
አብዮት ሳጎያ
ከሰሞኑ በኮንሶ ሚዲያ ስለ ኮንሰኛ ቋንቋ የውይይት ሃሳቦች በተለያዩ ወንድሞች እየቀረቡ ነው። እኔ በበኩሌ በዚሁ ሚዲያ ድህረ-ገጽ ላይ የተለጠፉትን ወደ አራት የሚደርሱ ጦማሮችን በፍጥነት ለማምበብ ሞክሪያለሁ። ከዚህ በፊት ስለ ኮንሰኛ ቋንቋ የተደረጉ ወይይቶችም ሆነ በሌላ መልክ የቀረቡ ሃሳቦችን የማየት ዕድሉ አልገጠመኝም። ነገር ግን እኔ በአንድ ወቅት (በቀድሞ የኮንሶ ልዩ ወረዳ) በባአይዴ እና በሶሮቦ ቀበሌያት ከ1 – 4ኛ ክፍል መምህር ሆኜ በገጠራማው የኮንሶ አካባቢ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኮንሰኛ የሆኑትን ተማሪዎች በአማርኛ አስተምሪያለሁ። ምንም እንኳን የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ልምዴን ማካፈል ባይሆንም፤ በኮንሰኛ ቋንቋ ላይ በተነሱት ሃሳቦች ላይ የምሰጠውን ግሌ አስተያየት ምን እንደቀረጸው (what informed my conclusion) ያመላክትልኛል ብዬ አምናለሁ። እስካሁን ባለው ውይይት ደግሞ ማንም ኮንሰኛ ቋንቋ ወደ ዘመናዊ ትምህርት በመግባቱ ላይ ልዩ አቋም ያሳየ የለም።
በአጭሩ ስለኮንሰኛ ቋንቋ ጉዳይ እስከ አሁን ባለው ደረጃ ሁለት መሰረታዊ ሙግቶች አሉ። እያንዳንዱ ሙግት የየራሱን ጠንካራ ናቸው ያላቸውን መሰረታዊ ምክንያቶች አቅርቧል። ሙግት (1)፡ የኮንሰኛ ቋንቋ ከ1ኛ – 6ኛ ክፍል የማስተማሪያ ቋንቋ (instructional language) ይደረግ። ሙግት (2)፡ የኮንሰኛ ቋንቋ ከ1ኛ – 12ኛ ክፍል እንደ አንድ ተጨማሪ የቋንቋ ትምህርት ይሰጥ።
ከዚህ ጋር በተያያዠነት የተነሳው ጉዳይ ደግሞ ቋንቋው የትኛውን ፊዴላት ይጠቀም የሚለው ሲሆን ሙግቱ አሁንም በሁለት ጎራ ተከፍሏል። በአንድ በኩል የሳቢያን ፊዴላት ቀዳሚ የኮንሰኛ ቋንቋ የመሰረታዊ ትርጉም ስራ በተለይ በመካነ ኢየሱሰ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት የተሰራበት ጅማሮ ስራ ስላለ እሱኑ ማስቀጠል እና በእርሱ ላይ መገንባት ተገቢ ነው የሚል ሙጉት ሲሆን። በሌላ በኩል ደግሞ ከኮንሰኛ ቋንቋ ባህሪ እና ቅርጽ አኳያ ምቹ የሆነው የፊዴል ዓይነት ላቲን በመሆኑ እሱን መጠቀም ተገቢ ነው የሚል ሙግት ቀርቧል።
የትኛው ፊዴል ይሁን የሚለው ሙግት ምንም እንኳ ራሱን የቻለ ወሳኝ ጉዳይ ብሆንም ያን ያህል በስፋት ትኩረት ያገኘ የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኑ የቀረበ አይመስልም። ይልቁኑ የውይይቱ አስኳል ኮንሰኛ ቋንቋ ከትምህርት ጋር ባለው ጉዳይ ላይ ነው። በእኔም አስተያየት የፊዴል ጉዳይ የዘርፉን ሙሁራን የሚመለከት ራሱን የቻለ ሙያዊ ማብራሪያ እና አስተያየት የሚፈልግ እንደሆነ አምናለሁ። ስለዚህ ለባለሙያዎቹ ጉዳዩን እተውና ቋንቋው ከትምህርት ጋር ባለው ጉዳይ ላይ ለተነሱት አሳቦች የግሌን አጠር ያለ አስተያየት ለማዋጣት እጥራለሁ።
እንደመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ በኮንሶ ሚዲያ ኦፊሻል ድህረ-ገጽ ላይ ለንባብ ከቀረቡት ጦማሮች፤ ከላይ የቀረበውን ሙግት (1)ን ደግፈው የተሟገቱት ወንድሞቻችን ያቬሎ ናታየ እና ኩሴ ጉያሎ ናቸው። ወንድም ያቬሎ «የአፍ መፍቻ ቋንቋና ትምህርት-የኮነሰኛ ጉዳይ» በሚል ርዕስ በጉዳዩ ላይ የተደራጀ፣ በመረጃ የተደገፈ፣ ዘለግ ያለ እና የኮንሰኛ ቋንቋ ትርጉም ስራ ታሪካዊ ትንታነን ያካተተ ጽሑፍ አስነብቧል። የያቨሎ ጽሑፍ ብዙ ነገሮችን አጥርቶ ለማሳየት የጣረ እንደመሆኑ በስፋት መነበብ አለበት የሚል አስተያየት አለኝ። ለምሳሌ፦ የኮንሶ ዞን ት/ት መምሪያ የኮንሰኛን ቋንቋ እንዴት ወደ ዘመናዊ ትምህርት አስገብቶ ለመጠቀም እንዳቀደ በዝርዝር ለማመላከት ጥረት አድርጓል።
(1ኛ). ከ1ኛ – 6ኛ ክፍል ሁሉም የት/ት ዓይነት በኮንሰኛ ቋንቋ ይሰጣል(instructional language)። ኮንሰኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ እንደ አንድ የቋንቋ ትምህርት (subjects) ይሰጣሉ። ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ አማርኛ ቋንቋ ተጨማሪ ትምህርት (subject) ሆኖ ይሰጣል።
(2ኛ). ለከተማ አደግ (አማርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻቸው ለሆኑ) ደግሞ፤ ከ1ኛ – 6ኛ ክፍል ሁሉም የት/ት ዓይነት በአማርኛ ቋንቋ መሰጠቱን ይቀጥላል። ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ የኮንሰኛ ቋንቋ እንደ አንድ የት/ት ዓይነት ይሰጣል።
(3ኛ). ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ሁሉም የት/ት ዓይነት በእንግሊዝኛ ይሰጣል (instructional language)። አማርኛ፣ ኮንሰኛ እና እንግሊዝኛ ደግሞ እንደ አንድ የቋንቋ ት/ት (subjects) ሆነው ይሰጣሉ።
(4ኛ). ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ሌላ አራተኛ የቋንቋ ት/ት (subject) መርጦ የመማር ዕድል አለ።
ይህ ከላይ የተዘረዘረው አካሄድ የኮንሰኛን ቋንቋ የማስተማሪያ ቋንቋ አድርጎ በመጠቀም ሂዴት ውስጥ የቋንቋው ተጠቃሚም ሆነ ቋንቋውን በሚገባ ታሳብ ያደረገ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። የኮንሰኛ ቋንቋን የማስተማሪያ ቋንቋ አድርጎ መጠቀም ስታሰብ፤ ለአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ቦታ ያልተሰጠ አስመስሎ ሙግት ለሚያነሱ ወገኖች ይህ ጥሩ ማሳያ ነው። ከ1ኛ – 6ኛ ክፍል አማርኛም እንግሊዝኛም እየተሰጠ ከሆነ፣ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ሁሉም የት/ት ዓይነት በእንግሊዝኛ የምሰጥ (instructional language) እና አማርኛ፣ ኮንሰኛ እና እግሊዝኛ በቋንቋ ት/ትነት (subjects) የሚቀጥሉ ከሆነ፤ በምን መልኩ ነው ታዳጊዎችን ከአገር አቀፍና ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያግዳቸው? ከተማ አደግ የሆኑ ተማሪዎችን ታሳቢ ያደረገ አማራጭ መቅረቡስ ቋንቋውን ዝም ብሎ ለፖሌትካዊ ግብ ወደ ማስተማሪያ ቋንቋነት ለማስገባት የተደረገ ጉዳይ አለመሆኑን አያሳብቅም ወይ?
በመሆኑም የኮንሰኛ ቋንቋ ከ1ኛ – 6ኛ ክፍል የማስተማሪያ ቋንቋ (instructional language) መደረጉ፤ እንደ ወንድም ታታሻ ታካየ እና ካፍትሌ ቶራይቶ ስጋት ለአማርኛ እና ለእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መዳከም ብሎም ታዳጊዎች አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አያደርግም። ምክንያቱም እየተባለ ያለው ኮንሰኛ ቋንቋ በማምጣት አማርኛ ቋንቋን እና እንግሊዝኛ ቋንቋን እናስወግድ አደለም።
እንደ መጠቅለያ
በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መማር የተማሪዎችን ንቁ ተሳትፎ፣ ፈጣን የእውቀት ሽግግርን፣ የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ማምጣቱ ልታመንበት ይገባል። መሰረት የሁሉም ነገር ቁልፍ ነው፡፡ መሰረት ስጠነክር ሁሉም ነገር ይጠነክራል። የኮንሰኛ ቋንቋን የአንደኛ ደረጃ ማስተማሪያ ቋንቋ መሆኑ አማርኛን እና እንግሊዝኛን የሚያዳክም፣ ታዳጊዎችን ደግሞ ተወዳዳሪነታቸውን የሚገታ ይሆናል የሚለው ሙግት መሰረታዊ ጉዳዮችን ያማከለ ሆኖ አላገኝሁትም። በነገራችን ላይ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ተናጋሪ የምኮነው ትምህርት ቤት ገብቶ በመማር ብቻ ከሆነ ኢትዮጵያ ትመስክር። ዋናው የትምህርት ጥራት ላይ መስራት እና በተቻለ መጠን የትምህርት ግባቶችን ማሟላት ነው። ስለ ኦሮሚያ የተሰጠው ምሳሌም ቢሆን ጉዳዩ ከኮንሰኛው ጋር በቀጥታ በምን መልኩ እንደምገናኝ ግልጽ አይደለም። እውቁ ደቡብ አፍርካዊው የነጻነት ታጋይ የነበረው ነንሰል ማንዴላ ስለቋንቋ የተናገሩትን በመጥቀስ ላብቃ።
“If you talk to a man in a language he understands, that goes to his head. If you talk to him in his own language, that goes to his heart.”
«አንድን ሰው በሚረዳው ቋንቋ ብታናግረው ወደ ጭንቅላቱ ይሄዳል። በገዛ ቋንቋው ብታናግረው ወደ ልቡ ይሄዳል።»
ልዩነቱ ይሄ ነው። ትምህርቱ ወደ ጭንቅላትም ወደ ልብም ይደርስ ዘንድ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቁልፍ ነው!! አበቃሁ።
ለቋንቋው ጥቅም ላይ መዋል “በአዎንታ” ለቀረበው ሙግት ተጨማሪ ግልፅነት ለመፍጠር ላቀረብከው ፅሑፍ አመሰግናለሁ።
ትክክል! ያቫ።