወስድ ድንጋዩን ብቻ ይዞ ቆመ፡፡ ሌላኞቹ ደግሞ የኛ ፓርቲ መሪዎች ውሰዱ እስኪሉን ድረስ ምንም አንነካም ብለው ድንጋይ እንደያዙ ቆሙ፡፡
ጋዜጠኛ መጣ፡፡ ‹‹ለምድን ነው ድንጋይ የያዛችሁት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ንጉሱን ለመውገር እንደሆነ ነገሩት፡፡ ጋዜጠኛው ጠየቀ፡- ‹‹ዳቦ ያዘነበላችሁ ንጉስ ለምን ትወግራላችሁ?” ‹‹ንጉሱ እያታለለን›› አሉ፡፡
ጋዜጠኛው ወደ አንድ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ሄደ፡፡ ‹‹ትናንትና ንጉሱ ቱራ-ኦሬ ስላዘነበው ዳቦ ምን አስተያየት አለህ? ›› ብሎ ጠየቀ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው መለሰ፣ እንዲሀም አለ ‹‹ይህን ሕዝብ በዳቦ ለመሸወደ የተደረገ ሴራ ነው፣ ሕዝቡ ዳቦ መች ጠየቄ፣ ሕዝቡ እያለ ያለው መብት ስጡኝ ነው እንጂ ዳቦ አዝንቡልኝ መች አለ? ይህ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ ሕዝብን ሳያማክሩ በአምባገነናዊነትና በማን አለብኝነት መንፈስ የተደረገ የልወደድ ባይ ድርጊት ነው››
ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ፡- ‹‹ግን እኮ ሕዝቡ ዳቦ እንደሚያስፈልገው ምንም ጥያቄ አያስፈልግም፣ መራቡ ይታወቅ የለ? ደግሞ ዳቦ ማዝነቡ ምንድን ነው ክፋቱ?”
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ “ ዳቦ መዝነቡ ክፋት አለው አላልንም፣ እኛ እያልን ያለነው ዳቦ ለማዝነብ መጀመሪያ ሕዝቡን ማነጋገር አለበት ነው፡፡ ይኸ ሕዝብ እኮ ሄዶ ዳቦውን እንዲወስድ የመከርነው እኛ ነን፡፡”
ሌላኛው ተቃዋሚ መሪ ጋ ሄዶ ጠየቀ፡ መሪውም መለሰ “ቢያንስ ይህንን የሚያህል ዳቦ የማዝነብ አገራዊ አጀንዳ ለመተግበር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ያስፈልጋል፣ ድርድር ሳይደረግ፣ ለዚህ ሕዝብ ዳቦ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም በሚለው ጉዳይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ዝም ብሎ አንድ መሪ ተንስቶ እንደት በራሱ ፈቃድ ዳቦ ያዘንባል?” አለው፡፡
ለላኛው አክቲቪስት ጋ ሄደ “ትናንትና ስለዘነበው ዳቦ ምን አስተያየት አለህ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ አክቲቪስቱ “አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት መረገጡን ነው ያየነው፣ ደግመን ደጋግመን ተናግረን ነበር፡፡ ይሄው ዛሬም ተመሳሳይ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ሕዝቡ ዳቦው እንዳልተስማማው ይሄው ጮኾ እየተናገረ ነው፣ እኛም ብዙ ጊዜ ተናግረናል”
‹‹ምንድን ነው ችግሩ?››
“ሕዝቡ የሚፈልገው በራሱ ብሔር ሲዘንብለት ነው፣ ከራሱ ብሔር ውጪ በሆነ ሰው የዘነበ ዳቦ እንደማይስማማው እየተናገረ ነው፡፡ ትንሽ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂው ዳቦ አዝናቢ ነኝ ባዩ መሪ ነው የሚሆነው”
ጋዜጠኛው ወደ አንድ ታዋቂ ሰዓሊ ጋ ሄደ፣ ቃለ ምልልስ ሊያደርግለት፡፡
ጠየቀ፡- “ትናንትና ንጉሱ ቱራ-ኦሬ ያዘነበው ዳቦ ከ150 ዓመታት በፊት ንጉሱ ታኩማ ካዘነበው ዳቦ ጋር ያለው ትስስር ምንድን ነው?
ሰዓሊው “አጼ ታኩማ ያዘነበው ዳቦ ሳይሆን ጥይት ነው”
ጋዜጠኛው “ግን እኮ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የታርክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ታመነ ‹የኢትዮጵያ ታርክ፡ ከአጼ ኃይለማሪያም እስከ ታኩማ› በሚለው መጽሐፋቸው አጼ ታኩማ ዳቦ እንዳዘነበና ልክ እንደ ዛሬው ሕዝቡን አብልቶ እንዳስደሰታቸው ጽፈዋል፡፡
ሰዓሊው ተናደደ፡፡ ቀኝ እጁን ቦክስ ጨብጦ የእግራ እጁን መዳፍ እየደበደበ “ይኸ ንጉስ እኮ ነው የሕዝባችንን ጆሮ የቆረጠው” እያለ በንደት ያወራ ጀመረ፡፡
ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ፡- ‹‹በዚያን ጊዜ የነበረው ሕዝብ ዳቦ ስለበላ ንጉሱን ለማምለክ ተሰብስቦ ነበር፤ ንጉሱ አምላክ መስሏቸው፡፡ ይህንን የተመለከተው ንጉስ ማማ ላይ ወጥቶ ‹‹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ስማኝ፣ ፈጣሪ በሰጠኝ ጥበብ ለሚወደውና ለሚወደኝ ሕዝቤ ዳቦ ከሰማይ ባዘንብ አምላክ ነው እያልክ ለኔ የማይገባኝን ክብር እየሰጠህ ከማምነው ፈጣሪ ልታጣልኝ እንደሆነ ሰምቻለሁ፣ ከእንግዲህ በኋላ እንደወትሮው ሁሉ ወደ እውነተኛ ፈጣሪህ ልመናህን ማድረስ ትተህ ወደ እኔ ብትለምን ማሪያምን ትጣላኛለህ” ብለው አዋጅ እንዳስነገሩ በታርክ ሰምተናል፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ሕዝብ ንጉሱን ከወደደ አንት ለምን ትጠላዋለህ?
ሰዓሊው “ይኸ የነሱ ታሪክ ነው፣ እኛ ግን የምናውቀው ጆሮአችንን መቊረጡን ነው”