
የኮንሶ ልማት ማህበር በዓይነቱ ለየት ያለና ለድርጅቱ ሥራ የሚሆኑ ቢሮዎችንና ለአካባቢው ማህበረሰብ ልዩ ልዩ ግልጋሎቶችን የሚሰጡ ተቋማትን በውስጡ መያዝ የሚችል ግንባታ እያቀደ መሆኑን የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽብሩ ሲካ ለኮንሶ ዜና አስታወቁ።
የግንባታው ዲዛይን መጠናቀቁንና ጠቅላላ ወጪው በመጠናት ላይ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በታቀደው መሠረት ግንባታው ሲከናወን ከኮንሶ ልማት ማህበር ቢሮዎች በተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾች፣ የእንተርኔት ተግባቦት ማዕከል፣ የንባብ ቦታዎች፣ መናፈሻዎችና የመዋኛ ገንዳዎች፣ የሠርግና ሌሎች መርሃ ግብሮች ማከናወኛና ካፍቴሪያዎችም ይኖሩታል ብለዋል።

የግንባታው ዓላማ፣ የልማት ማህበሩን ሥራ በተጨማሪ የውስጥ ገቢዎች ለመደገፍ ነው የተባለ ሲሆን፣ የአካባቢው ኅብረሰተስብ አማራጭ የመናፈሻ አገልግሎቶችን ማቅረብ መሆኑ ታውቋል።
ይህ ሁለገብ ግንባታ የታሰበው፣ የኮንሶ ልማት ማህበር ጽ/ቤት ያለበትን ቤትን ቦታ ጨምሮ ልማት ማህበሩ የሚያስተዳድራቸው ሌሎች ተቋማት ያሉበት መሬት የሚጨምር ሲሆን፣ የተለያዩ ቅርጽና መጠን ያላቸው ብዙ ህንጻዎች ይኖሩታል።
አጠቃላይ ግንባታው ምን ያህል ወጪ እንደሚያወጣ በጥናት ከታወቀ በኋላ፣ ልማት ማህበሩ ይህ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ የግንባታውን ወጪ ለመሸፈን ከተለያዩ አካላት ገቢ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል። ከእነዚህም አካላት መካከል የተለያዩ የኮንሶ ማህበረሰብ አካላት፣ መንግሥት፣ ባንኮች፣ የተለያዩ ድርጅቶችና ልማት ወዳድ ዜጎች ይገኙበታል። ይህ ኮንሶ ዜና ነው።