“ኮንሶን እናስተዋውቅ” በሚል መሪ ሐሳብ በዘመን መለወጫ ቀን የተዘጋጀው የቁንጅናና ባህልን የማስተዋወቅ ውድድር በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ

“ኮንሶን እናስተዋውቅ” በሚል መሪ ሐሳብ በዘመን መለወጫ ቀን የተዘጋጀው የቁንጅናና ባህልን የማስተዋወቅ ውድድር በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ

ወጣት ታምራት ጨንፋ አስተባባሪነት የተጀመረውና ከዘመን መለወጫ በዓል ቀደም ብሎ በነበሩት ሳምንታት ተጀምሮ የነበረው ባህልን የማስተዋወቅ የቁንጅና ውድድር በስኬት መጠናቀቁን፣ አስተባባሪውን ጠቅሶ የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ፕሮግራሙ የኮንሶን ህዝብ ባህል፣ የሥራ ታታሪነት፣ ብሩህ የትምህርት አዕምሮ፣ ሰው አክባሪነትና ሌሎችንም የማህበረሰቡን እሴቶች ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

የፕሮግራሙ ዋና አስተባባሪ ወጣት ታምራት ጨንፋ፣ ለፕሮግራሙ መሳካት ድጋፍ ያደረጉትን የዞን አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ፣ ባህልና ቱርዝም መምሪያ፣ AMN Production፣ ኮንሶ ዕድገት ሆቴል፣ ጂንካ ዱላ ጠቅላላ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ድርጅትና ሌሎችንም ድርጅቶች አመስግነዋል።

“ኮንሶን እንስተዋውቅ” ከኮንሶ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር በኮንሶ ዕድገት ሆቴል መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም በ5 የተለያዩ ዘርፎች ደማቅ የቁንጅና ውድድር ዝግጅት አድርጎ ነበር።

በውድድሩ “በቆንጅት ኮንሶ/ Miss Konso 2014” ዘርፍ በተደረገው ውድድር፣ ወይዘሪት እያኤል ኩሴ በርሻ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የ2014 “ቆንጅት ኮንሶ” ሆና ተሰይማለች። ከዞን አስተዳደር ጽ/ቤት የገንዘብ ሽልማትና የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘቷም በዘገባው ተገልጿል።

በተጨማሪም “በቆንጅት ኮንሶ 2014” ዘርፍ ወይዘሪት ገነት መንግሥቱና ወይዘሪት ዮዲት ገበየሁ፣ በቅደም ተከተል 2ኛና 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል። “የአመቱ የወንዶች ውብ 2014” በተሰኘ ዘርፍም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡ ወንዶችም ዕውቅና መሰጠቱ ተገልጿል። በዚህ ዘርፍ 1ኛ የወጣው ወጣት ኩሴ መንግሥቱ መሆኑ ታውቋል።

በባህል ዘርፍ “ቆንጅት ባህል/Miss Culture 2014” ወይዘሪት መድኃኒት ኦካሶ “ቆንጅት ባህል” የተሰኘውን ማዕረግ የተቀዳጀት ሲሆን፣ ከእሷ ቀጥሎ ደግሞ ወይዘሪት ቤተልሔም ብርሃኑና ወይዘሪት ካልሶ ገለቦ 2ኛና 3ኛ ሆነው አሸንፈዋል።

በMiss Promote Konso/ ቆንጅት ኮንሶን እናስተዋውቅ” ዘርፍ ኮንሶን በማስተዋወቅ፣ ወይዘሪት ንግሥት ኩሴ 1ኛ ስትሆን ሪንዶ ደሌኔና ቤተልሔም መንግሥቱ ሁለቱም የ2ኛነት ደረጃን አግኝተዋል።

በተያያዘ ዜና፣ የኮንሶ ዞን መንግሥት ከPromote Konso ጋር በመተባባር ከ6 ወር በኋላ፣ “Back to Origin/ ወደ መገኛችን” በተሰኘ መሪ ሐሳብ፣ ሙሉ በሙሉ ባህልን የሚያስተዋውቅ የቁንጅና ውድድር ለማዘጋጀት ማቀዱን፣ Promote Konso በገጹ በኩል ይፋ አድርጓል።

ውድድሩ የቀደምት ኮንሶዎችን ባህል ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ያደጋርል የተባለ ሲሆን፣ የውድድሩ ዘርፎችና የምዝገባ ቀናት ለወደፊት እንደሚገለጹ፣ Promote Konso አስታውቋል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *