የኮንሰኛ ቋንቋ ጒዳይ

የኮንሰኛ ቋንቋ ጒዳይ

ክፍል ፩

መግቢያ

ለሥራ ጒዳይ ወደ ኮንሶ ልማት ማኅበርና ሆስፒታል በተመላለስኲባቸው ጊዜያት ግርግዳ ላይ የተለጠፈ አንድ ፖስተር ካየሁ ውዲህ በአእምሮዬ የሚጒላላውን ሐሳብ ታታሻ በማኅበራዊ ሚዲያ አፍርጦ ለብዙዎች መነጋገሪያ አደረገው። ጒዳዩ የብዙዎችን ትኲረ የሳበው በአንገብጋቢነቱና በወሳኝነቱ ይመስለኛል። አንዳንድ ወንድሞች “ጒዳዩ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ከተመለሰ በኋላ እንደገና አሮጌ ፋይል ስቦ ወደ ውይይት ጠረጴዛ ማምጣት ምን እንዲሆን ነው” የሚል አስተያተ አላቸው። እውነት ነው በቋንቋ ጒዳይ ላይ ብዙ ውይይቶችና (ስንፖዚየሞች?) መደረጋቸውና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው ትምህርትም እንደሚስጥ ውይይት ተደርጓል። እኔም ተሳተፈበታለሁ (በወቅቱ ለአቀመ አስተያየት ባልደርስም)

ሆኖም ግን ውይይቱ በብዛት በምሁራን አካባቢና በወቅቱ ስብሰባውን የተካፈሉ ሰዎች የሚታወቅ ቢሆንም ለመላው ማኅበረሰብ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች መደርጋቸውን አላውቅም(ሊኖር ይችል ይሆናል)። ከዚህ በተጨማሪ ኮንሰኛ እንዴ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጣል ወይስ አሁን እንደተባለው ሙሉ ትምህርት በኮንሰኛ ይሰጣል በሚለው ላይ ሁሉም ሰው መረጃ ያለው አይመስለኝም። ይህ ሐሳብ በማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በ2014ቱ የምሁራን ውይይት ላይም ተነስቶ ዐውቃለሁ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተንሸራሸሩ አስተያየቶች መረዳት እንደሚቻለው በጒዳዩ ላይ ሁሉም ሰው አንድ አቋም የለውም። ስለዚህ ጒዳይ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት የተመለሰ ሳይሆን በብዙ ፋይሎች ሥር ተበደብቆ የቈየ መሆኑን እንገነዘባለን። የውይይት አጀንዳ መሆኑ የበለጠ ግልጽነት ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚ እንጂ ጒዳቱ ብዙ አልታየኝም። ይልቊን በጒዳዩ ላይ የተሳተፉና በቂ ዕውቀት ያላቸው ወንድሞች ሂደቱንና ውሳኔዎቹን ግልጽ ቢያደርጒልን፣ ግንዛቤያችን እንዲያድግም የቋንቋ ፋይዳውን እንዲያስረዱን ወደ ውይይት መድረኲ እንጋብዛለን።

ጭብጥ

በእርግጥ የተባለው ምንድን ነው? ጥቂት ወንድሞች የውይይቱን ጭብጥ የሳቱት ይመስለኛል። በኮንሰኛ ትምህርት መሰጠት አሰፈላጊ አይደለም ያለ የለም፣ አልተባለም።  

ውይይቱ ሁለት ጭብጦችን የያዘ ነው።

አንደኛ፥- ኮንሰኛ እንዴ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጥ ወይስ ሁሉም ትምህርቶች በኮንሰኛ ይሁን? የሚለው የመጀመሪያ ጭብጥ ነው። ሁሉም ትምህርቶች በኮንሰኛ የሚሰጡ ከሆነ እስከ ስንተኛ ክፍል ድረስ? የሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።

ሁለተኛ፥  የመጻፊያ ፊደል ጋር የተያያዘ ነው፣ የግእዝ ፊደል ወይስ ላቲን? በሚለው ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።

የኔ ሐሳብ

[በዚህ ክፍል የማተኲረው በመጀመሪያው ጭብጥ ላይ ነው።]

በእርግጥ በዚህ ጒዳይ ላይ ሙያዊ አስተያየት መስጠት የማልችል መሆኔ መናዘዝ ይኖርብኛል። ምክንያቱም ሙያዬ ባለመሆኑና በርዕሱ ዙሪያ ያለኝ ንባብ በቂ ስላልሆነ በድፍረት መናገር ስለማልችል ነው። ሆኖም ግን አንዳንድ አጠቃላይ ጒዳዮች ላይ ሐሳብ መስጠት አያቅተኝም።

የቋንቋ ዕድገትን በተመለከተ

ከቋንቋ ባህሪያት መካከል ልክ ሕይወት እንዳለው ነገር “ማደገና መሞት መቻሉ ” ነው። ዛሬ በዓለም ላይ በጣም ያደጉ ቋንቋዎች እንዳሉ ሁሉ የሞቱ (የጠፉ)ም አሉ። ብዙ ወንድሞችም አሁን ያለውን አካሄድ የሚደግፉት ከቋንቋ ዕድገት ጋር በተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ብሔር የራሱን ቋንቋና ባህል እንዲያሳድግ መብት ተስጥቶታል።

በኔ እምነት ቋንቋ የሚያድገው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛ የቋንቋ ባለቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸውላቸው ሲማሩበትና የሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ ሲያደርጒት ነው። እንዲያውም ትልቊ ድርሻ ያለው ሥነ-ጽሑፍ ነው። ኮንሰኛ የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ብቻ አያድግም። ሕዝብ እስካለ ድረስ ቋንቋው ይኖራል። በቋንቋው ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፣ በተለይ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች። በኮንሰኛ የሚጻፉ የልቦለድ፣ ኢልቦለድ፣ መጽሔቶች፣ የንግድ ስሞች፣ ዘፈኖች፣ ፊልሞችና የመሳሰሉ ሥራዎች በቋንቋው ካልተሠሩ የሚጠበቀውን ያህል ላያድግ ይችላል።

ሁለተኛ ድንበር መሻገር መቻል። እዚህ ጋር አንዳንድ የዋህ አስተያየቶችን ማቅናት ያስፈልጋል። አንዳንድ ወንድሞች በራሳቸው ቋንቋ ተጠቅመው ኃያላን የሆኑ እነ ቻይና ሩሲያ፣ ሕንድ… ወዘተ ይጠቅሳሉ። እያወራን ያለነው እኮ ስለ ኢትዮጵያ ሳይሆን ስለ ኮንሶ ነው። እነዚህ ቋንቋቸውን ተጠቅመው ኀያላን የሆኑ አገራት ናቸው፣ የሚወዳደሩትም ከአገር ጋር እንጂ ከአንድ ዞን ጋር አይደለም። ቻይና ውስጥ ያለች አንድት ትንሽ ግዛት የራሷን ቋንቋ ተጠቅማ ዓለም ላይ ኀያል ከሆነች ለኛ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች።

ቋንቋ ድንበር ካልተሻገር በተናጋሪዎች ብቻ ብዙ ተጽዕኖ መፍጠር አይችልም። ተናጋሪ አባላቶችን ማብዛት ይኖርበታል። ለዚህም የሕዝብ ብዛት አንደኛው ምክንያት ሲሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ድንበር ተሻጋሪ ሥራዎችን ይዞ መገኘት ይኖርበታል። ከግእዝ ወደ አማርኛ የተደረገው ሽግግር ከተናጋሪዎች ብዛት የተነሣ ነው። ግእዞ ሞቱ እንኳን (አሁን ትንስሤ እያገኘ ነው) ተፈላጊ ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶችን ይዞ ስላለ ነው። ዛሬ ኦሮሚኛ ሁለተኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን የተወሰነው ከተናጋሪዎች ብዛት ነው። እንግሊዝኛ የዓለም ዐቀፍ ቋንቋ የሆነው በተናጋሪዎች ብዛትና ባዳበረው ጒልበቱ ነው።

ስለዚህ ቋንቋ ያድጋል ስንል ትምህርት አንዱ መስፈርት እንጂ ሁሉንም ያቀፈ እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል። ትምህርት በር ከፋች ነው፣ ዋናው ነገር በሱ መሥራት ነው፣ በተለይ ሥነ-ጽሑፍና ሥነ-ጥበብ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። እንግሊዝኛን ዓለም ላይ ያሰራጨው ከቅኝ ግዛት መስፋፋት ቀጥሎ የአሜሪካ ፊልሞች፣ ዘፈኖችና የሕትመት ውጤቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። እነ ሼክስፕርም በሥነ-ጽሑፍ ሥራቸው በእንግሊዝኛ ዕድገት ላይ ያመጡት ዕድገት በቀላል የሚታይ አይደለም።

በአፍ መፍቻ መማር

በኔ እምነት ይህ መንታ ጒዳዮችን ያረገዘ ሐሳብ ነው። ጥቅምና ጒዳት።

ጥቅም

ሰዎች አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ ሲማሩ የሚያገኙት ጥቅም ቀላል አይደለም። ቀጥታ ትምህሩ ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር ብቻ እንዲገናኙ ያደርጋቸዋል። አፋቸውን ባልፈቱበት ቋንቋ ሲማሩ ግን ከትምህርቱ ሐሳብ በተጨማሪ የቋንቋ መሰናክል ማለፍ ይኖርባቸዋል። በተለይ የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም።

ሌላው ለቋንቋው ዕድገትም ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው። በተለይ ከላይ እንደተከለጸው እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ በገዛ ቋንቋቸው ቢማሩ ከተግባቦት ባለፈ ለሥነ-ጽሑና ለሥነ-ጥበብ መጠቀም ይጀምራሉ ማለት ነው። በቋንቋቸው የሚያስቡ፣ የሚፍላሰፉ፣ የሚያዜሙ፣ የሚገጥሙና የሚጽፉ ሰዎችን ለመፍጠር ይረዳል።

ሌላው አሁን እንደተባለው እስከ 6ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ በቋንቋው ቢያንስ ዲፕሎማ ያላቸው መምህራን ያስፈልጒናል (ኮንሰኛን እንዴት ትምህርት ዓይነት ለሚያስተምሩ)። ከዚህ በተጨማሪ የመዝገበ ቃላትና ተጨማሪ አጋዥ መጽሐፍት እጅግ በጣም አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ያልተሟሉ ከሆነ ግን ሂደቱን አቸጋሪ ከማድርጒም በላይ በትውልድ ላይ መፍረድ ይሆናል። ቢያንስ ከኢትዮጵያ ሁሉ ጋር እንደምንወዳደር መዘንጋት የለበትም።

በቀላሉ ከሌላ ማኅበርሰብ ጋር ተግባብቶና ተወዳድሮ ብቁ ለመሆኑ ቋንቋ ትልቅ መሣሪያ ነው።

ጒዳቱ

በገዛ ቋንቋ መማር ለቋንቋ ዕድገትና ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከላይ ለመጥቀስ ሞክሪያለሁ። ሆኖም ግን ጉዳትም አለው ብዬ አምናለሁ። ቋንቋውን ያሳድጋል፣ ሰዎቹን ግን ይጎዳል። በተለይ አሁን የተመረጠው አካሄድ ትንሽ የሚያስቸግር ይመስለኛል። ከ1ኛ እስከ 6ኛ በኮንሰኛ፣ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ በእንግሊዝኛ መሆኑ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድረዋል፣ በተልይ አማርኛ።

አሁን ባለንበት ማኅበረሰባዊ መስተጋብር ውስጥና በቀጣዩ ዘመናት እየተፈጠረ ካለው ዓለም ጋር እኲል ለመራመድ ከሚያስፈልጒ መሠረታዊ ጒዳዮች መካከል ቋንቋ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የቋንቋ ችሎታ (Fluency) በአንድ ሰው ሕይወት ስኬት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አለው። ከዚህ በፊት በአማርኛ በሚገባ ተምረን እንኳን ብዙ እንደምንቸገር የታወቀ ነው። የኛ ልጆች ደግሞ በብዛት ተጋላጭነቱም ስለሌላቸው (ከከተማ ልጆች በስተቀር) እንደ አንድ ትምህርት ብቻ ወስደው ገቢያ ላይ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ብሎ ማስብ ይከብዳል። ዞሮ ዞሮ ተምሮ ተመልሶ ወደ ኮንሶ የሚሰበሰቡ ዜጎችን ነው የምናፈራው። ይህ የሥራ አጥነትን ያበዛል፣ የልጆችን በራስ መተማመን ይጎዳል። ይህ በኦሮሚያ ክልል ተሞክሮ በተግባር የታየ ነው።

የተማሩ የኮንሶ ልጆች ከኮንሶ መውጣት አይፈልጒም የሚል ትችት የባለፈው የምሁራን ውይይት ላይ ተነስቷል። እውነት ነው፣ ይኸ ችግር አለ። የዚህ ዓይነተኛ ምንጭ ደግሞ ቋንቋ ነው። በቀላሉ ከሌላ ማኅበርሰብ ጋር ተግባብቶና ተወዳድሮ ብቁ ለመሆኑ ቋንቋ ትልቅ መሣሪያ ነው።

በተለይ ደግሞ እነ ዶ/ር ኲሴ ኮይሪታ ያነሱት Human development Capital ፕሮጀክት ላይ ትልቅ ተጽዕኖር ይፈጥራል። ዕቅዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ ሰው ኀይል መፍጠር ሲሆን የቋንቋ ችሎታ ማነስ ግን ወደ ቀበሌ የሚመልስ ይሆናል።

ሲጠቃለል

ኮንሶ ለግብርና የሚሆን የተፈጥሮ መሬት የላትም፣ ያላት የሰው ሀብት ነው። ያንን የሰው ሀብት በአግባቡ መጠቀም ካልቻለች ከድህነት ልትወጣ አትችልም፣ ተመሳሳይ ችግሮች በየዘመናቱ ሲያማርሩን ይኖራሉ። ስለዚህ የሰው ሀብት ግንባታ ላይ ትኲረት የምናደርግ ከሆነ በችኮላና በግምት የምንወስናቸውን ውሳኔዎች ትተን ጥልቅ ውይይቶችን በማካሄድ የተሻለ የሆነውን መንገድ መምረጥ ይኖርብናል።

ከተማ ላይ የሚኖሩ ልጆች ከትምህርት ቤት በተጨማሪ በግላቸው የቋንቋ ሀብታቸውን ለማሳደግ ከፍለው እንግሊዝኛ፣ ቻይንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዐረብኛ ወዘተ. . . ይማራሉ። ይህንን የሚያደርጒት ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ነው። እኛም ከዚህ አንጻር ራሳችንን ልንመዝን ይገባል።

ይኸ ችግር እንደማይፈጠርና የራሴ ስጋት ብቻ ከሆነ እሴየው ነው፣ በያዝነው መንገድ መቀጠል እንችላለን። ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል የሚገመት ከሆነ ግን ከወዲሁ መቅረፊያ መንገዱን ማማተር ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

ይህንን ሐሳብ ከመቋጨታችን በፊት ግን አንድ ጥያቄ ላንሳ። በኮንሰኛ ምንድን ነው መሥራት የፈለግነው? እንዲሁ ሌሎች ስለሚያደርጒ “ከማን አንሼ” በሚል ወኔ ብቻ ነው ወይስ በቋንቋው ከመማር ባለፈ ለምርምር፣ ለሥነ-ጽሑፍ፣ ለሥነ-ጥበብ፣ ለቴክኖሎጂና ለሙዚቃ እንገለገልበታለን?

አንድ የኮንሶ ልጅ በአማርኛ ልቦለድ ብጽፍ ነው የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆነው ወይስ በኮንሰኛ? በቋንቋ ልናሳክ ያሰብነው ግባችንስ?

ክፍል ፪ ይቀጥላል


4 Comments

  1. Yavello Nataye

    ዕይታህ መልካም ነው። ይሁንና የኮንሶ ልጆችን ተወዳዳሪነት ለመጨመር መፍትሔው (በእኔ አመለካከት)፣ ኮንሰኛን ቢያንስ በአንደኛ ደረጃ መጠቀምን መተው ሳይሆን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ ከዚህ በፊት ከተደረገው የተሻለ ጥረት ማድረግ ነው።

    በእኔ እምነት የ1ኛ ደረጃ ትምህርትን በኮንሰኛ ቋንቋ መስጠት የአማርኛንም ሆነ የእንግሊዝኛን ቋንቋዎች ዕድል አይዘጋም። ይልቁኑ ለኮንሰኛ ቋንቋ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት፣ ለአማርኛና ለእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ።

    ራሱን የቻለ መፍትሔ የሚፈልግን ጉዳይ ከኮንሰኛ ቋንቋ ጋር አያይዘን እየተወያየን ያለ ይመስለኛል።

    ለማንኛውም ቀደም ሲል በፅሑፍሕ ለማንሳት እንደሞከርከው፣ ቋንቋውን በተመለከተ በተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የተሳትፉ የቋንቋ ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ቢሰጡን እጅግ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት እኔም ጋር አለ። እስኪ የሚሉንን እንስማ።

  2. ማቴዎስ ገለቦ

    ##ቋንቋችንን የማሳደግ ጉዳይ ….

    እንደተባለው ከ2006 ዓ.ም በኋላ ‘’Afaa xonso’’ን የትምህርት ቋንቋ ከማድረግ አኳያ ጠጨማሪ ሀሳብ ለማሰባሰብ ታስቦ የተዘጋጁ የምክክር መድረኮች ስለመኖራቸው መረጃው የለኝም፡፡ መረጃ ያላቸው አካላት ካሉ ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሊሠጡ ይችላሉ፡፡
    የሆነ ሆኖ አሁን ላይ እያከረከረ ያለው ጉዳይ “”ሀሳቡ ለምን ተነሳ??”” የሚል አይመስለኝም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ መለዋወጥና በጥልቀት መወያየትማ ይበረታታል እንጂ መኮነን ያለብን አይመስለኝም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው የኮንሶ ተወላጅ ምሁራንን በመጋበዝ “”በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ተሞክሮና ክህሎት(አንተም እንዳነሳሄው ጥቅሙና ጉዳቱን በሚያሳይ መልኩ) እንዲያካፍሉን ማድረግም አንድ የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፡፡
    ይሁንና ችግሩ ያለው አንዳንድ የሚሠጡ አስተያየቶች በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳብ እንድንለዋወጥ በር የሚከፍቱ ሣይሆኑ አስቀድመው “”የራስን ውሳኔ የማሳረፍ”” ዓይነት አካሄድ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አይመስለኝም፡፡ አንተም እንዳልከው የራሳችንን ቋንቋ ማሳደግን የሚጠላ የለም፡፡ ቋንቋ የሚያድገው ደግሞ ተናጋሪዎች ስላሉት ብቻ ሣይሆን ቋንቋው ወደትምህርት እና ወደሥራ ቋንቋ ሲሸጋገር ነው፡፡ የራስን ቋንቋ የማሳደግ ጉዳይ ደግሞ ለዜጎች የተሠጠ ህገመንግስታዊ መብትም ጭምር ነው፡፡
    ስለሆነም ሀሳብ ስንለዋወጥ በመሠረታዊ ጭብጦች ላይ ከማተኮር ይልቅ በራሳችን ቋንቋ “”ማስተማር/መማር””ን እንደልዩ ችግር የመቁጠር ሁኔታ በቅድሚያ መታረም ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተለይም ልጆችን በቋንቋ ማስተማር “”ትውልድን መግደል ነው፣ ወንዝ አያሻግርም፣ ቅጽበታዊ ውሳኔ ነው፣ ወንጀል ነው፣ የፖለቲካ ውሳኔ ነው ወዘተ”” የመሳሰሉ አባባሎች ቀድመው መምጣት ያለባቸው አይመስለኝም፣ መታረምም አለባቸው፡፡
    በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ የምንሠጣቸው/የምንለዋወጣቸው አስተያየቶቻች አስቀድሞ “”ደምድሞ የመሄድ/የመምጣት”” ዓይነት አካሄድ ከመከተል ይልቅ፡-
    1. እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎችን በጥልቀት በሚፈትሽ/በሚዳስስ፣
    2. የራሳቸውን ቋንቋ የትምህርት ቋንቋ ያደረጉ በርካታ አካባቢዎች ከሀገራቻን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ምን ምን ጥቅሞች እንዳገኙና ምን ምን ተግዳሮቶች እንዳጋጠማቸው በጥልቀት በሚዳስስና ለሌሎቻችን ልምድ በሚያፍልና ግንዛቤ በሚያስጨብጥ፣
    3. በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የትምህርት ሚ/ር ወቅታዊ አቋምና አቅጣጫን በጥልቀት በሚቃኝ/በሚዳስስ፣
    4. ቋንቋውን የጽሑፍ ቋንቋ በማድረጉ ሂደት የትኛው ፍደል/ላቲን ወይስ ሳባዊያን/ ተመራጭ እንደሆነና ለምን ተመራጭ ተደርጎ እንደተወሰደ ከሙያና ከልምድ አንጻር በአግባቡ በሚተነትን፣
    5. ቋንቋችንን ከየትኛው የትምህርት ደረጃ/ክፍል/ መጀመር እንዳለብን፣ ስንጀምር “”እንደአንድ የትምህርት ዓይነት”” ወይስ “”ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በቋንቋችን የማስተማርና የመማር”” አስፈላጊነት ጥቅምና ጉዳት ከሙያ አኳያ በጥልቀት በሚተነትን፣
    6. በቋንቋችን ማስተማርና መማር የሥራ ዕድል ከማስፋት፣ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ወዘተ ላይ ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ምን ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በሚያብራራና ሌሎችን ግንዛቤ የማስጨበጥ አካሄድ በመከተል፣ ወዘተ
    7. በአጠቃላይ ቋንቋችንን “”የትምህርት ቋንቋ”” የማድረግ ጉዳይ ምን ምን ፋይዳዎች/ጥቅሞችንና ጉዳቶችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል በግልጽ በሚያሳይና ለሌሎች ግንዛቤ በሚያስጨብጥ መልኩ ቢሆን እጅግ ተመራጭ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

    • እውነት ነው፣ ሐሳባችን ተቀራራቢ ነው። ችግሩ አንዳችን የሌላችንን ሐሳብ በወጒ ስለማንረዳ ይመስልኛል። አሁን እየተደረገ ያለው ውይይት መልካም ይመስለኛል። በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ነው የውይይት ባህል የሚዳብረው።

  3. Tamirat

    ባጭሩ ለሎች ቋንቋዎች እንዳደጉ ሁሉ የኛ ትውልድ ከጀመረው ቀጣዩ ትውልድ ትኩረት ሰቶ ከሰራበት ቋንቋው ያድጋል። ቡዙ ተናጋሪ እንደምኖረው መገንዘብ መቻል መሠረታዊ የሆኔ ሃሳብ ይመስለኛል። ይሄ ላይ ሳንስማማ ቃላት መርጠን ረጅም ፁፍ ስለፃፍን እንብዛም አሳማኝ መስሎ አይታየኝም። ለማንኛውም ቋንቋን በተመለከቴ እስካሁን ከተሰጡ አስተያዬቶች #ያቤሎ_ናታዬ የፃፈው ለሁላችን ገዥ ሃሳብ ይመስለኛል።

    ከዛ በዘለለ ምንም አድስ ሃሳብ በዝህ ፁፍ ውስጥ አልታየኝም።

    #ሳጠቃልለው ቋንቋው በትምህርት መልክ መስጠት ቋንቋውን ለማሳደግ እና ከሞት ለመታደግ(ተናጋሪ እየቀነሴ በመጣ ቁጥር እና በቋንቋው የምፃፉ ህትመቶች በጠፉ ቁጥር ቋንቋው እየሞተ መሆነን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል።) መነሻ ይሆናል። ከዝያም በቋንቋው የተማረ ትውልድ ሥነ-ፅሁፍ፣ልቦለድ፣የተረት መፅሃፍቶች፣መዝገበ ቃላት እና ለሎችንም መፃፍቶችን መፃፍ የምስችል አቅም ይፈጥራል። ይህም ማለት መጀመሪያ ት/ት ከሁሉም ይቀድማል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *