
በሳይንሱ አለም ተረት የሚመስሉ ነገሮች እውን ሆነው መታየት ጀምረዋል።በተለያየ ምክንያት ጸንሰው መውለድ ለማይችሉ ሴቶች የአብራካቸውን ክፋይ እንካችሁ የሚል ኩባንያ በይፋ ተዋውቋል።
ኤክቶላይፍ የተሰኘው የጀርመን ኩባንያ በአመት 30 ሺህ ህጻናትን በሰው ሰራሽ ማህጸን ለማቅረብ ተሰናድቻሉ ብሏል።
ከአምስት አስርት አመታት በላይ ምርምር ሲደረግበት የቆየውን ጉዳይ አሁን ወደተግባር ለመለወጥ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን፣ ሃሸም አል ጋይሊ የተሰኙት የኩባንያው የባዮቴክኖሎጂ እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው፣ “በተፈጥሮ መጸነስ የማይችሉና የካንሰር ታማሚዎች በሰውሰራሽ ማህጸን ልጃቸውን እንዲያገኙ የሚያስችል” ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ወላጆች፣ ከልጃቸው የአይን ቀለም አንስቶ እስከ ቁመት እና የማስተዋል ብቃት እንዳሻቸው መምረጥ የሚያስችል አሰራርም ዘርግተናል ሲሉ ሃሸም አል ጋይሊ ተናግረዋል።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በየአመቱ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ከ300 ሺህ በላይ ሴቶች ህይወታቸው ያልፋል። የኢክቶላይፍ ሰውሰራሽ ማህጸንም ታዲያ የነፍሰጡሮችን ስቃይና ሞት ታሪክ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
እንደ ጃፓን፣ ቡልጋሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ የውልደት መጠናቸው ተመናምኖ የህዝብ እደገታቸው እየቀነሰ ለመጣ ሀገራትም መልካም ዜና ስለመሆኑ፣ ኩባንያው ገልጿል።
የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂም ሆነ አጠቃላይ ሂደቱ መቶ በመቶ ሳይንሱን የሚከተል ቢሆንም፣ የአመለካከት ክፍተትና ግብረ ገብ ጉዳዮች ግን ፈተና እንደሚሆንባቸው፣ ሃሸም አልሸሸጉም።

በሰው ልጅ ጽንስ ላይ ሳይንሳዊ ምርምር ማድረግ የሚቻለው ለ14 ቀናት ብቻ መሆኑና ብዙ ክለከላዎች ያሉበት ጉዳይ መሆኑ ሌላው ኩባንያውን ሊያጋጥም የሚችል ችግር ነው ተብሏል።እነዚህ ችግሮች ከተቀረፉ ግን፣ ኤክቶላይፍ 400 ጽንስ በአንድ ጊዜ መያዝ በሚችሉ 75 ዘመናዊ ቤተሙከራዎቹ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል።
ሰውሰራሽ ማሕጸኖቹ ጽንሱ በእናቱ ሆድ የሚያገኘውን ሁሉ እንዲያገኝ ተደርገው የተሰሩ ናቸው ተብሏል። የተገጠሙላቸው ስክሪኖችም የጽንሱን አጠቃላይ መረጃ በየጊዜው ያሳያሉ፤ ወላጆችም እድገታቸውን በሞባይል ስልካቸው አማካይነት ባሉበት ሆነው መከታተል ይችላሉ ነው የተባለው።
የሙቀት መጠናቸውን፣ የደም ግፊታቸውን እና አተነፋፈሳቸውን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታቸውን የሚቆጣጠሩ ሴንሰሮችም ተገጠመውላቸዋል።
በሰውሰራሽ ማህጸኖች የሚያድገው ጽንስ፣ እናቶች በማህጸናቸው ከሚያሳድጓቸው ይልቅ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸውም ዝቅተኛ መሆኑን ኩባንያው የሚጠቀመውን ቴክኖሎጂ በመጥቀስ ይገልጻል።
የጽንሶቹ እድገት ከወላጆቹ ዘረመል ጋር በተያያዘ የእድገት ውስንነት የሚያስተናግድ ከሆነም በፍጥነት ለይቶ ያሳውቃል ተብሎለታል።
በሰው ሰራሽ ማህጸን የሚያድጉት ህጻናት ቋንቋ እንዲያውቁና ወላጆቻቸውን እንዲለዩ ሙዚቃዎች እና የወላጆቻቸውን ድምጾች እንዲሰሙ ይደረጋልም ተብሏል።
፥ዋነኛው አላማችን የወላጆችን ፍላጎት ማሟላት ነው” የሚለው የጀርመን ኩባንያ፣ የህግ ገደቦች መላላት ከቻሉ፣ 30 ሺህ ህጻናትን በአመት በሰው ሰራሽ ማህጸን ለማቅረብ መሰናዳቱን የዘገበው ሚረር ጋዜጣ ነው።