የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱ ተገለጸ

የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱ ተገለጸ

የወንዶች የዘር ፍሬ ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

ለሰው ልጅ መጸነስ ዋነኛ መሰረት የሆነው የወንዶች የዘር ፍሬ ወይም ስፐርም ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ሳይንቲስቶች ገልጸዋል።

አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው (ወንድ) በአማካኝ በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ከ20 እስከ 150 ሚሊዮን  በሚሊ ሊትር የዘርፍሬ የሚረጭ ሲሆን፣ እርግዝና ለመፍጠር ግን ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ሚሊ ሊትር የዘር ፍሬ በቂ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ያለው የወንድ የዘር ፍሬ መጠን በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱን ዩሮ ኒውስ ተመራማሪዎችን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።

ይህ ጥናት በ53 የዓለማችን ሀገራት ላይ ባሉ ከ53 ሺህ በላይ ወንዶች ላይ የተደረገ ሲሆን፣ የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን ከ100 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ ቀንሷል ብሏል።

በተለይም በደቡብ አሜሪካ፣ እስያ እና አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን መቀነሱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና አውስትራሊያ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ በጥናት ተረጋግጦ እንደነበርም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

ይህ የወንድ የዘር ፍሬ መቀነስ በዚሁ ከቀጠለ ጥንዶች ጽንስ ለመፍጠር ወይም ልጅ ለመውለድ የግድ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

ይህንን ጥናት በሂብሪው ዩንቨርሲቲ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሃጋይ ለቪን የተመራ ሲሆን፣ “የወንዶች የዘር ፍሬ መቀነስ በሰው ልጆች ህልውና ላይ የተደቀነ በእጃችን ላይ ያለ ችግር ነው” ብለዋል።

የዚህ ጥናት ቡድን አባል የሆኑት በኒዮርክ ዩንቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሻና ስዋን በበኩላቸው፣ የወንዶች የዘር ፍሬ ቁጥር መቀነስ ጉዳይ ከዚህ በፊት በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ብቻ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን ችግሩ በሌሎች አህጉራት ላይም መከሰቱን ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱን የገለጹት ፕሮፌሰር ሻና፣ ከፈረንጆቹ 1973 እስከ 2018 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ የአንድ ወንድ አማካኝ የዘር ፍሬ መጠን በ1 ነጥብ 2 በመቶ ሲቀንስ፣ ከ2000 ጀምሮ ደግሞ መጠኑ በየዓመቱ በ2 ነጥብ 6 በመቶ እየቀነሰ ነውም ብለዋል።

በመሆኑም የዓለማችን ማህበረሰብ ልክ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ሁሉ የወንዶች የዘር ፍሬ መቀነስን አምኖ ለመፍትሄው መስራት እንደሚገባም ፕሮፌሰር ሻን ተናግረዋል።

አሁን ላይ አንድ ጤነኛ ሰው በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የሚረጨው የዘር ፍሬ መጠን ከ104 ሚሊዮን በሚሊ ሊትር ወደ 49 ሚሊዮን በሚሊ ሊትር ዝቅ እንዳለ፣ ይሄው ጥናት አረጋግጧል ተብሏል።

ይሁንና ለወንዶች የዘር ፍሬ መጠን መቀነስ ምክንያቶቹ በጥናቱ አልተገለጹም። ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጽኑ ህመሞች መስፋፋት፣ አካባቢ በካይ ኬሚካሎች እና የኑሮ ዘይቤ ለውጥ ዋነኛ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *