ደስታ ፍለጋ

ደስታ ፍለጋ

Search for Happiness

Search for Happiness

ሰው ሁሉ ደስታን ይፈልጋል፡፡ በተለይ አሁን ያለንበት ዘመን ለደስታ ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ የመጠጥ ፋብሪካዎች እንደ ጉድ መፈልፈል፣ የቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ብዛት፣ ከልክ ያለፈ ገንዘብ አፍቃሪነት፣ ታዋቂነት፣ ሥልጣን፣ ወሲብ፣ ቪላ ቤቶችን መገንባት ወዘተ… ደስታ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች ይመስሉኛል፡፡ ዓለም ሁሉ ደስታን ይፈልጋል፡፡ ግና ደስታ እንደት ማግኘት ይቻላል?

ኑሮ በፈረቃ ነው፤ ባንድ ወቅት በሆስፒታል አልጋ ላይ ተንጋልሎ ከሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠ ሰው ዛሬ ያን ሁሉ ረስቶ በዳንኪራ ቤት ሊገኝ ይችላል፡፡ ትናንት ጭፈራ ቤት ዛሬ ሆስፒታል፡፡ ይህንን ባሰብኩ ጊዜ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የበሽታ መልካም ጎኑ ታየኝ፡፡ በሽታ ከገባንበት የሕይወት ውጥረት ትንሽ ረገብ ያደርገናል፡፡ ኑሮ ማለት ሆድ ለመሙላት ብቻ መባከን ነው ያለው ማን ነው? ስለ ሕይወታችን ንጽሕናም እንድናስብ ያስፈልገናል፡፡ በተሳሳተ መንገድ ላይ ሆነን ከሆነም እንደገና ራሳችንን እንድናስተካከል ዕድል ይሰጠናል፡፡ ምናልባት ስቃይ ባይኖር ደስታ ራሱ በሚገባ ለማጣጣም እንቸገር ይሆናል፡፡ ደስታ ምን እንሆነ፣ ሲገኝም እንዴት ማጣጣም እንዳለብን ለማወቅ በቅድሚያ ስቃይን መረዳት አስፈላጊ ሳይሆን አይቅርም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጭፈራ ቤቶች ጎራ የምንለው ስቃዮቻችንን ለጊዜውም ቢሆን ለመሸሽ ይመስለኛል፡፡ ጭፈራና አልኮል ለጊዜውም ቢሆን የምንኖርበትን ዓለም ያስረሳናል፣ በሽታ ደግሞ ለሕይወት ዋጋ እንድንሰጥ ያስገድደናል፡፡ ለዚህ ነው ሶቅራጥስ፥-

 “ይሄ ደስታ ተብሎ በአብዛኛው የሚጠቀሰው ስሜት ምን ገራሚ የሆነ ነገር ነው! በተቃራኒው ከሚገለጸው ስቃይ ጋር ምን ያህል ጎን ለጎን ተያይዘው እንደሚጓዙ የሚያስገርም ነው” [1]

ያለው፡፡ ሶቅራጥስ የደስታ ስሜት ያጣጣመው እግሩ ላይ ታስሮ ሲያሰቃየው የነበረው እግረ-ሙቅ ከተፈታለት በኋላ ነው፡፡ የጤንነት ዋጋ የምገባን ታመን ከዳንን በኋላ ነው፡፡ እንደ ሶቅራጥስ ዐሳብ ደስታና ስቃይ አንዱ የሌላው ተጎታች ነው፡፡ ደስታን ለማግኘት ብዙ ርቀት ስትሄድ በተጓዳኝ ስቃይንም ታገኛለሁ ማለት ነው፡፡ ሁለቱም ግን በአንድ ጊዜ ላይሰሙ ይችላሉ፡፡

“ለሰው በአንድ ጊዜ ሁለቱም አይሰሙም፣ ሆኖም ግን አንደኛውን አሳድገህ ስትይዘው ሁልጊዜ ሌላኛውንም በተጓዳኝ ለማግኘት ትቃረባለህ በአንድ ራስ ስር ሁለት አካላት ተጣብቀው እንደሚገኙ ማለት ነው፡፡”

በሌላ ጎን ደግሞ ስናየው፣ የሥጋ ደስታ የመንፈስ ቁዛሜን ያስከትላል፡፡ ለዚህ ነው መንፈሳዊ አባቶች ለሥጋዊ ተድላ ራሳቸውን ከመስጠት ይልቅ መንፈሳቸውን ማስደሰት ሥጋቸውን የሚያጎሳቆሉት፡፡

ለአንዳንዶቹ ግን ነፍስን ለማስደሰት ሲባል ሥጋን ማጎሳቆል ሌላ ሥቃይ ያመጣል ብለው ስለሚያስቡ ልኬኛ ኑሮን ይመክራለሁ፡፡

ለምሳሌ፡-

ሲድሃርታ ጉተማ (ቡድሃ)

በምቾት ከተከበበ ሕይወቱ ወጥቶ ለእውነትኛ ደስታ ፍለጋ እንዲወጣ ያስገደደው የሰው ልጆች ሁሉ እጣ ፈንታ የሆነው እርጅና፣ ሕመምና ሞትን በማየት ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ወደ ውጪ ሳይወጣ እዚያው በቤተ መንግሥት በምቾት ለማጠር ቢሞክሩትም አንድ ቀን ወጥቶ ዓለም ውስጥ ያለውን ስቃይ ለማየት በቃ፡፡ ብዙ ከተንከራተተ በኋላ በዚህ ስቃይ በተሞላችው ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚገባ መፍትሄ አግኝቻለሁ በማለት የራሱን አስተምህሮ ይጀምረና በዚህም ቡደህዝም የሚባል ሃይማኖት ይመሠረታል፡፡

በዓለም ላይ ብዙ ተከታይ ካላቸው ሃይማኖቶች መካከል አንዱ የቡድህዝም ሃይማኖት ነው፡፡ በሕንድ ውስጥ የተጀምሮ በእስያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት የቆየው ይህ ሃይማኖት እንደ ክርስቲናና እስልምና ተልዕኳዊ ሃይማኖት[2] (Missionary Religion) በመሆኑ ወደ ተለያዩ የዓለም ማዕዘናት ሊሰራጭ ችሏል፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን የዓለም ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ወደ ቡድህዝም ሃይሞናት እየተሳበ ይገኛል[3]፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ከ400 እስኬ 500 ሚሊዮን የቡድሃ እምነት ተከታዮች ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

ቡድህዝንም ከክርስቲና ወይም ከእስልምና ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ከሰው መረዳት በላይ የሆነ፣ ራሱን የቻለና አምልኮ የሚፈልግ አምላክ አለመኖሩ ነው፡፡ የሃይማኖቱ መሥራች (ቡድሃ) ራሱ የሃይማኖቱ ተከታዮቹ የሚያምልኩት አምላክ(አማልክት) ስለመኖሩ ወይም ስላለመኖሩ ያስተማረው ነገር የለም፡፡ በአንድ ውቅት ላይ ስለ አምላክ መኖር ከደቀመዝሙሮቹ የቀረበለትን ጥያቄ በዝምታ ለማለፍ ሞከረ፡፡ ጫና ሲፈጥሩበት የሚከተለውን ዘወርዋራ ምላሽ ይሰጣቸዋል፤

በሆድ ቁርጠት በሚትሰቃይበት ጊዜ ሕመሙን በማስታገስ ላይ ነው ወይስ ሐኪም የሰጠውን የሕክምና ትዕዛዝ በመመራመር ላይ ነው ትኩረት የምታደርገው? አምላክ ኖረ አልኖረ የእኔም የእናንተም ጉዳይ አይደለም፣ ጉዳያችን በዓለም ውስጥ ያለውን ስቃይ ማስወገድ ነው[4]

ከዚህ የተነሣ ቡድህዝም በዚህ ዓለም ላይ የሚከሰት ማንኛውም ክፉም ሆነ በጎ ነገር የሚወቅሰውም ሆነ የሚያመሰግነው ልዩ አምላክ የለም፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ የሰው ልጆች ሁሉ መሻት የሆነው ከአምላክ(አማልክት) እርዳታን የመሻት ስሜትን ሙሉ በሙሉ ዜሮ ያደርገዋል፡፡ በእኛ ላይ የመጣ መከራ ሁሉ በድክሜታችን ወይም በራሳችን ሥራ (Karma) ምክንያት እኛው በራሳችን ላይ ያመጣነው መዘዝ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ባጭሩ ቡድህዝም በድካማችን ጊዜ እንድረዳን የምንማጸነው አምላክ አያሳየንም፣ ወይም የ“እርዳታ ተስፋ” አይሰጥም ማለት ይቻላል፡፡

“Be ye to yourselves your own light, your own refuge, seek no other refuge”[5] ቡድሃ

የቡዳ ሃይማኖተ አስተምህሮ በአራት መሠረታዊ የእውነት ምሶሶዎች ላይ የተገነባ ነው፡፡

  1. በዓለም ላይ ስቃይ(dukkha) የመኖሩ እውነታ
  2. በዓለም ያለው ስቃይ መንስኤ
  3. ከዚህ ስቃይ ነፃ የምንወጣበት ደረጃ (Nirvana)
  4. ነፃነቱን የምንቀዳጅባቸው ስምንት መንገዶች

ቡዳ ከገባንበት መከራ ወይም ስቃይ መውጣት የምንችልባቸው ስምንት መንገዶች (Eight-Fold) የድህነት (ራስን የማዳን) መንገዶችን አበጅቷል፡፡ እነዚህ መንገዶች በሌላ እሳቤ በመከራ እራስን በማጎሳቆልና የዚህ ዓለም ተድላ ብቻ በመጎምጀት መካከል ያለ ልኬኛ መንገድ (“Middle Path”) ነው፡፡ ይህ ማለት ሕይወት ስለት ባላቸው ሁለት ጫፎች መካከል የሚትወዛወዝ ፔንዱሌም ነች፣ ወደ አንደኛው ጫፍ ስታመዝን ስለቱ ስለምወጋት በመካከል ላይ ሚዛን ጠብቆ መቆየት ብቸኛ የመዳን መንገድ ይሆናል፡፡

ቡድሃ የጠቆማቸው እራስን የማዳን ስምንቱ መንገዶች እንደሚከተሉት ናቸው፡፡

ትክክለኛ፡

  1. ንግግር(ካለመታመን፣ ከሀሜት፣ ክፉ ቃላትን ከመጠቀምና ከከንቱ ንግግሮች እራስን መቆጠብ)
  2. ድርጊት (ከግድጣ፣ ስርቆትና ከወሲባዊ አፈንጋጭነት መቆጠብ)
  3. ኑሮ(የሌሎች ፍጥረታትን ሕይወት የማያውክ)
  4. ጥረት(ክፉ አስተሳሰብን ማስወገድ/ማሸነፍ፣ ደግ ደጉን ማነሳሳትና ማስቀጠል)
  5. ግንዛቤ(ለእያንዳንዱ የሰውነት ስሜቶች ትኩረት መስጠት)
  6. ትኩረት(በሆነ ዕቃ ላይ በማተኮር ጥልቅ ተመስጦአዊ ዓለም ውስጥ መግባት)
  7. እይታ( አራቱን እውነታዎች መረዳት)
  8. ሐሳብ(ከክፉ ፈቃድ፣ ምኞት፣ ጭካኔና እውነተኛ ካለመሆን እራስን መቆጠብ)[6]

የሚሉት ከስቃይ ሊያላቅቁን የሚችሉ የመዳኛ መንገዶች ናቸው፡፡ ስለዚህ በቡድህዝም አንድ ሰው ደስተኛ ለመሆን ከፈለገ የዚህን ዓለም ቁሳዊ ሀብቶችን ከመጎመጀትና ሙሉ በሙሉ የብህትውና ሕይወት ውስጥ ከመግባት ይልቅ መካከለኛ (“Middle Path”) መምረጥ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ሁለቱም ጽንፎች ደስታችንን የሚዘርፉ ወንበዴዎች ናቸው፡፡

አርስጣጣሊስ

ከዛሬ 2300 ዓመታት በፊት ስለ ደስታ ያቀረበው ጥያቄ፡- “What is the ultimate purpose of human existence?” የሚል ነበር፡፡ መልሱ የሰው ልጅ የመጨረሻ ግቡ በሕይወቱ ደስታን ማግኘት ነው፡፡ ገንዘብ፣ መዝናናት፣ መልካም ስምና የመሳሰሉ ቁሳዊ ሀብቶች ሁሉ የሰው ልጅ የመጨረሻ ግብ ወደሆነው ደስታ መውሰድ እንጂ በራሳቸው ግቦች አይደሉም፡፡ ደስታ የሕወት ግብ እንደመሆኑ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠፋ አይደም፡፡ እንደ ቡድሃ አርስቶትልም ደስታ ለማግኘት መካከለኛ መንገድ (Mean) አስፈላጊ መሆኑን ያምናል፤ በለየለት ድህነትና ከበቂ በላይ በማግበስበስ መካከል ያለ ልኬኛ መንገድ ለደስተኛ ሕይወት ያበቃል፡፡

ሌሎች እነ እፒኩረስ ያሉ ፈላስፎችም ቢሆን ደስታ ለማግኘት ብዙ ከማግበስበስ ይልቅ በትናንሽ ነገሮች ራስን ማስደሰት ይቻላለ ነው የሚሉት፡፡ የእፒኩረስ ትልቁ የደስት ምንጭ ያለው በትንሽ ነገር መርካት ሚለው ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ባለህ ትንሹ ነገር ከረካህ ብዙ ቅይማት አይደርስብህም፣ ተቃራኒው እውነት ይሆናል፡፡ ብዙ ውድ ነገሮች ካግበሰበስክ በምታጣቸው ጊዜ የበለጠ ያበሳጨኻል/ያሳምምሃል፡፡ ሙሉ በሙሉ ማጣትም እንደዚሁ ያሳምማል፡፡

ሐዋሪያው ጳውሎስ

ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም “…የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።” ይላል፡፡ ሐዋሪያው ያለፈበት ሕይወት ተስፋ የሚያስቆርጥና ደስታን የሚዘርፍ ቢሆንም እሱ ግን “ደስተኛ ነኝ” ይላል።ስለዚህ ደስታ ከውጪ በሚመጡ መልካም ነገሮች ላይ ብዙም እንደማይመሰረት ያስተምረናል፡፡

ስለዚህ ደስተኛ መሆነ የሚፈልግ ሰው እውነተኛ ደስታ የሚገኝበትን መንገድ አብሮ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በተለመደው ግንዛቤ በፈንጠዝያ ውስጥ ደስታ አገኛለሁ ብሎ የበለጠ ደስተኛ ወዳልሆነ ኑሮ እንዳይዘፈቁ መጠንቀቅ ያስልጋል፡፡ ምድር በስቃየ የተሞላች ናትና እራሴን ለማርካት/ለማስደስት ወደ ፈንጠዝያ መግባት አለብኝ የሚል ሰው በተቃራኒው በሌላ ጫፍ ወዳለው ስህተት ይወድቃል፡፡ አርጣጣሊስ “ከልክ በላይ ማረም” (over correction) የሚለው ነው፡፡ ከአንዱ ጽንፈኝነት ወደ ሌላኛው ጽንፈኝነት እንደማለት ነው፡፡ ከሥጋ ስቃይ (አካላዊ ሕመም) ለመሸሽ ወደ ነፍስ ህመም መሸጋገር እንዳይሆን መጠንቀቅ፤ ሁለቱ የሕይወት ገጽታዎች የሥጋ ፈንጠዝያና የነፍስ ህመም ወይስ ዘላቂ ደስታ ለመጎናጽፍ ሚዛናዊ ሕይወት መምራት?

የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና!

[1] ስንታየሁ ዘርዓብሩክ ገጽ 60

[2] David A. Brown, A Gude to Relegions, TEF Study Guide 12 1980, p-123

[3] Shi, Y. (2016) Mind Is Reality: Buddhism Is Not a Pessimistic Religion. Open Journal of Social Sciences, 4, 28-38.

[4] Comparative study of the cocept of God in Islam and Buddhism

[5]William Paton, Jesus Christ and the world Religion, 1947, London

[6] David A. Brown፣ A Gude to Relegions

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *