የኮንሰኛ ቋንቋ

የኮንሰኛ ቋንቋ

Kussie K. Guyalo (Kussie)

ሰሞኑ በተለያየ የግለሰብ ገጾች የመወያያ ርዕስ የሆነው የአፋ-ኮንሶ ትምህርት አሰጣጥ የተመለከቱ ግላዊ አስተያየቶች በርክተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ በቅንነት መረጃን መሠረት አድርጎ መከራከሩ በራሱ ችግር የለውም፡፡ አንዳንዱ ወገን ከዚህ በፊት ውይይት ተካሂዶበት ከስምምነት ተደርሶ የተዘጋ አጀንዳ ስለሆነ በወቅቱ ጥሪ ሲደረግላችሁ የት ነበራችሁ የሚል ገፊ ሃሳብ የሰነዘሩ እንዳሉ ነገሩን ከፋይዳውና ከጉዳቱ አንጻር ለመገምገም የሞከሩም አሉ፡፡

ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር እንዳለባቸው UNISCO ጭምር የሚያበረታታው ጉዳይ ከመሆኑም ባሻገር በተጨባጭ ምን ጥቅምና ጉዳት አለው ብሎ ማየቱ መልካም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአካባቢያችን የቅድመ ትምህርት (KG) ስላልነበረ እኔ በ1988 ዓ.ም 1ኛ ክፍል ስገባ በወቅቱ በትምህርት ቤቱ የነበሩ መምህራን አማርኛ ቋንቋ ብቻ የሚችሉ በመሆናቸው መምህራኖቹ ትምህርቱን በአግባቡ ማስተላለፍ እኛም የሚገባውን ለመረዳት ተግዳሮት ሆኖብን ነበር፡፡ በወቅቱ አስተማሪያችን የነበረችው ጥሩነሽ ፀጋዬ ትምህርቱን ለእኛ ለማስጨበጥ የዛፍ ቅጠል፣ አበባ፣ ድንጋይ፣ እንጨት፣….ወዘተ ለቃቅማ እብድ መስላ ለማስተማር የመጣችባቸው ጊዜያት አያሌ ነበር፤ተጽዕኖውም ቀላል አልነበረም፡፡ እንግዲህ የግል ገጠመኜን ለማቅረብ የሞከርኩበት ምክንያት በተለይ በአንደኛ ደረጃ በ2ኛ ቋንቋ መማር ያለው ተጽዕኖ ለማሳየት ያህል ነው፡፡

ስለዚህ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር የተማሪዎች ስነ-ልቦና ጫናን በመቀነስ በደስታ ትምህርት እንዲከታተሉ ማድረግ፣ በቀላሉ ስለሚረዱ የትምህርት ጥራት መኖሩ፣ የደጋሚዎች ቁጥር መቀነሱ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማቋረጥ ምጣኔ መቀነስ ወዘተ ፋይዳዎች ያሉት በመሆኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ፋይዳ እንዳለው ሁሉ በውጭ ቋንቋ ወይም በሌሎች ቋንቋዎች መማርም ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ ለምሣሌ፡- አድማሶችን ማስፋት (የሌላውን ባህል፣ ታሪክ፣ ወግ ማወቅ)፤ የማስታወስ ብቃት መጨመር (የውጭ ቃላትን በማስታወስ አዕምሮን ማሠራት)፤ በራስን መተማመን መጨመር (በሌሎች የአለም ሀገራት በራስ የመተማመን ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መገናኘት እና የተለያየ ድርድሮችን በቀላሉ ማካሄድ ያስችላል፤ በፍጥነት ሥራ ለማስገኘት ያስችላል)፤ የመረጃ ማከማቻ ድረ-ገጾች (ዌብሳይቶች) ብዙ ተናጋሪ ባላቸው ቋንቋዎች የተሠሩ በመሆናቸው መረጃን በቀላሉ አግኝቶ ጥናት ለማካሄድ ፈጠራ እንዲጨምር ያደርጋል፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ላይ ማሻሻያ እንድናደርግም ሊረዳን ይችላል፣ ….ወዘተ ፋይዳ አለው፡፡ በመሆኑም የአፍ መፍቻ ቋንቋም ሆነ ከአፍ መፍቻ ውጪ ያሉትን ቋንቋ መጠቀም የራሳቸው የሆነ ጥቅምና ጉድለት ያላቸው በመሆኑ አመዛዝኖ የት፣ መቼ፣ እንዴት ….ወዘተ መጠቀም እንዳለብን በጥንቃቄ መወሰንን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ከጉድለት የጸዳ ነገር ባለመኖሩ ፍጹምነትን ሳንጠብቅ ከነጉድለቱ መጀመርና በሂደት ክፍተቱን ማጥበብ ነው፡፡ ከቋንቋ ተናጋሪ ቁጥር ማነስ ጋር ተያይዞ ቋንቋው በሌሎች አካላት ዘንድ ለጥናትና ምርምር የሚውልበት ጊዜ ቅርብ ስለማይሆን ሰፊው ዓለም የሚጠቀመውን ቋንቋ ላይ ማተኮር አለብን የሚለው ሃሳብም ገዢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ የህዝብ ብዛት ኦሮሞ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል አሁን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሀገር ውስጥ ከኦሮሚኛና አማርኛ በተጨማሪ በውጭ ከእንግዚዘኛ በተጨማሪ የቻይና ቋንቋ በመደበኛነት መሰጠት ተጀምሯል፡፡

ቻይና አሁን በአለም ላይ ካላት የሳይንስና ምርምር ሥራ፣ ካላት ባህር ተሻጋሪ የንግድ ተቋማት እና በሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት የአለም የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ሚዛን ወደ እሷ እያደላ በመሆኑ የኦሮሚያ ተወላጆች ቻይንኛ በመማራቸው ነገያቸው የተሻለ ይሆናል እንጂ ተጎጂ አይሆኑም፡፡ ወደ እኛ ስንመጣም ቋንቋና ባህል ከማሳደግ አንጻር በ1ኛ ደረጃ ሁሉም ኮርሶች እንዲሁም ከተወሰነ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ ኮርስ በሁሉም ደረጃ ቢሰጥ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ተማሪዎቻችን ትምህርት ሲጨርሱ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ ሄደው መሥራት እንዲችሉ ቢቻል ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ሰፋፊ ተናጋሪ ያላቸው የሀገር ውስጥ ቋንቋ ጭምር ቢሰጣቸው ተጠቃሚ እንሆናለን እንጂ አንጎዳም፡፡ ከሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ጋር ሳይቸገሩ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚጠቅማቸው በመሆኑ የአለም ቋንቋዎችን በሰፊው መማርም ተገቢ ነው፡፡ አሁን ጉዳዪ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ተገድደን የምንገባባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ፡- በUN ተቋማት ውስጥ ለመቀጠር ቢያንስ የተቋሙ የሥራ ቋንቋ የሆኑ እንግሊዘኛ፣ አረብኛ፣ ቻይንኛ፣ ረሺኛ፣ ፈረንሳይኛና ስፓንኛ ውስጥ አንዱን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ልጆቻችን ወደፊት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ እንዲሠሩ ከፈለግን ከወዲሁ እነዚህን ቋንቋ ማስተማር አለብን ማለት ነው፡፡ የትምህርት ችሎታ እያለን ቋንቋ ባለመቻላችን ወደኋላ ሊያስቀረን አይገባም፡፡ ስለአስፈላጊነት ይህን ያህል ካልኩኝ ቋንቋ የትኛውን የፊደል ገበታ ይጠቀም የሚለው ቀጣዩ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ሀገራት በተለያየ አጋጣሚ የተለያየ የፊደል ገበታን ለትምህርት ስርዓታቸው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ መጀመሪያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የግዕዝ ፊደላትን በመጠቀም በአብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ ትምህርቶችን ስትሰጥ እንደቆየች እና በሂደት ሥልጣን ወደ አገዎ ገዥዎች ሲሸጋገር አማርኛን የቤተ-መንግሥት ቋንቋ እንዳደረጉ እንዲሁም የሚሽነሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከመንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ ሳይንሳዊ ትምህርት በውጪ ቋንቋ ጭምር መስጠት መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቱ ከግዕዝ ወደ አማርኛ እንዲሁም ወደ እንግሊዘኛ የተሸጋገረበት በጥናት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የወቅቱ የሃይማኖት ሰዎችና ሥልጣን ላይ ያሉ ሹማምንቶች ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር የቃኙት ይመስላል፡፡ የሆነው ሆኖ አሁን እኛ ይህን ወይም ይሄኛውን የፊደል ገበታ እንጠቀም ወይም አንጠቀም ለማለት በትምህርት ሂደቱ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በመገምገም ነው፡፡ አንድ የአፋ-ኮንሶ ቃል የድምጽ አወጣጥን ብቻ በመቀየር ሁለት እና ሶስት ወይም አራት ትርጉም እንዲኖረው የሚደረግ ሲሆን የአማርኛ ፊደል ደግሞ ይህንን ችግር የማይፈታ በመሆኑ ወደ ሌላ አማራጭ ማማተራችን የግድ ይሆናል፡፡ አማርኛ በተመሣሣይ ፊደል የተጻፈ ቃል ቢበዛ ጠብቆና ላልቶ በማንበብ ሁለት ትርጉም ብቻ ይሰጣል፡፡ በመሆኑም የላቲን ፊደላት የቃላት የጽምጽ አወጣጥን በመከተል አናባቢና ተነባቢን በመቀነስና በማብዛት ለእያንዳንዱ የድምጽ ጥርቅም ልዩ ጽሑፍ ለመቅረጽ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለአፋ-ኮንሶ ተመራጭ ይሆናል ባይ ነኝ፡፡ ሻሎም !!

2 Comments

  1. kandisha

    እናመሰግናለን ጥሩ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *