የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊዮን መድረሱ ተገለጸ

የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊዮን መድረሱ ተገለጸ

የአለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊየን መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኛ ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ አድርጓል። የዓለማችን ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን መድረሱ የተገለጸው የዛሬ 11 አመት ገደማ ነበር።

የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 8 ቢሊዮን የመድረሳችን ዜና ባበሰሩበት ወቅት፣ “8 ቢሊየን መድረሳችን ስናበስር ብዝሃነት እና ዕድገታችንን ልናከብር ይገባል፤ ሁላችንም የሰው ልጆች ለምድራችን ሃላፊነትን መጋራት አለብን” ብለዋል።

የተመድ ትንበያ እንደሚያሳየው፥ የአለም ህዝብ ቁጥር በ2030 8 ነጥብ 5 ቢሊየን፣ በ2050 ደግሞ 9 ነጥብ 7 ቢሊየን ይሆናል። በ22ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ – ማለትም በ2100 ደግሞ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ይደርሳል።

ቀጣይ 1 ቢሊየን ህዝብ ለማግኘት 15 አመታትን መጠበቅ ያስፈልጋል ተብሏል። በሌላ አገላለጽ በፈረንጆቹ 2037፣ 9 ቢሊየን እንደርሳለን። ይህም የዕድገት ምጣኔው እየቀነሰ መሄዱ እንደማይቀር ያመላክታል ተብሏል።

ከአለማችን አህጉራት እስያ በርካታ ህዝብ የሚኖርባት አህጉር ሆና የምትቀጥል ሲሆን፣ ምስራቅና የደቡብ ምስራቅ እስያ አገራት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ ይኖርባቸዋል። ይህም የምድራችንን 29 በመቶ የህዝብ ቁጥርን ይይዛል። የመካከለኛው እና ደቡባዊ እስያም አገራትም፣ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ሰዎች እንደሚኖሩባቸው ተገልጿል።

ቻይና እና ህንድ ብቻ በ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ገደማ የህዝብ ቁጥር በመያዝ ከዓለማችን የህዝብ ቁጥር 17 ከመቶውን ይዘዋል።የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ እንደሚያሳየው፣ ህንድ በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት ቻይናን በመብለጥ በህዝብ ቁጥር ቀዳሚውን ደረጃ ትይዛለች ተብሎ ይጠበቃል።

ምድራችን እስከ ፈረንጆቹ 2050 ከምታስመዘግበው የህዝብ ብዛት ግማሹ ከስምንት ሃገራት የሚመነጭ መሆኑም ተመላክቷል። ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ፊሊፒንስ እና ታንዛኒያ ናቸው ፈጣን እድገት ያስመዘግባሉ የተባሉት።

የህዝብ ቁጥር ዕድገቱ አማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ መጨመር ጋር የተያያዘ ነው። በ2019 አለም አቀፍ አማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ 72 ነጥብ 8 አመት መድረሱ ይታወሳል። ይህም በ1990 ከነበረበት፣ የ9 አመታት እድገት አሳይቷል።

የሞት ምጣኔው እየቀነሰ፣ በ2050 አማካይ በህይወት የመቆያ እድሜ በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 77 ነጥብ 2 አመት ከፍ እንደሚል፣ የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል።አለም አቀፋዊ አማካይ እድሜው ለሴቶች 73 ነጥብ 8 አመት ለወንዶች ደግሞ 68 ነጥብ 4 አመት ነው።

የመውለድ ምጣኔው ግን እየቀነሰ ተብሏል ነው። በ1950ዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በአማካይ 5 ልጆችን ይወልዱ የነበረ ሲሆን፣ በ2019 ግን አማካዩ ወደ 2 ነጥብ 3 ልጆች ዝቅ ብሏል። ይሄው አማካይ በ2050 ወደ 2 ነጥብ 1 እንደሚወርድ ተገምቷል። የውልደት ምጣኔው እየቀነሰ ቢሄድም በህይወት የመቆያ አማካይ ዕድሜ እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ከ15 አመት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ 9 ቢሊየን እንደርሳለን ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *