የአፍ መፍቻ ቋንቋና ትምህርት – የኮንሰኛ ጉዳይ

የአፍ መፍቻ ቋንቋና ትምህርት – የኮንሰኛ ጉዳይ

መግቢያ

ልጆች አፍ በፈቱበት ቋንቋ መሠረታዊ ነገሮችን ሲማሩ የበለጠ ግንዛቤ እንደሚጨብጡ፣ የቋንቋ ምሁራን በምርምራቸው የደረሱበትና በየጊዜው የሚናገሩት ሐቅ ነው። በተለይ ከቅድመ መደበኛ እስከ የመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያው ሳይክል ድረስ ባሉት ክፍሎች ለልጆች የሚሰጡ ትምህርቶች፣ በይዘታቸው መሠረታዊ ጉዳዮችና ክህሎቶች ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉና የተወሳሰበ የቋንቋ አጠቃቀምን የማይጠይቁ፣ ነገር ግን በቀጣይ ክፍሎች ላሉ የትምህርት ይዘቶች መሠረት የሚጥሉ ስለሆኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሆን በሚገ’ባ ይረ’ዱታል።

ሰሞኑን በኮንሶ ዞን በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላሉ ተማሪዎች “ሁሉም የትምህርት ዓይቶች በኮንስኛ ቋንቋ ይሰጣሉ” መባሉን ተከትሎ፣ በኮንሶ ምሁራን ዘንድ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። በርግጥ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሊነሳ የቻለው፣ አንዳንዶች ከአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ጋር ተያይዞ የተወሰነ ውሳኔ ስለመሰላቸው ነው። ነገር ግን በአፍ መፍቻ ቋንቋ መደበኛ ትምህርትን የመማሩ ዕቅድ የተጀመረው ቀደም ብሎ ስለነበር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰጠው ትምህርት እስከ 4ኛ ክፍል መድረሱን ከዞን ትምህር መምሪያ አካባቢ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ስለዚህ፣ ይህ ጉዳይ ከአዲሱ የትምህር ፖሊሲ ጋር አብሮ የተጀመረ ሳይሆን፣ ቀደም ብሎ ተጀምሮ በአዲሱ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለ ጉዳይ ነው።

የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በተነሳው ውይይት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆንና ለሌሎችም ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ስለሁኔታው የሚያውቀውን በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ ይሞክራል።

የኮንሰኛ ቋንቋ ጽሕፈት አጀማመር

ኮንሰኛ ቋንቋን በአማርኛ ፊደላት የመጻፉ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው በፈንጆቹ በኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ፣ በጉዳዩ ላይ የተመለከትኳቸው የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ። ሥራውም የተጀመረው ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበርና በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የጋራ ትብብር መሆኑ ይታወቃል። 

የአማርኛ ፊደላት ለኮንስኛ ቋንቋ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ፣ በ1985 አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን በሚተረጉሙት አካላት የመጀመሪያው ራስን በራስ ኮንስኛ ቋንቋ ማጥኛ አነስተኛ የጥናት መጽሐፍ ተዘጋጀ። መጽሐፉ አማርኛና ኮንስኛን ጎን ለጎን የሚያስተምር ሲሆን፣ የተማሩ የኮንሶ ልጆች በአማርኛ አነባብና በኮንስኛ ቋንቋ አነባብ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲረዱ ተብሎ የተዘጋጀ ነበር።

ምንም ፊደል ላልተማሩት ማስተማሪያ የሚሆን፣ “ፍተለ አፈ ኾንሶ /fitala afa χonso” የተባለ ማስተማሪያ መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው በ1989 አካባቢ ነበር። በዚህ የማስተማሪያ መጽሐፍ አማካይነት በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብዙዎች ፊደልን ተምረው ኮንስኛ ቋንቋን በአማርኛ ፊደላት ለማንበብ በቅተዋል።ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ቤተ ክርስቲያን ፊደል ለሚያስተምሩ መምህራን በየጊዜው ሥልጠናዎችን ሲታዘጋጅ ቆይታለች።

ብዙዎች ኮንስኛ ቋንቋን ማንበብ ከጀመሩ በኋላ፣ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኮንሰኛ ቋንቋ መዝሙር መጽሐፍ፣ እንዲሁም የታሪክ መጻሕፍት በተለያዩ ደራሲያን ተዘጋጅተው በአማርኛ ፊደላት በኮንሰኛ ቋንቋ ለንባብ በቅተዋል።

በዚህ ሁኔታ ኮንስኛ ቋንቋ የአማርኛ ፊደላትን ለጽሕፈት እየተጠቀመ በቤተክርስቲያን አካባቢ ተገድቦ ለ20 አመታት ገደማ ከቆየ በኋላ፣ በ2006 ዓ.ም አካባቢ በመንግሥት በተቋቋመ የቋንቋ ኮሚቴና በሥሩ በተቋቋመ የቋንቋ ጽሕፈት ልማት ኮሚቴ አማካይነት የቋንቋው ጽሕፈት ከቤተክርስቲያን ባለፈ በሰፊው ህዝብ ዘንድ እንዲለመድ ስለታሰበ ሥራውን ለማቅለል፣ የጽሕፈት ፊደላቱ ከአማርኛ ወደ ላቲን እንዲለወጥ ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ከሁለት አመት በኋላም የላቲኑ ፊደላት ዝግጅት ተጠናቆ በኮሚቴው ተቀባይነት አገኘ። ከዚያም በኋላ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በኮንስኛ ቋንቋ ተዘጋጅተዋል።ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የሙከራ ትግበራም መጀመሩ ከትምህርት መምሪያ አካባቢ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኮንሰኛን ለመጻፍ ከአማርኛ ወደ ላቲን ፊደል መቀየር ለምን አስፈለገ?

ኮንሰኛን ለመጻፍ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የአማርኛ ፊደል ለመቀየር ምክንያት የሆነው፣ የአማርኛ ቋንቋ ፊደላት ባህሪያትና የኮንሰኛ ቋንቋ ባህሪያት አለመጣጣም ነው።

የአማርኛ (ወይም በተለምዶ የግዕዝ) ፊደላት በባህሪያቸው ተነባቢ-አናባቢን (Consonat-vowel combination) አጣምረው የሚይዙ ናቸው። ስለዚህ የአማርኛ ቋንቋ ፊደላት እያንዳንዳቸው ክፍለ ቃልን የሚወክሉ እንጂ፣ እንደ ላቲን ፊደላት አንድን ድምጽ (ተነባቢ ወይም አናባቢ) ብቻ የሚወክሉ አይደሉም።ይህ የፈደላቱ ባህሪ ነው ሲሆን፣ ሴማዊ ቤተሰብ ለሆኑ ቋንቋዎች ጽሕፈት እጅግ አመቺ ሆነው ተገኝተዋል።

ይሁንና ከዚህ የፊደላቱ ባህሪ የተነሳ፣ ተነባቢና አናባቢ ፊደላት ላይ ለየብቻ ተግባራዊ የሚደረጉ ህግጋት ያሏቸው ቋንቋዎችን ለመጻፍ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ቋንቋውን ውስብስብና ለማንበብ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ፣ በአማርኛ ፊደላት አጻጻፍ የሚጠብቁ ተነባቢዎችንና የሚረዝሙ አናባቢዎችን መግለጽ አይቻልም። ለዚህ በእጅጉ አመቺ የሚሆኑ ፊደላት ክፍለ ቃልን የሚወክሉ ፊደላት ሳይሆኑ፣ ተነባቢንና አናባቢን እንደ ድምጽ ለየብቻ የሚወክሉ የፊደል አይነቶች ናቸው። 

በሌላ በኩል ደግሞ ኮንሰኛ ቋንቋ የምሥራቅ ኩሻዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ አባል እንደመሆኑ መጠን፣ ተነባቢና አናባቢ ድምጾች ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ የቋንቋ ህግጋት የሚስተዋሉበት ቋንቋ ነው። ይህም ማለት ከቋንቋው ባህሪ የተነሳ የሚጠብቁ ተነባቢ ድምጾችና የሚረዝሙ አናባቢ ድምጾች የሚበዙበት ቋንቋ ነው።

ኮንሰኛ ቋንቋን ለመጻፍ የአማርኛ ፊደላት ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ፣ የተነባቢ ድምጾችን መጥበቅና የአናባቢ ድምጾችን መርዘም በቀላሉ ማመልከት አይቻልም። ከዚህም የተነሳ በአማርኛ ፊደላት የተጻፈ የኮንሰኛ ቋንቋ ጽሑፍ፣ አማርኛን እንደማንበብ ቀላል አይሆንም። ይህም በቤተክርስቲያን አካባቢ ከ20 አመታት በላይ ጥቅም ላይ ከዋለው የአማርኛ ፊደላት አጠቃቀም የተገኘ ልምድ ያመለከተው ነው።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪ ምሁራን የኮንሰኛ ቋንቋን ጽሕፈት በአማርኛ ፊደላት ማድረጉ፣ አገርኛ የሆነውን የአማርኛ ፈደል ለማጎልበት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነና በአገር ውስጥ ምርት/ታሪክ እንደመኩራትም ነው ይላሉ። የላቲን ፊደል መጠቀምን ደግሞ የራስን ትቶ የባዕድ አገርን ፊደል/ምርት/ታሪክ እንደማድነቅ ይቆጥሩታል። በእነዚህ ምሁራን አስተያየት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ቋንቋዎች ሁሉ አገርኛ በሆነው የአማርኛ (በተለምዶ ግዕዝ) ፊደላት ሊጻፉ ይገባል እንጂ በባዕድ አገር ፊደላት ሊሆን አይገባም። እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ኮንሰኛን ወይም የሌሎች ብሔር ቋንቋዎችን በባዕድ አገር ፊደላት ከመጻፍ ይልቅ፣ አገርኛው ፊደላት ላይ በጥናት አንዳንድ ማሻሻዎችን (የቅርጽ ለውጥ) በማድረግ ለብሔሩ ቋንቋ መጻፊያነት አመቺ ማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው።

ሌሎች አስተያየት ሰጪ ምሁራን ደግሞ ከሌሎች ተቀራራቢ ቋንቋዎች ልማት ልምድ በመውሰድ፣ በላቲን ፊደላት መጻፉ ለቋንቋው ባህሪ በእጅጉ የሚስማማና ቋንቋውን መጻፍና ማንበብን ቀላል ከማድረጉም በላይ፣ የውጭ አገር ሰዎችም ቋንቋውን በቀላሉ እንዲማሩ ዕድል ይሰጣቸዋል ብለው ያምናሉ። እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ለቋንቋው ጠባይ አመቺ፣ ቀላልና ዝግጁ ፊደላት እያሉ፣ “አገርኛ ፊደላትን ለመጠቀም” በሚል ብቻ፣ተጨማሪ ልፋት ውስጥ መግባት አይገባም ባይ ናቸው።

አማርኛ ፊደላትን ከሞከሩ በኋላ ወደ ላቲን ለመቀየር ከተገደዱ ቋንቋዎች መካከል እንደ ኮንሰኛ ቋንቋ ሁሉ ኩሻዊና የኮንሰኛ ዘመድ የሆነው ኦሮምኛ ቋንቋ ተጠቃሽ ነው። ከኦሮምኛ ቋንቋ የተገኘው ልምድም ከአማርኛ ወደ ላቲን ፊደላት ለተደረገው ለውጥ ወይም ሽግግር ታሳቢ መደረጉ ልብ እንዲደረግ፣ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ማሳሰብ ይወዳል።

በ2006 ዓ.ም በኮንሶ ዞን መንግሥት (የያነው ወረዳ) ደረጃ በቋንቋ ባለሙያዎች ምክክር ከተደረገበት በኋላ፣ ፊደላቱ ላቲን እንዲሆኑ ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በኩልም አዲሱን የላቲን ፊደላት የማስተዋወቅ ሥራ ወዲያው ተጀምሮ በስፋት እየተሠራበት ይገኛል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ጋር በመተባበር ከዚህ በፊት የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ፊደላት በተጻፈው ኮንሰኛ ማሳተሟ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይና አዲስ ኪዳናትን በአንድነት) ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ጋር በመተባበር ተርጉማ፣ በአዲሱ የላቲን ፊደላት እንዲታተምላት በቅርቡ ወደ ቻይና አገር መላኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ታትሞ ይመጣል ተብሎም ይጠበቃል።

ይሁንና፣ ከዚህ በፊት በአማርኛ ፊደላት ኮንሰኛን ማንበብ የተማሩና አዲስ ኪዳንን በአማርኛ ፊደላት የሚያነቡት ሰዎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በላቲን ከሚያሳትመው ሙሉ የኮንሰኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጎን ለጎን በኮንሶ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጥረት የሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰኑ ኮፒዎች በአማርኛ ፊደላት ለማሳተም መታሰቡን፣ የትርጉም ሥራውን ከሠሩ አገልጋዮች ለመረዳት ተችሏል።  

 ቤተክርስቲያን ከዚህ በፊትም ኮንሰኛ ቋንቋን ለማልማት ቅድሚያ ኃላፊነት ወስዳ የመሥራቷን ያህል፣ አሁንም በጽሕፈት ፊደላት ሽግግርም ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች።

ኮንሰኛ ቋንቋና መደበኛ ትምህርት ቤቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች ሁሉ የራሳቸውን ቋንቋ አልምተውና አበልጽገው፣ ቢያንስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ለልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርት እንዲሰጡ በፖሊሲ ደረጃ ተቀምጧል።

በዚህ አግባብ፣ ከአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በፊት አስቀድሞ የተጀመረውን ጥረት በማስፋፋት የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ላሉት በዞኑ ለሚገኙ ተማሪዎች ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በኮንሰኛ ቋንቋ ቋንቋ ለመስጠት ዝግጅቱን ጨርሶ ወደ ትግበራ በመግባት ላይ ይገኛል።

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ሁሉም ትምህርቶች በኮንሰኞ ቋንቋ የሚሰጡ ሲሆን፣ ከቋንቋ ትምህርቶች መካከል ደግሞ እንግሊዝኛና ኮንሰኛ ቋንቋዎች ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጣሉ።ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ አማርኛ ቋንቋ በሁለተኛ ቋንቋነት ተጨምሮ መሰጠት ይጀምራል።

በከተማ አካባቢ ለሚኖሩና አፋቸውን በአማርኛ ቋንቋ ለፈቱት ልጆች ደግሞ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል፣ እንደቀድሞው ሁሉም ትምህርቶች በአማርኛ ቋንቋ የሚሰጡ ሆነው፣ ኮንሰኛ ቋንቋ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ እንደሚሰጣቸው የትምህርት መምሪያ መረጃ ያመለክታል።

ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጡ ሲሆን ኮንሰኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ደግሞ እንደ ቋንቋ መሰጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ከትምህርት መምሪያ በተገኙ መረጃዎች ተመልክቷል።

በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሠረት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል አንደኛ ደረጃ የሚባል ሲሆን፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል መካከለኛ ደረጃ ይባላል። ከ9ኛ እስከ 12ኛ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ይባላል። ቋንቋን በተመለከተ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ አንድ አዲስ ነገር፣ የየአካባቢ መንግሥታት (ክልሎች፣ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች) 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገቡ ተማሪዎቻቸው አንድ ተጨማሪ የአካባቢ ቋንቋን መርጠው ለተማሪዎች መስጠት ይችላሉ።

ይህም ማለት በቋንቋ ትምህርት ረገድ፣ ኮንሰኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣሉ። ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ አማርኛ ቋንቋ ይጨመራል። በመጨረሻም 9ኛ ክፍል ሲደርሱ የኮንሶ ዞን መንግሥት ለኮንሶ ተማሪዎች ወደፊት የሥራ ዕድል ለማስፋት “ይጠቅማል” ብሎ የወሰነውን ቋንቋ እንደ 4ኛ ቋንቋ መውሰድ ይጀምራሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ የኮንሶ ዞን መንግሥት የኦሮምኛ ቋንቋን ወይም ሌላ የአካባቢ ወይም ዓለም አቀፍ ቋንቋን ሊመርጥ ይችላል።

የ1ኛ ደረጃ ትምህርትን በኮንሰኛ ቋንቋ መስጠት ያለው ጥቅምና ጉዳት ምንድን ነው?

“ኮንሰኛ ቋንቋ በአማርኛ ፊደላት መጻፉ ቀርቶ በላቲን ፊደላት ይጻፍ” የሚለው ሐሳብ በኮንሶ ምሁራንና ልህቃን መካከል ክርክርና የተለያየ አመለካከት እንደፈጠረ ሁሉ፣ ቢያንስ በአንደኛ ደረጃ (ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍሎች) ላሉ ተማሪዎች ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች (ከቋንቋ ትምህርቶች በስተቀር) በኮንሰኛ ቋንቋ ይሰጡ የሚለው ሐሳብ አሁንም ክርክርና የአመለካከት ልዩነትን ሳያስከትል አልቀረም።

በቅርቡ በማህበራዊ ሚድያ ላይ በኮንሶ ምሁራን መካከል በዚሁ ጉዳይ ላይ በተደረገ የሐሳብ ልውውጥ በዋናነት ሁለት ዓይነት አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል። የመጀመሪያው አመለካከት “ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በኮንሰኛ ቋንቋ ለተማሪዎች ማስተማር፣ አነስተኛ ብሔር ለሆነው ለኮንሶ ህዝብና ለተማሪዎቹ ጉዳት ነው” የሚል ነው። ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ ኮንሰኛን ለኮንሶ ልጆች ማስተማር ቋንቋውን ለማሳደግና ለማልማት እጅግ ጠቃሚ ነው የሚል ነው።

የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ የሁለተኛውን ቡድን አመለካከት ይጋራል። የአንድን ማህበረሰብ ቋንቋ ለማልማትና ለማበልጸግ ቋንቋውን ለትምህርት መሣሪያነት መጠቀም ምትክ የሌለው አማራጭ ነው። ቋንቋው ለትምህርት መሣሪያነት ሲያገለግል፣ ማህበረሰቡ የቋንቋ ልማት ተቋም በማቋቋም ቃላቶችን እስከመፍጠር የሚሄዱ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ለቋንቋው ልማት እንዲተጋ ዕድል ይሰጣል። ተማሪዎችም በቋንቋው ሲማሩ፣ ቋንቋውን ለጽሑፍ ለመጠቀም ይበረታታሉ። በዚህም ቋንቋው በሰፊው የማህበረሰቡ ክፍል ዘንድ በጽሑፍ ቋንቋነት እየተለመደ ይሄዳል።

በዚያው ላይ በዚህ ጽሑፍ መግቢያው ላይ እንደተመለከተው፣ በአንደኛ ደረጃ የሚሰጠው የትምህርት ይዘት መሠረታዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩርና ከፍተኛ ቃላትን (advanced words) የማይጠቀም በመሆኑ፣ በኮንሰኛ ቋንቋ መሰጠቱ ለተማሪዎቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ለምሳሌ፣ አንደኛ ክፍል ስንገባ ትምህርቱ ፈጽሞ በማናውቀው ቋንቋ ከመሆኑ የተነሳ ለአንድ ሴሚስተር ያህል ምን ያህል ስንቸገር እንደነበር፣ የሁላችንም ትዝታ ነው። ቢያንስ የአካባቢ ዕውቀት ላይ የሚያተኩረውን የአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል (ከ1ኛ እስከ 4ኛ) ትምህርት በራስ አፍ መፍቻ ቋንቋ ሲሰጥ፣ ልጆች በቀላሉ እንደሚረዱትና ለቀጣይ ክፍሎች ትምህርትም ጽኑ መሠረት ለመጣል እንደሚረዳቸው፣ በቋንቋ ምሁራን ጥናት የተረጋገጠ ነው።

በዚህ ጸሐፊ እምነት፣ “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ማስተማር ጉዳት አለው” የሚል አመለካከት ያላቸው ወገኖች ወደዚህ ድምዳሜ የደረሱት፣ ከኮንሰኛ ቋንቋ ይልቅ ለኮንሶ ተማሪዎች ይጠቅማል ተብሎ የታሰበው የአማርኛ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ የሚተ’ው ስለሚመስላቸው ነው። አማርኛ ቋንቋ ከ1ኛና 2ኛ ክፍል በስተቀር እንደ 2ኛ ቋንቋ መሰጠቱ እንደሚቀጥል ልብ ማለት ያስፈልጋል። አማርኛን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እስከ ተማሩ ድረስ፣ የአማርኛ ቋንቋን በመማር ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ፈጽሞ አያጡም ማለት ነው። ዋናው ነገር፣ ጥሩ የአማርኛ መምህር ማግኘታቸው ነው። በዚህ ጸሐፊ እምነት፣ ሁሉንም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቶችን በአማርኛ ቋንቋ መማር፣ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ ላይ እምብዛም ለውጥ አያመጣም። ለዚህም የተማሩ የኮንሶ ልጆችን የአማርኛ ችሎታ መታዘብ በቂ ነው።

የአማርኛ ቋንቋ ችሎታቸው የዳበረ የኮንሶ ልጆች፣ የቋንቋ ችሎታቸውን ያዳበረው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በአማርኛ ቋንቋ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች መማራቸው ሳይሆን አማርኛን መጠቀም የሚችሉበት ከባቢ ውስጥ የመሆን ዕድል በማግኘታቸው ነው። ለምሳሌ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አማርኛ ቋንቋን እንደ መግባቢያ ቋንቋ መጠቀም የጀመረው በፕሪፓራቶሪ ትምህርት ምክንያት ከኮንሶ ወጥቶ አርባምንጭ ከተማ ላይ 11ኛ ክፍልን መማርን በጀመረበት ወቅት መሆኑን በመግለጽ የራሱን ተሞክሮ በማሳያነት ማቅረብ ይፈልጋል። 

እንደ መደምደሚያ

በኮንሶ ዞን ከ6ኛ ክፍል በኋላ ባሉት ክፍሎች ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚሰጡ ይታወቃል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ እስካልተለወጠ ድረስ፣ እስከ 6ኛ ክፍል በአማርኛ ሲሰጥ የነበረው ትምህርት በኮንሰኛ እንዲሰጥ ተደርጎ አማርኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠት መቀጠሉ፣ በኮንሶ ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ ላይ የጎላ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ይልቁን ተማሪዎች መሠረታዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመማራቸው ለቀጣይ ደረጃ ትምህርታቸው መልካም መሠረት እንዲጥሉና በተጨማሪም ለቋንቋው ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ለመደበኛ ትምህርት ጥቅም ላይ ማዋል፣ ምናልባትም የተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ላይም ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት ላለባቸው ወገኖች አጭር ነገር በማለት ጽሑፉን ለመቋጨት እንሞክር። ከዚህ በፊት እንግሊዝኛ ቋንቋ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል እንደ አንድ ትምህርት እንደሚሰጥና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚሰጡ ይታወቃል።

በአዲሱ ፖሊሲም ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ልዩ ትኩረት ስለተሰጠ፣ አሁንም እንግሊዝኛ በተመሳሳይ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል። ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ፣ ሁሉም ትምህርቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሰጣሉ። ስለዚህ ከ1ኛ ክፍል እስከ 6ኛ ክፍል ሁሉም ትምህርቶች በኮንሰኛ ቋንቋ መሰጠታቸው፣ በተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክህሎት ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም።

እንደ አማርኛው ሁሉ፣ የኮንሶ ልጆች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት አጥጋቢ እንዳልሆነ ይታወቃል። ስለዚህ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በኮንሰኛ ቋንቋ መስጠት፣ የተማሪዎችን የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ክህሎቶችንና እንዲሁም አጠቃላይ የትምህርት አቅማቸውን ያዳክማል ተብሎ በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ የሚሰጋው ሥጋት፣ አላስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለን።

የኮንሶ ተማሪዎች የትምህርት አቅም ወደነበረበት የዕውቅና ደረጃ ለመመለስ ለአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችም ሆነ፣ ለሁሉም የትምህርት ዓይነቶች አቅም ያላቸው መምህራንን መመደብና በትምህርት ቤቶች አካባቢ በሚታዩ የግብዓት ክፍተቶች ላይ ተባብሮ መሥራት እንጂ፣ የኮንሰኛ ቋንቋን ገና ከጅምሩ በሥጋት ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢነት የለውም።  የተለየ አመለካከት ያለውን ማንኛውም ሰው፣ የራሱን ሙግት በምክንያቶች አስደግፎ ማቅረብ ይችላል። ጽሑፉ ላይ አስተያየታችሁን እየሰጣችሁ፣ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ የበለጠ መወያየት እንችላለን።

6 Comments

  1. tesfaye chenfa

    በጣም ሰፋ ያለ ትንታኔ ነው ። it is somehow convincing !!

  2. Tamirat Chenfa

    በሃሳብህ 100 በመቶ ተስማምቻለሁ። የምገርም አቀራረብ ነው። በእውነቱ ልክ አንብበ ስጨርስ ከተቀመጥኩበት ብድግ ብዬ። ዋው ነው። ያልኩት። በርቱ!

  3. ጉደኖ ተይጋኔ

    ገዥ ሐሳብ ነው። አማርኛ የIQ መለኪያ አይደለም። ስለዚህ እንደ አንድ ሳብጀክት መሠጠቱ ተገቢ ነው። እነ ራሺያ፣ ቻይና፣ ኮሪያ ወዘተ ሀገሮች በቋንቋቸው ተምረው ነው ዛሬ የዓለም የቴክኖሎጂ ምንጭ የሆኑት። ፀሐፊው እንዳስቀመጠው፤ “የኮንሶ ምሁራን የአሁን የአማርኛ ችሎታ ደረጃ ማየት ይቻላል” ያለውም ነገር እውነት ነው። ይህ ግን የኮንሶን ልጅ ዕውቀት ልገድብ አልቻለም። ኮንሶ በሄደበት ትምህርት ቤት ሲሰቅል ነው የሚናውቀው። ይህም የሚያሳየው አማርኛ IQ ችንን አይወስንም ማለት ነው። ግፋ ብል በፌዴራል እና በክልል አካባቢ ያሉ የሥራ ዕድሎችን ይነፍጋል። በቀጣይ ደግሞ ከአራት በላይ ቋንቋ ለሥራ መጠቀም ስለሚንጀምር ተፅዕኖው ይቀንሳል። በበኩሌ ፀሐፊውን ስለማብራሪው አመሰግነዋለሁ። የእሱ ሐሳብ ሐሳቤም ስለነበር።

  4. kushabo araro

    I will communicate you back and will discuss more!

  5. አማኖ

    ወንድም ያቬ አፋ ኾንሶን ለትምህርት በማዋል ጉዳይ ላይ በጣም ጥሩ የመነሻ ሀሳብ ና ጠቅለል ያለ ማብራሪያ በማቅረብህ አድናቆትን ሳልገልጽ አላልፍም ።
    የኔ አስተያየት እንደሚከተለው ነው
    በመጀመሪያ አፋ ኾንሶን ለትምህርት፣ ለምርምር ና ለማህበረሰባዊ አገልግሎት እንዲውል የመጀመሪያውን ጥረት ያደረጉ አባቶችን ማስታወስና እውቅና መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው ። በ1970/80ዎቹ የማህበረሰብ አንቂና መሪዎች የነበሩ የወቅቱ የኾንሶ ምሁራን በዋናነት እነ አቶ ኮራ ጋራ ፣ ዮሐነስ ሀዳያ፣ ቶራይቶ የመሳሰሉ ፣ አፋ ኾንሶ ለምቶ ለትምህርት።፤ለምርምርና ለማህበራዊ አገልግሎት መዋል አለበት ብለው፣ጉባኤ አካሂደዋል ፤ ፊደላቱን በመቅረጽ ለአፋ ኾንሶ ጽህፈት መሠረት ጥለዋል ። እናም አድናቆት ያሻቸዋል ።
    በመቀጠል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነየሱስ ቤ/ክ የሳባዊያን ፈደላትን በመጠቀም አፋ ኾንሶ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ አገልግሎት ላይ እንዲውል ያበረከተችው አስተዋጽኦ ሁሌም የሚታወስ ድንቅ ሥራ ነው ። አዲስ ኪዳን በአፋ ኾንሶ ከመታተሙ አስቀድሞ የተለያዩ አጫጭር ጽሁፎችን ፤ የልጆች የተረት መጻሕፍትን ፤የመ/ቅደሱ ታሪኮችን በማሳተም ማ/ስቡን ከቋንቋው ጽህፈት ጋር ለማገናኘት አገናኝ ድልድይ ነበረች ቤተክርስቲያን። እናም ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት ለታሪክ መዝግቦ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ።
    ቋንቋውን (አፋ ኾንሶን) ለትምህርት አገልግሎት ማዋል በርካታ ማህበራዊ ና ኤኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው አያጠያይቅም ። እናም አሁን መነጋገር የሚያስፈልገው የመማሪያ መጽሐፍቱ ይዘት ፣ ደረጃ እና የወደፊት የማሳደግ አድማስ ላይ ነው መሆን ያለበት እንጂ ያስፈልጋል ወይ አያስፈልግም የውይይት ርዕስ አይሆንም። ቋንቋ የአንድ ማህበረሰብ የታሪክ ፤።የማንነት ፤ የስልጣኔ ና የትምህርት ማጎልበቻ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ የሁሉም ማህበራዊ አገልግሎቶች መከወኛ መሠረት ነው። በተጨማሪም የአንዱ ህዝብ ሁለንተናዊ ማንነት መገለጫ እሴት ነው። ስለዚህ አስፈላጊነቱ ግልጽ ነው ።
    መደበኛ ት/ት በአፋ ኾንሶ መስጠትን በተመለከተ ፣ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሰዎች በአእምሯቸው ውስጥ ሃሳባቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋ አሰላስለው ነው በኋላ ቃላት የሚያወጡት ። ይህ ለህጻናት ልጆች ምን ያህል ትርጉም እንዳለው መገመት አያዳግትም ። ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለ አካበቢ፣ስለማህበራዊ ህይወት ፣ስለተፈጥሮ፣ ስለተግባቦት ና ስለ ሂሳብ መሠረታዊ ግንዛቤ ለማሰጨበጥ ከአፍ መፍቻ ቋንቋ የተሻለ ቀላልና ውጤታማ መንገድ የለም።
    ስለዚህ አንደኛ ደረጀ ት/ት ላይ ተካቶ መጀመሩ ምንም ጥያቄ አይኖረውም ። እንዲሁም የዘገየ ስለ ሆነ ቶሎ ወደ ትግበራ መግባት ይኖርበታል ።
    አማርኛ የሀገሪቱ መንግስት የሥራ ቋንቋ ስለሆነ ፣ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠቱ በአገር ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ፋይዳው የጎላ ነው ። በተመሣሣይ መልኩ ኢንግሊሽ በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ከመነገሩም ባለፈ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በቀዳሚነት የተቆራኘ ስለሆነ ዋና የትምህርት መስጫ ቋንቋ መሆኑም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ።
    ባጠቃላይ አፋ ኾንሶን ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ በትምህርት ካሪኩላ ውስጥ አካትቶ ሥራ ላይ ማዋል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም ። የአከባቢው ምሁራንም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ፣ ቶሎ ወደ ትግበራ የሚገባበት መንገድ ላይ ተደጋግፈው መቆም ይኖርባቸዋል ።
    ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች ግብረመልስ በመቀበል የማሻሻያ ትምህርት መውሰድ ይቻላል ።
    ያቬ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ስላነሳህ ምስጋናየን አቀርባለሁ ።
    በመማሪያ መጽሀፍቱ ይዘትና አቀራረብ ላይ ተጨማሪ ውይይት ቢደረግ ጥሩ ግብዐት ይሆናል ብየ እላለሁ ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *