የቋንቋ ጒዳይ

የቋንቋ ጒዳይ

Tatasha Takaye Kasito: Lecturer at Wolaita Sodo University

በዚህ ጉዳይ ላይ አለመተንፈስ አልቻልኩም ወደፊት አልተናገርኩም ብዬ ከሚጸጸት ልተንፍሰው የኮንሶኛ ቋንቋ ወደ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ሳይገባ ይቆይ እንጂ መካነ-ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን በከፍተኛ ወጪ ለዘመናት ለፍታ ከሳቢያን ፊደላት የኮንሶኛ ቋንቋ ወደ ጽሑፍ አሳድጋለች። በዚሁ ጅምር ሥራ ላይ እያሳደጉና እያሻሻሉ መሄድ ይገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ። እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆንም ቤተ-ክርስቲያን (መካነ-ኢየሱስ) በሁለቱም፤ በሳቢያንም ላቲነኛም መጽሐፍ ሊታሳትም ነው ይባላል። ቢያንስ ሁለቱን ጎን ለጎን ማስከዱ መልካም ነው። ሁለቱን አስተምሮ ማስጨበጥ ከተቻለ የጨመረ እንጂ የቀነሰ ነገር የለም ማለት ነው የቀድሞውን ያወቀ በቀድሞው፣ ላቲነኛዉንም ያወቀ በላቲነኛ፣ ሁለቱን ማስተማር ከተቻለ ሁለቱን የቻለ በሁለቱ ይችለዋል። የእውነት ይህን ካደረገች ሊትመሰገን ይገባታል። ሌሎችም ተቋማትም ያንኑን ፈለግ ቢከተሉ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለዉም። ለዚያዉም ቀድሞ መካነ-ኢየሱስ በጣለችው መሠረት ላይ ተንተርሶ መሥራት ቀላል ነው። ምንም የሚጋጭ ነገር ያለው አይደለም።

የእኔ ጥያቄ ዘመናዊ ትምህርት ላይ ነው ኮንሶኛ ወደ ዘመናዊ ትምህርት መምጣቱ መልካም ነው። እሱ ላይ ጥያቄ የለም። እንደ እኔ እምነት ግን የቀድሞ የቤተ-ክርስቲያኗን ኢንቨትመንትና የዘመናት ልፋትን ወደጎን በመተው “ላቲነኛ” በሚል ፈሊጥ ኮንሶኛን በላቲነኛ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ለማስገባት መሞከሩ የስህተቱ መነሾ ነው ብዬ አምናለሁ። የቋንቋ ባለሙያ ወንድሞቻችን በሙያችሁ ውስጥ ጥልቅ ብለን በድፍረት ባንገባም በዚህ ጉዳይ ላይ ትክክል መሆን አለመሆናችሁ ዳኛ ሆኖ የሚበይነው ጊዜ ብቻ ነው። እኔ የማምነው ጉዳዩ ከሙያ ይልቅ የማይጠቅም ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለበት አደገኛ ስህተት ነው። እኔ ውሸታም ሆኜ ትክክል ቢትሆኑ ደስ ይለኛል። አይሆንም እንጂ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ አስተያየት የሳቢያን ፍደሎች ተሠርተው ያለቁ፣ ምንም ተጨማሪ የፈጠራ ልማትና ኢንቨስትመንት የማያስፈልጋቸው ስለሆኑ ኮንሶኛ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ሲገባ በሳቢያን ፊደሎች ይሁን። የሚያሥቸግሩ ድምጸቶች አሉ የሚባለውን ደግሞ ተፈላስፋችሁ ፍጠሩ። በተለያዬ ምልክት። ከዚያ ሰው ይማራል፣ ያውቃል። አንድ በሉ።

ሁለተኛ ኮንሶኛ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ቢሰጥ መልካም ነው። በዚያ ላይ ምንም ተቃውሞ አይኖርም። እስከ 12ኛ እንደ አንድ ትምህርት ሆኖ ይዝለቅ። እያደገ ሲሄድ እስከ ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲ መሠጠት ይችላል። ይኼ የቋንቋው ሳይንሳዊ ዕድገት የሚወስነው ጉዳይ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አሁን እንደምንሰማው “ኮንሶ ዞን ውስጥ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ከ1ኛ እስከ 6ኛ በኮንሶኛ ይሰጣል” የሚባለው ትክክል አይደለም። ትክክል አይደለም ብቻ ሳይሆን ትውልድ ላይ የሚፈጸም አደገኛ ወንጀል ነው። “ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው፣ ይኼ ዓለም አቀፍ መብት ነው፣ ቋንቋ የማሳደግ መብት ነው፣ ምንትስ….” እና የመሳሰሉ እንቶፈንቶ መከራከሪያዎች እዚህ ጋር እንደማይመጡ ተስፋ አደርጋለሁ። “ቋንቋ አይደግ” ያለ የለም፣ “ልጆች ኮንሶኛ እንደ ትምህርት አይማሩ” ያለ የለም። እያልን ያለነው “ኮንሶኛ ቋንቋ ይልማ፣ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ይግባ ነገር ግን አገባቡ የነገ ትውልድን ብሔራዊና አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን በሚጎዳ መልኩ መሆን የለበትም” ነው። እንዲህ ዓይነቱ የቋንቋ ፖሊሲ በሀገራችን ሌሎች አካባቢዎች ተተግብረዋል። ውጤቱ ግን ያሳዝናል። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ሰው ይህን ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ። ይህን እያየን ኮንሶ ውስጥ ተመሳሳይ ፖሊሲ ይተግበር ማለት ወይም ሲተገበር ምንም ሳይተነፍሱ ማየት ነገ ጸጸትን እንዳያመጣብኝ ነው ይህን አስተያየት የምጽፈው። ስለዚህ ሳይረፍድ መስተካከል አለበት የሚል አስተያየት አለኝም። ኮንሶ ዞን ውስጥ ትምህርት መሠጠት ያለበት የነገ ትውልድ ብሔራዊና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን አለበት። ለዚህ ሲባል ደግሞ ትምህርት በአማርኛና በእንግሊዝኛ መሰጠት አለበት።

All Subjects by Afa Xonso or as one subject? Sabean or Latin script is preferred?

እደግመዋለሁ በአማርኛና በእንግሊዝኛ መሰጠት አለበት። በእነዚህ ቋንቋዎች ትምህርት እየተሠጠ እንኳን ተወዳዳሪነት እየቀነሰ ነው፣ መሻሻል መምጣት አለበት፣ ጥራት ላይ፣ የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ… መሠራት አለበት እያልን ባለንበት ጊዜ ሌላ እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ነገ ከኮንሶ ውጭ ሄዶ መግባባት፣ መወዳዳር የማይችል ትውልድ እንፍጠር ማለት ራስን እንደማጥፋት ነው። ስለዚህ ከወዲሁ ይስተካከል ባይ ነኝ። ቢቻል ቢቻል እና አቅሙ ካለ ከ3ኛ በኋላ እንደ ኦሮሚኛ ያለ ሰፊ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ቢሰጥ፤ ሰው ቢያውቀው መልካም ነው። ተወዳዳሪ ያደርጋል። ይጠቅማል። ከዚያ ውጭ ያለ መንገድ እውነት ለመናገር አጥፊ ነው። ለዚያውም ትውልድ አጥፊ። በቅንነት ነገሮች ሥር ሳይሰዱ፣ ወጪ ሳይወጣ፣ ትውልድ ሳይጎዳ ፣አስተካከያ ማድረግ አማራጭ የለዉም የሚል አስተያየት አለኝ።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *