<a>የሕይወት ሁለት ገጾች</a>

የሕይወት ሁለት ገጾች

ደስታና ስቃይ

የጎረቤቴ ጂፓስ “አላለቅስም” የሚል መዝሙር ከፍ ባለ ድምጽ ይዘምራል፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ በሰቆቃ ደብተሬ ላይ የለቅሶ እንጉርጉሮ እየፃፍኩ ነበር፡፡ “አምላክ ሆይ፥ ሕይወቴን ነገርሁህ፤ እንባዬን እንደ ትእዛዝህ በፊተህ አኖርህ።”[1] እያልሁ፣ ተቃርኖ፡፡ “ዛሬ የማያለቅሱ ብፁዓን ናቸው” አልኩ በሆዴ፡፡ ዛሬ የማያለቅሱ ብፁዓን ናቸው ካልኩ በኋላ ነገ ያለቅሳሉና የሚል ሐረግ ለመጨመር አስቤ እርግማን እንዳይሆን ፈርቼ ተውኩት፡፡ ለምን ቢባል የተራራው ስብከት የሚባለው ትምህርት መቼቱ ሁለት ነውና፤ አሁንና ነገ፡፡ ትምህርቱ ንጽጽሮሽ የተመሠረተው በዛሬና ነገ ላይ ነው፡፡ ዛሬ የምንሆነው ነገ ውጤቱን በተቃራኒ ነው የምናገኘው፡፡ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።” የሚያዝኑ፣ መቼ? ዛሬ፤ መፅናናትን ያገኛሉ፣ መቼ? ነገ፡፡ ዛሬ የሚያለቅሱ ነገ ይስቃሉ፡፡

ገጽ ፩

የዓለም ስቃይ

ዛሬ ላይ እየኖሩ አለማልቀስ አይቻልም፣ ይልቁን ጥያቄ የሚሆነው “ለየትኛው አልቅሼ የትኛውን ልተወው?” የሚለው ነው፡፡ አቤት የሚያስለቅሱ ነገሮች አበዛዛቸው!!

ከገና በፊት (የ2011 ዓ.ም) የነበሩ ሁለት ሣምንታት ሆስፒታል ውስጥ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ እንደምናውቀው ሆስፒታል ማለት በብዛት ነፍሳት የምድር ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት ቦታ ነው፤ ወይም ደግሞ የሞት ደጅ ጋር ደርሰው የሚመለሱበት፡፡ በዚህ ቆይታዬ ብዙ ነፍሳት የሕያዋንን ምድር ተሰናብተው ዳግም ላይመለሱ ጥለውን ሲሄዱ አይቻለሁ፡፡ ከሕክምና ባለሙያዎች እርዳት ሽተው አልጋ ላይ የተኙ ሕሙማን ከስቃያቸው የተነሣ የሚያሰሙት የጣር ጮኸት ከሚሄዱት ነፍሶች ይልቅ ልብን የሚሰብር ነበር፡፡ አንድ ሰው ውጭ ሆኖ ቢያለቅስ ምን ሆነሃል/ሻል? ተብሎ ይጠየቃል፤ ሆስፒታል ግን ይኸ ጥያቄ አይኖርም፡፡ ሰው ቢያለቅስ ለምን እንደሚያለቅስ ይታወቃልና፣ በሥጋው ውስጥ ገብቶ እረፍት በሚነሳው ሕመም አሊያም በዘመዱ ላይ በሚደርሰው ስቃይ፣ ወይም ባጠቃላይ የሰው ልጅ የሚቀበለው መከራ አሳዝኖት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ሆስፒታልና ለቅሶ ቤት ብቻ ይመስለኛ ሰው በነፃነት እንዲያለቅስ የሚፈቀደው፡፡

In an intensive care ward, all visitors are united by a single, awful thread: concern over a dying relative or friend. Economic differences, even religious differences, fade away. You’ll see no sparks of racial tension there. Sometimes strangers will console one another or cry together quietly and unashamedly. All are facing life at its most essential[2]

(ትርጉም) “በሆስፒታል ውስጥ የተገኙ አስታማሚዎች ወይም ጠያቂዎች በሚሞተው ወዳጃቸው ወይም ዘመዳቸው ምክንያት በአንድ አሳዛኝ የስሜት ሰንሰለት ይተሳሰራሉ፣ እዚያ ጋ የሃይማኖት ወይም የሀብት ልዩነት ይደበዝዛል፡፡ የዘረኝነት ውጥረትም አታገኙትም፡፡የማይተዋወቁ ሰዎች እንኳን ሳይቀር አንዱ ሌላውን ማጽናናት ይጀምራል፣ አሊያም በጋራ ያለ ፍርሃት ያለቅሳሉ፣ ሁሉም ሕይወት በወሳኝ ሰዓት ላይ የምትሆነውን ያዩታል፡፡” 

እነዚያ የስቃይ ጩኸቶች መስማት ጆሮአችን እንደ ሙዚቃ በለመዱበት ሰዓት ከተለያዩ የከተማው ማዕዘናት ነፋስ ይዞት የሚመጣው የፈሽታና የፈንጠዝያ ጩኸት አልፎ አልፎ በጆሮአችን ሽው እያለ ይሰማ ነበር፡፡ ምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው? አንዱ በሞትና በሕይወት መካከል ወድቆ ሲያቃስት ሌላኛው በአልኮል ኃይል ማናቸውንም የምድር መከራዎቹን ሁሉ ረስቶ ዓለሙን ይቀጫል፡፡

ሁለቱንም ጩኸቶች አመዛዝኜ ማንሰላሰል ተያያዝኩት፡፡ እዚህ ነፍስ ውጪ (ሞት) ነፍስ ግቢ (ሐኪሞች) ግብግብ ምክንያት የሚፈጠር የስቃይ ጩኸት፣ እዚያ ደግሞ ዓለምን ከነ ስቃዩ ርስቶ ነፍሱን በቁጥጥሩ ሥር ጨብጦ ዳንኪራውን የሚያጣጥም ቡድን የሚያሰማው የፈንጠዝያ ጩኸት፡፡ ሌላው ጩኸት ከየአብያተ ክርስቲያናት የሚወጣ የጭፈራና የዘፈን የሚመስል የዘመኑ አምልኮ የሚሉት ነገር፡፡ ይህም ከዳንኪራው ሠፈር ጩኸት ብዙም የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ሁለቱም የውጪውን ስቃይ ለመርሳት የሚደረጉ ሙከራዎች ናቸው፡፡

አንዴ በሀሳብ በፈጣሪ ወንበር ላይ እራሴን አስቀምጬ እነዚህ ከሁለት ቦታዎች የሚሰሙ ጩኸቶችን መስማት ጀመርኩ፡፡ ከደስታው ይልቅ የኀዘኑ ጩኸት የበለጠ ጆሮዬን የሚስብ መስሎ ታየኝ፡፡ ፈጣሪስ የትኛውን ጩኸት ነው የበለጠ የሚያዳምጠው? የእግዚአብሔርን ልብ የሚያንኳኳው የጩኸት ዓይነት የትኛው ነው? የደስታ ወይስ የለቅሶ?

ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። ጠቢቡ ሰሎሞን

ዓለም ላይ ሁለት የክፋት መንጋዎች አሉ ይባላል፤ አንደኛው ተፈጥሮአዊ የሆኑ የክፋት መንጋዎች ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ ሰው ሠራሽ ናቸው፡፡ ረሃብ፣ በሽታ፣ የአካል ጉዳት፣ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች፣ ተስፋ ቢስነት፣ ብቸኝነት… ወዘተ የተፈጥሮ ክፋቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ሰው ሠራሽ ክፋቶች

በየእስር ቤቶች የሚፈጸሙ አሰቃቂ የወንጀል ምርመራ ሂደትች፣ ግድያ፣ ጦርነት፣ ማጭበርበርና ማታለል ወዘተ… ሰው ሠራሾች ናቸው፡፡ ተፈጥሮ የሚታደርስብን ያነሰ ይመስል እኛም ተጨማሪ ጉዳቶችን እንፈበርካለን፣ የሰው ልጅ የክፋት ፋብሪካ ነውና፡፡

አንድ ቀን ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ ድንገት የተናገረው ነገር አእምሮዬ ውስጥ ተጽፎ ቀረ፤ ወዳጄ “የሆሊውድ ፊልም ሠሪዎች ሰይጣንን ጭካኔ ያስተምራሉ” የሚል ሐሳብ ነበር ያካፈለኝ፥ ወይቼው ጉድ! ሰው ከሰይጣን በልጦ?! አዎን የሰው ልጅ በክፋቱ ከሰይጣን ሳይበልጥ ይቀራል እንዴ ሰዎች?! ማንም ሰው የመላእክትን ስሜት ማወቅ አይችልም፣ ምን እንደሚወዱ፣ ምን እንደሚጠሉ፣ ምን እንደሚያሳዝናቸው፣ ምን እንደሚያስደስታቸው በእርግጠኝነት እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፣ መልአክ ሆኖ የሚያውቅ ሰው ካልሆነ በስተቀር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መላእክትም የሰውን ስሜት በቀላሉ ሊረዱ አይችሉም፡፡ ሰይጣንም መልአክ እንደመሆኑ መጠን የሰውን ስሜት በወጉ ይረዳል ብዬ አላምንም፡፡ እሱ የቤት ሥራውን በቁጥጥሩ ሥር ላደረጋቸው ሰዎች ይሠጣል፣ ሰው ደግሞ እንዴት አድርጎ የገዛ ወገኑን ማሰቃየት እንዳለበት ስለሚያወቅ ሰይጣን ከሰጠው በላይ ይፈጽማል፡፡ ምክንያቱም ሰው ነው የሰውን ስሜት ሊረዳ የሚችለው፣ ሰውን በጣም ሊጎዳ ወይም ሊያሰቃይ የሚችል ምን እንደሆነ ሊያወቅ የሚችለው፡፡ እና ማዕከላዊ፣ ቃሊት፣ ኦሽዊትዝንና ጓንታናሞ የሰው አእምሮ የፈለሰፋቸው ሰይጣናዊ አሳይሜንቶች የሚፈጸሙባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ሰይጣን የሚዋሳቸው የክፉ ሰዎች አእምሮ በገዛ ወገኑ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ሰይጣን ሊያደርግ ከሚችለው በላይ ነው፡፡ ስለዚህ የጓደኛዬ አባባል ከእውነት የራቀ አይመስለኝም፡፡

ከሂትለር ምድራዊ ገሃነም የተረፈ ኤሊ ዊዘል የሚባል አይሁዳዊ ለአንድ ራባይ(መምህር) ለብዙ ጊዜ ሲያስቸግር የኖረውን ጥያቄ ሰነዘረ፣ “መምህር ኦሽዊትዝን[3] ካዩ በኋላ እንዴት በእግዚአብሔር ማመን ቻሉ?”፤ ራባዩም ለረጅም ጊዜ በዝምታ ከቆዩ በኋላ “ኦሽዊትዝን አይተህ እንዴት በእግዚአብሔር ላታምን ትችላለህ?” ሲሉ በለሆሳስ መለሱለት[4]፡፡ የሰው ልጅ ለገዛ ፍላጎቱ ትንሽ ለቀቅ ሲደረግ ምን ሊያደርግ እንደሚችል እነ ሂትለር ምስክሮች ናቸው፡፡ ሆልኮስት የሰው ልጅ ለገዛ ወገኑ የፈበረከው ምድራዊ ገሃነም ነው፡፡

ባለፈው በሊቢያ ምድር ወንድሞቻችን ሲታረዱ ልባችን በመሰበሩ እንባ እየተራጨን “እንዴት ሰው በሰው ልጅ ላይ እንዲህ ይጨክናል?” ብለን ተገርመን ነበር፣ በአንድነትም እነዚህ ሰብዓዊነት ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸው የሲዖል መንጋዎችን ረገምን፡፡ እየቆየ ሲመጣ በገዛ ምድራችንም የዕለት ዕለት ዜና ሆኖ አረፈ፡፡ እርግጥ እነዚህ አሸባሪዎች እዚያ የድንዛዜ ደረጃ ላይ የሚደርሱት ከብዙ የጭካኔ ልምምድ በኋላ ነው፤ ለመግደል ነው ሳጥናኤል የቀባቸው፡፡ በአገራችን እየሰማን ያለነው ግን ከየት የመጣ ነው? የሃይማኖት ደሴት ተብላ ለዘመናት ስትወደስ ከኖረች አገር ይኸ ይጠበቃል? በአፍቅሮተ ንዋይ የነኆለሉ፣ በዘር ጥላቻ የጦሱ፣ ሰው ሳይሆን “ብሔር” የሚባል የማይታይ ማይጨበጥ ከሰብአዊ ክቡርነት በላይ የበለጠባቸው ክፋት ከልክ በላይ ያሰከራቸው ሰዎች የሚፈጽሙት የሳጥናኤል ግብር ነው፡፡ ብር ብቻ ስጠው፣ ሰው የፈለግከውን የጭካኔ ዓይነት ያሳይሃል፡፡ ይህ ነው ሰው ሠራሽ ምድራዊ ገሃነም፡፡

የእነዚህ ሁሉ (ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ ስቃዮች) መደምደሚያው ሞት ነው፤ የሰው ልጆች ሁሉ እጣ ፈንታ፡፡ ሞት የሚባለው ክፉ መንፈስ በሁላችንም ላይ የሚያንዣብብ ጥላ ነው፤ ትዝ ባለን ቁጥር ቀፋፊ ስሜት የሚፈጥርብን፡፡ ሰው የሚሰቃየው እስከ ሞት ነው፡፡ ስቃያችንን በማቆሙ ምክንያት ሞት እንኳን ኖረ ልበል? የስቃይ ማቆሚያ ኬላ በመሆኑ፡፡ በሌላ በኩል ግን ሞት ይሉት ነገር የሚያደርስብን የፍርሃት ድባብ ቀላል አይደለም፡፡ “ሕይወት በጣም ቆንጆ ስለሆነች ሞት አፈቀራት” ይላሉ ሰዎች፡፡

ሞትን እንደት ማሸነፍ ይችላል?

ሞት እንዳያስፈራራው የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መጀመሪያ ፍርሃቱን ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡ ኢፒኩረስ የተባለ ግርካዊ ፈላስፋ የሰው ልጆችን ደስታ ከሚዘርፉ ሁለት ዓበይት ምክንያቶች 1ኛ “በክፉ ተግባራችን ምክንያት አማልክት ይቀጡናል ብሎ መፍራት ሲሆን ሁለተኛው ሞትን የሚያስፈራ ኃይል አድርጎ ማሰብ” ይላል፡፡ እነዚህ ሁለቱ አስተሳሰቦች በሰው ልጅ ላይ የሚፈጥሩት ውጥረት ከፍተኛ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ለመጀመሪያ መፍትሄ አማልክት ፍጹማን ስለሆኑና በሰው ልጆች ጉዳይ ብዙም ስለማያስቡ መጨነቅ አያስፈልግም፤ ለፈጸምነው ኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ሲባል አላስፈላጊ የአምልኮ ድካም ውስጥ መግባትም አይጠበቅብንም ይላል ፈላስፋው፡፡ ሞትን መፍራት ደግሞ መሠረተ ቢስ ነው ይላል፡፡ ምክንያቱም ሞት የሚያደርስብን ስቃይ ስለሌለ፡፡ “Death is meaningless to the living because they are living, and meaningless to the dead… because they are dead.”

ሞት ለሕያዉ ትርጉም አልባ ነው ምክንያቱም እየኖረ ስለሆነ፣ ለሞተውም እንደዚሁ ምክንያቱም ሞቷልና፡፡

የሞትን ፍርሃት ካሸነፉ ፈላስፎች መካከል አንዱ ሶቅራጥስ ነው፡፡ ሶቅራጥስ በትምህርቱ ወጣቶችን ይበክላል ተብሎ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ በእስር ቤት ውስጥ ያሳየው መረጋጋት በጣም ይገርም ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ብዙ ካወጉ በኋላ

“… ቆይታ አድርጌ መርዙን ብጠጣ በመቆየቴ ምንም የማተርፈው ነገር የለኝም፣ ያለቀለትን ምንም ሊሰጥ የማይችልን ሕይወት የሙጥኝ ብዬ ብጠመጠምበት እራሴን ዕርባና ቢስ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ እባክህን የምልህን ብቻ አድርግ እናም መቃወም አያስፈልግም”[5]

ብሎ የምድር ቆይታውን የምታሳጥረውን መርዝ እንዲያመጡለት ጠቀየቃቸው፡፡ መርዙንም ከጠጣ በኋላ ሌሎች ጓደኞቹ በለቅሶ ሲነፋረቁ እሱ ተመልሶ ያጽናናቸው ነበር፡፡

“ወዳጆቼ ምን እያደረጋችሁ ነው? ምን እንግዳ ባሕሪ ነው የምታሳዩት! ሴቶቹን ከክፍል ለቀው እንዲሄዱ አስቀድሜ ያደረኩበት ምክንያት ይህን መሳዩን ሁከት ለመከላከል ነበር፣ ምክንያቱም የተነገረኝ ሰው ሲሞት በተረጋጋ መንፈስ መሆን ይኖርበታል፡፡ እራሳችሁን ሰብስቡ እናም ጠንካራ ለመሆን ሞክሩ” [6]

በሞት ደጃፍ ከቆሜ ሰው ይህንን የመሰለ ጠንካራ ንግግር ይጠበቃል? የዓለማችን ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት ኢንስታይንም “ሕይወቴን በሰው ሠራሽ መንገድ ማቆየት አልፈልግም” ብሎ ሞቱን በጸጋ ተቀብሏል፡፡ በሽታው ሊድን የሚችል ቀላል እንደሆነ ይነገራል፡፡

ሌላው የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ነው፡፡ እንደ ሶቅራጥስ ሁሉ በቅርቡ በሮም ፍ/ቤት ሞት እንደሚጠብቀው የተረዳው ቅዱስ ጳውሎስ መሞቱን የገለጸበት መንገድ በፍርሃትና በመርበትበት ሳይሆን የድል ዋዜማ መድረሱን በማመልከት ነው፡፡

“For I am now ready to be offered, and the time of my departure is at hand.”   

በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።              

2ኛጢሞ. 4፡6

ሰው ሕይወቱ ብዙ እንደማትቆይ በዶክተሮች ሲነገረው ምንድን ነው የሚያደርገው? ብዙዎቻችን መሞትን ስለማንፈልግ ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ወይም ስለሞት አስበንም ስለማናውቅ እስካሁን ተስመቶ የማይታወቅ አዲስ መቅሰፍት እንደመታን አድርገን እናስባለን፡፡ የሃይማኖት አስተማሪዎቻችን ለሞት እንዴት መዘጋጀት እንዳለብ ከማስተማር ይልቅ እንደማንሞት ማስተማር ይቀላቸዋል፡፡ አንድ ሰው ፈጣሪ ባርኮታል የምንለው በዚህ ምድር ላይ ረጅም ዘመናት ሲቆይ እንደሆነ ተምረናል፡፡ የሕይወት ስኬትን በረዘሜ ዕድሜ መለካት እንወዳለን፡፡ ለመሞት ጥቂት ጊዜያት እንደቀሩን ሐኪሞች ሲነግሩን፣ አእምሮአችንም እያወቀ ግን ከማናሸነፈው ጠላት ጋር አላስፈላጊ ግብግብ ውስጥ ለመግባት እንገደዳለን፡፡ ሁሌ ጥንካረ አይሠራም፣ ጥበብ እንጂ፡፡ ለማላተርፋት ወይም ለጥቂት ጊዜያት ብቻ ለማቆየት ብዬ በሕይወት በቀሩት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በሚያሳድር መልኩ ተጨማሪ ትግል ውስጥ መግባት ፋይዳው እስከ ምን ድረስ ነው? ምናልባት አንዳንድ እራስን ለሞት ማዘጋጀትም መልካም ሳይሆን አይቀርም፣ ልክ እንደ አርቲስት ፈቀዳዱ ተክለማሪያም፡፡ ፈቃዱ ተ/ማሪያም ሕይወቱን በምድር ላይ ለተወሰኑ ጊዜያት ሊያቆያት የሚያስችለውን ዕድል እምቢ ብሎ (ለሌላ ሕፃን አሳልፎ በመስጠት) ለሞት እራሱን በማዘጋጀቱ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ አስተማሪ ሐውልት ተክሎልን ሄዷል፡፡

ሰው በሞት ፊት እንዲህ ደፋር የሚሆነው ምን አግኝቶ ነው?

ከፈላስፋው ሶቅራጥስና ከቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ሁለት ዓበይት ምክንያቶችን ማየት እንችላለን፡፡

፩ኛ፡- አግባብነት ያለው ሕይወት

ምንም እንኳ ወጣቶችን በትምህረቱ ይበክላል ብለው ቢከሱትም ሰውዬው ግን ለፍትሕ፣ ለእውነትና ለትክክለኛ ሕይወት ዘመኑን የሰጠ ነው፡፡ “ያልተመረመ ሕይወት እረባና ቢስ ነው” በማለት የሚታወቀው ሶቅራጥስ ለዓለማችን ትልቅ አስተሳሰቦችን አበርክቶ አልፏል፡፡

ከሐዋሪያው ቅዱ ጳውሎስ ሕይወትም የምንረዳው ተመሳሳዩን ነገር ነው፡፡ ሐዋሪያው በራሱ አንደቤት ሲመሰክር

“መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ”

[2ኛጢሞ. 4፡6]

ይላል፡፡

እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው መጨረሻ “ያንን ባደረገው/ ባላደርገው ኖሮ” ብለው የሚቆጩበት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ በኖሩት ሕይወት ደስተኛ ናቸው፡፡ ሐዋሪያው የተጋደለው ተጋድሎ መልካም ስለሆነ ሽልማትን ይጠብቃል እንጂ ኢፒኪዩረስ እንዳለው ቅጣት ይጠብቀኛል አይደለም ያለው፡፡ ብዙ ክፉ ሥራ የሠራ ሰው መሞት ላይፈልግ ይችላል፣ ምክንያቱም ከሞትኩ በኋላ ቅጣት ይጠብቀኛል ብሎ ስለሚያስብ፡፡ አሊያም እንደገና ስህተቱን ለማረም 2ኛ ዕድል ማግኘት ስለሚፈልግ ከሞት ጋር የሚፈጥረው ግብግብ ቀላል አይሆንም፡፡ አእምሮው በተሳሳተ የሕይወት መስመር ላይ እንዳለ የሚነግረው ሰው ሞትን ቢፈራ አይፈረድበትም፡፡ ሞትን በመሸሽ አናመልጠውም፣ ሞትን የምናመልጠው በሕይወት ዘመናችን መልካም ሥራ በመሥራት ነው፡፡ ከሞት በላይ ገዝፎ ለመታየት ዛሬ ያለውን ጊዜ በአግባቡ መኖርና ከሞትን በኋላ ስማችንን የሚያስጠራ አንዳች የረባ ነገር መሥራት ነው፡፡

፪ኛ ሞት የሕይወት መጨረሻ እንዳልሆነ መገንዘብ

ሶቅራጥስም ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሞትን ከቁብ ያልቆጠሩት ሕይወታቸው ከመቃብር እንደሚያልፍ ስላመኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶቅራጥስ ሞትን ለምን እንደማይፈራና ከሞት ወዲያ ምን ዓይነት ነገር እንደሚገጥመው ሲናገር፡-

“በመጀመሪያ ስሞት ከሌሎች ጠቢባን ከሆኑ ሰዎችና ከመልካም አማልክት ጎራ እንደምቀላቀል ባላምን፣ በመቀጠልም አሁን በዚህች ምድር ካሉ ሰዎች ይልቅ እዚያ የተሻሉ ቀድመው የሞቱትን እንደማገኝ ተስፋ ባላደርግ ኖሮ በእውነቱ በሞቴ አልተከፋሁም ብል ስህተት እሆን ነበር፡፡ ይህን ካልኳችሁ ታዲያ ስሞት እራሴን መልካም ሰዎች መሃል እንደማገኘው ማረጋገጥ ትችላላችሁ፣…እዚያ ፍጹም የሆኑ መለኮታዊ ጌቶችን አገኛለሁ፡፡”[7]

ከጠቢባንና ከአማልክት ጋር ለመገናኘት የሚሄድ ሰው ሞትን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ እንጂ እንደ አንዳች አጥፊ ኃይል አድርጎ አይመለከተውም፡፡

ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- 

“ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” ቁጥር 6

ብሏል፡፡ ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት የሽልማት መሆኑን ስታወቅ ሞት ዛሬ ብመጣ “እንኳ ደህና መጣህ” ትላለህ እንጂ አትዋጋውም፡፡ ሞት ማብቂያ አይለም፣ ሕይወት ትቀጥላለች፡፡ ምንም እንኳ አሁን እያለፍንበት ያለው ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላች ብትሆንም ሁሉም እስከ ሞት ነው፣ ከዚያ ወዲያ ያለው ላሳለፍነው የመከራ ሕይወት ካሳ የምንቀበልበት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋሪያው በሌላ ቦታ “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” ያለው፡፡ ሞት የሕይወት መጨረሻ ቢሆን መልካም የሚያደርጉ ሰዎች ተጎጂዎች ይሆናሉ፡፡

ለመሞት መዘጋጀት የውስጥ ኃይልን ይጠይቃል፡፡ ከሞት ለማምለት ግን የውጭ ኃይልን ያስለምናል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም

[1] መዝሙረ ዳዊት 56፡8

[2] Philip Yancey: Where is God when it Hurst? Zondervan, Grand Rapids, 1977(p.71)

[3] ኦሽዊትዝ ሂትለር ከሚጠቀሚባቸው የማሰቃያ ካምፖች መካከል አንዱ ነው፡፡

[4] ጳውሎስ ፈቃዱ(ተርጓሚ)፣ ሌሊት (2006 ዓ.ም)፣

[5] ስንታየሁ ዘርዓብሩክ (ትርጉም)፣ የሶቅራጥስ የሕይወቱ መጨረሻ ቀናት እና ፍስፍናው (2008 ዓ.ም)  ገጽ 158፣ አዲስ አበባ

[6] እዛው ገጽ 159

[7] ስንታየሁ ዘርዓብሩክ ገጽ. 65-66

1 Comment

  1. Gezahegn kawayta kanola

    እውነት+ ፍልስፍና= የተረጋጋ ሕይወት!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *