የኮሮና ቫይረስ የመራባት ሂደትን የሚገታ አዲስ መድሃኒት መሠራቱ ተገለጸ

የኮሮና ቫይረስ የመራባት ሂደትን የሚገታ አዲስ መድሃኒት መሠራቱ ተገለጸ

የኮሮና ቫይረስ ምስል

ከ6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የገደለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም የአለማችን አሳሳቢው ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። ዳግም የስርጭት አድማሱን ማስፋቱም፣ “አለም ከሁለት አመት በፊት ወደነበረችበት ልትመልስ ይሆን?” የሚል ስጋት እያስከተለም ይገኛል።

ለቫይረሱ መከላከያ የተዘጋጁ ክትባቶችና ከዚያም በኋላ የተሰራጩ መድሃኒቶች ውጤታማነትም አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮሩ መድሃኒቶች ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በሽታን የመከላከል አቅማቸው በተዳከመበት በአሁኑ ወቅት፣ በአሜሪካ ተመራማሪዎች አዲስ መድሃኒት ይፋ ተደርጓል።

የዳና ፋርበር የካንሰር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ያስተዋወቁት አዲሱ የኮሮና መድሃኒት፣ “ዲ ኤፍ ኮቭ 01” ተብሎ መሰየሙን ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶክተር ጎርዳን ፍሪማን አል አይን ኒውስ ለተባለ የዜና አውታር ተናግረዋል።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ፍሪማን እንደገለጹት፣ አዲሱ የኮቪድ 19 መድሃኒት የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያሳድግ ሳይሆን፣ የቫይረሱን መስፋፋት የሚገታ ነው።

የኮቪድ 19 ቫይረስ “ኤ ሲ ኢ 2” ከተሰኘው ሞሎኪዩል ማምለጥ እንደማይችልና ሞሎኪዩሉ ወደ ቫይረሱ ሲገባም የቫይረሱን የህይወት ኡደት እንደሚገታ ተማራማሪው ጨምረው ተናግረዋል። በዚህም መድኃኒቱ ቫይረሱ ደቂቅ የሰውነት ህዋሳት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ያስቆማል ብለዋል።

መድሃኒቱ በየጊዜው የሚፈጠሩ የኮቪድ 19 ዝርያዎችን ለማጥፋት እንደሚያግዝ መረጋገጡንም ነው ዶክተር ጎርደን ፍሪማን ለአል አይን ኒውስ የተናገሩት። “ዲ ኤፍ ኮቭ 01” በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለማከም ይውላል ተብሏል።

መድሃኒቱ ወረርሽኙን አስቀድሞ ለመከላከልም ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው የዳና የካንሰር ኢንስቲትዩት የምርምር ቡድን መሪው ተናግረዋል። የደም ግፊትን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሌሉትም ተጠቁሟል።

በኮሮና በተያዙ እንሰሳት ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው አዲሱ መድሃኒት፣ በቀጣይ በሰዎች ላይ ይሞክራል ተብሏል። በፈረንጆቹ 2023 ሙከራው ተጠናቆም፣ ለገበያ እንደሚውል ይጠበቃል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *