የመንግስትና የህወሓትን የሰላም ስምምነት የሚቆጣጠርና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን መቋቋሙ ተገለጸ

የመንግስትና የህወሓትን የሰላም ስምምነት የሚቆጣጠርና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን መቋቋሙ ተገለጸ

የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድንና የተልዕኮ ቡድን በአንድ ላይ

በአፍሪካ ሕብረት ሥር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን መቋቋሙ ተገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ በዛሬው እለት መቀሌ መግባቱ ይታወቃል። ታዛቢ ቡድኑ መቀሌ ከተማ መግባቱን ተከትሎ፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በተገኙበት ስብስባውን ያደረገ ሲሆን፤ የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን አቋቁሟል።

በአፍሪካ ህብረት ሥር የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከበር የተልዕኮ ቡድኑ ሶስት አባላት ያሉት ሲሆን፣ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሲቪልና ወታደራዊ ስምምነቱን አፈፃፀም የሚከታተል መሆኑን ኢ.ዜ.አ ዘግቧል።

የተልዕኮ ቡድኑ አባላትም ሜጀር ጀነራል ራዲና ስቴፈን ከኬንያ፣ ኮሎኔል ሩፋይ ኡመር ማይሪጋ ከናይጄሪያ እንዲሁም ኮሎኔል ቴፎ ሰኮል ከደቡብ አፍሪካ ናቸው።

አባላቱ በዛሬው ዕለት፣ ለፌደራል ፖሊስ በመቀሌ ከተማ ያሉ የመንግስት ተቋማትን የማረካከብ ሂደትን ማስፈጸማቸውም ተነግሯል። በርክክቡ ወቅት የተልዕኮ ቡድኑ ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ራዲና ስቴፈን “የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለመረዳት ጠቃሚ መንገድ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ በዘገባው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ በፌደራል መንግስት የሚተዳደሩ ተቋማትን ለመጠበቅ በዛሬው እለት መቀሌ መግባቱ ይታወቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከቀናት በፊት በትዊተር ገጻቸው በሳፈሩት ጽሁፍ፤ በ2ኛው የናይሮቢ የሰላም ስምምነት መሠረት ህወሓት የታጠቃቸው ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግስት የማስረከብ ሥራ እስከ ሀሙስ እንደሚያከናውን መግለጻቸው ይታወሳል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቀሌ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸው ነበር።

የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን በሰላም ስምምነቱ የተጠቀሱ ነጥቦች ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በዛሬው እለት መቀሌ ገብተዋል። በዚህ ሳምንትም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የፌደራል መንግስ ልዑክ ወደ መቀሌ ማቅናቱም ይታወሳል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *