<strong>አ</strong><strong>ስከፊው ድርቅና የኮንሶ ህዝብ ሰቆቃ!</strong>

ስከፊው ድርቅና የኮንሶ ህዝብ ሰቆቃ!

በእርሻ መካከል የሚገኙ የቡና ተክሎች በድርቁ ምክንያት መድረቃቸውን የሚያሳይ ምስል

አስከፊው ድርቅና ረሃብ በተመለከተ የቀረቡ ሪፖርቶች

የኮንሶ ህዝብ ላለፉት 4 አመታት በተከሰተ ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት እህል ማምረት ባለመቻሉና ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በነበሩበት ግጭቶች ኢኮኖሚው ደቅቆ፣ ከአምና ሐምሌ ወር ጀምሮ ላለፉት 9 ወራት በከፍተኛ ረሃብና ሰቆቃ ውስጥ ይገኛል።

ባለፈው አመት ሐምሌ ወር አካባቢ የዞኑ የአደጋ ዝግጁነት መሥሪያ ቤት ባደረገው ጥናት 190 ሺህ በላይ ዜጎች (ከማህበረሰቡ ጠቅላላ ቁጥር 2/3ኛው ያህል) የምግብ እህል ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጹም ይታወቃል።[በኦቻ (OCHA) መረጃ መሠረት አሁን ላይ የኮንሶ ህዝብ ቁጥር ግምቱ 302 ሺህ ገደማ ነው።] በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎችም ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ በተከሰቱ የጤና ቀውሶች የ13 ህጻናት ህይወት ማለፉን፣ እንደዚሁም ደግሞ ብዙ አረጋዊያንና ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው በሪፖርቱ ቀርቧል።

ከዞን መንግሥት የአደጋ ዝግጁነት መሥሪያ ቤት መረጃ በተጨማሪ OCHA የተባለውና በግጭት ሰበብ የተፈናቀሉ ወገኖችን ሲረዳ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤትም ቀደም ብሎ አምና ሚያዝያ ወር ባወጣው ሪፖርት፣ ህዝቡ ላይ አስቸጋሪ የረሃብ ድባብ እያጠላ መሆኑን ማቅረቡ ይታወቃል።

ድርጅቱ በጊዜው ከ86 ሺህ በላይ ዜጎች በመፈናቀልና በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውንና በትንሹ 13 ሺህ ገደማ ኩንታል የእህል ድጋፍ በየወሩ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከዚህም መካከል 3ሺህ ኩንታል ብቻ ለ20 ሺህ ተፈናቃዮች መሠራጨቱንና አስፈላጊው የግብዓት ድጋፍ ካልተደረገ ነገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚሸጋገሩ በሪፖርቱ ገልጾ ነበር።

ድርቅና ረሃብ ያጠፋው የሰው ህይወት

በኮንሶ ዞን ግጭቶች ያጠፉት የሰው ህይወት እንዳለ ሆኖ፣ የዝናብ መቆራረጥ ካስከተለው ድርቅ ጋር በተያያዘም የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ከተለያዩ ሪፖርቶችና የዜና ዘገባዎች ሰምተናል። እስከ አምና ብቻ (ለዚያውም የረሃብ መረጃ በይፋ በማይወጣባቸው ወቅቶች) በትንሹ 37 ሰዎች ህይወታቸውን በረሃብ ምክንያት አጥተዋል። ይህም በ2012 ዓ.ም 5 ሰው፣ በ2013 ዓ.ም ደግሞ 19 ሰው፣ ባለፈው 2014 ዓ.ም ደግሞ 13 ሰው ህይወታቸውን አጥተዋል። የዚህ አመት ሪፖርት ገና አልወጣም። ይሁንና ግን ካለው ችግር ስፋት አንጻር የከፋ ሊሆን ይችላል።

ችግሩን ለመቅረፍ በቂ ዕገዛ አለመደረጉ

OCHAም ባስቀመጠው ሪፖርት መሠረት ረጅ ድርጅቶችም ሆኑ መንግሥት በቂና ቀጣይነት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የኮንሶ ህዝብ 2/3ኛው ለረሃብ መጋለጡ አልቀረም። በወቅቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በራሳቸው የተለያዩ ጉዳዮች ተይዘው ግልጽ የመፍትሔ እርምጃዎችን ሲያደርጉ ባይታዩም፣ የኮንሶ ልማት ማህበርና በየሥፍራው ያሉ የኮንሶ ተወላጆችና ምሁራን በጋራ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። እህል ገዝቶ በልማት ማህበሩ በኩል ለተጎጂዎች እንዲደርስ እንዲሁም እህል የሚገዛበትን ገንዘብ በማዋጣት የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ልማት ማህበሩም በበኩሉ፣ የተለያዩ አካባቢ ካሉ መሰል የልማት ማህበሮችና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ግንኙት በማድረግና ስለህዝቡ ሰቆቃ በማስረዳት ህዝቡን ለመታደግ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። በወቅቱም የኮንሶ ተወላጆችና የልማት ማህበሩ ጥረትና ድጋፍ በመንግሥት ዕውቅና ባይሰጠውም መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ፣ ኮንሶ ዜና ዘግቦት ነበር።  ይሁንና ከችግሩ ስፋት አንጻር በልማት ማህበሩ ትብብር የተሰበሰበው ድጋፍ ትንሽ ነበር።

አምና ችግሩ በታወቀ ጊዜ የነበረው የመንግሥት ምላሽ

በወቅቱ ከክልል መንግሥት ጀምሮ እስከ ዞን አመራር ባሉት ወገኖች ዘንድ ሪፖርቱ ከታወቀ በኋላም፣የአካባቢውን (መንግሥታት) ገጽታ ያጠፋል በሚል መንግሥት ራሱ ለችግሩ መፍትሔ እስኪያመጣ ችግሩ በይፋ እንዳይታወቅ ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውን፣ በተደጋጋሚ በኮንሶ ዜና በኩል መዘገባችን አይዘነጋም። በወቅቱ በመንግሥት በኩል የተያዘ አቋም በሚመስል ሁኔታ፣ የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ “ድርቅ ነው እንጂ ረሃብ በኮንሶ የለም” እስከ ማለት የደረሱበት ሁኔታ መፈጠሩም አይዘነጋም።

የረሃብ ክስተቱን ለመሸፋፈን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ የዞን መንግሥት አመራር አካላትም በስተመጨረሻ ሁኔታው ሊሸፍኑት ወደማይቻልበት ሁኔታ መድረሱን ሲገነዘቡ፣ እነሱም ህዝቡ ዕርዳታ እንዲያገኝ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ተገደዋል።

አሁናዊው የድርቅ ሁኔታና የኮንሶ ህዝብ ሰቆቃ

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ የኮንሶ ህዝብ 2/3ኛ ለረሃብ የተጋለጠ ከመሆኑ አንጻር በቂ ነው ሊባል የሚችል ድጋፍ ለህዝብ ሊቀርብ አልቻለም ነበር። የቀረበው ድጋፍ በተወሰነ መልኩ ከተጎጂዎች መካከል የተወሰኑ ሰዎችን ችግር ያስታገሰ ቢሆንም፣ በቂ አልነበረም። በቂ ካለመሆኑም ባለፈ፣ ተከታታይነትና ቀጣይነት ያለው አልነበረም። አሁን ላይ ለረሃብ የተጋለጠው የኮንሶ ህዝብ ከ2/3ኛው የህዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምናባልትም እስከ 85% የኮንሶ ህዝብ በከፍተኛ ረሃብና ሰቆቃ ውስጥ ይገኛል።  

በማህበረሰቡ ዙሪያ የነበሩ ግጭቶችም አሁን ላይ በሰላም የተተኩ ቢሆንም፣ የዝናብ እጥረቱና ድርቁ ለ4ኛ አመት አሁንም እንደ ቀጠለ ነው። ህዝቡ ለተከታታይ 4 አመታት ምንም እህል ማምረት አልቻለም። አሁን ላይ የዞን መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተናገሩ ይገኛሉ።

ላለፉት 4 አመታት አርሶ አደር የሆነውን የኮንሶን ህዝብ ኢኮኖሚ ያደቀቀው ድርቅ፣ አጎራባች ዞኖች ላይም ተጽዕኖው በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ይገኛል። ከነዚህም መካከል አጎራባች የቦረና ዞን ተጠቃሽ ሲሆን፣ አርብቶ አደር የሆነው የቦረና ህዝብ በድርቁ ምክንያት ከብቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ እያለቁበትና ሰዎችም በድርቁ ሳቢያ በተከሰተ ድርቅ ህይወታቸውን እያጡ መሆናቸው፣ በተለያዩ ሚድያዎች እየተዘገበ ይገኛል።

የግጦሽ መሬቶች በድርቁ ምክንያት መጎዳታቸውን የሚያሳይ ምስል

የኮንሶ ዞን ህዝብ ሁኔታም ከአምናው እየከፋና እየባሰበት ይገኛል። ኮንሶ ዜና ሚድያ በራሱ ባደረገው ማጣራት፣ አሁን ላይ በኮንሶ አንዳንድ አካባቢዎች ከአምናው በከፋ ሁኔታ ሰዎች ሰቆቃ ውስጥ ይገኛሉ። አርባፓክላላ በተባለ የኮልሜ አካባቢ ከብቶች በድርቁ ምክንያት እየሞቱ ስለመሆናቸው መረጃዎች ለኮንሶ ዜና ሚድያ እየደረሱ ይገኛሉ። በተለያዩ የኮንሶ አካባቢዎች የሚገኙ የዝናብ ውሃ ማጠራቀሚያ ኩሬዎች ሙሉ በሙሉ በዝናብ እጥረት ምክንያት ደርቀዋል።

በኮንሶ ዞን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ቀይ ማሽላና በቆሎ በተመሳሳይ ዋጋ እየተሸጠ ያለ ሲሆን፣ በኩንታል እስከ 4500 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ይህ ዋጋ በከተሞች ጤፍ ከሚሸጥበት ዋጋ እኩል የሆነና በአንዳንድ ከተሞች እንዲያውም ጤፍ ከሚሸጥበት ዋጋም ከፍ ያለ ነው።

ኑሮ አስቀድሞ በጦርነት የወደመበት አርሶ አደር፣ በአንድ ወገን ከብቶች በመኖ እጥረት እያለቁበት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የምግብ እህል ዋጋ ሰማይ ነክቶ፣ ምድር ምንም ፍሬ ሳትሰጥ 4 አመታት ተቆጥረው ህዝቡ እንዴት ይዘልቀዋል!?

በተመሳሳይ በአንዳንድ የኮንሶ አካባቢዎች ምግብ መግዛት በማይችሉ ቤተሰቦች መካከል ህጻናት፣ አረጋዊያንና ጎልማሶች ሳይቀሩ በምግብ እጥረት ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል። ነገሮች ከህዝቡ ቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። ህዝባችን ትልቅ አደጋ ላይ ነው። በከተሞች አካባቢ ከሚገኙና በደመወዝ ከሚተዳደሩ የተወሰኑ ሰዎች በስተቀር መላው አርሶ አደር የኮንሶ ህዝብ በከፍተኛ ርሃብና ሰቆቃ ውስጥ ይገኛል።

ለመፍትሔ ምን እየተደረገ ነው?

አሁን ላይ በመላው ኢትዮጵያ የሚድያዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው የቦረና ህዝብ ረሃብና ሰቆቃ ላይ ሚድያዎች በመረባረብ ላይ ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን ከ9 ወር ጊዜ በፊት ጀምሮ ሲጮህበት የነበረው የኮንሶ ህዝብ የረሃብ ሰቆቃም፣ የሚድያዎችን ትኩረት እያገኘ ይገኛል።

አንዳንድ እንደ EBC እና ደቡብ ቴሌቪዥን ያሉና በህዝብ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱ ሚድያዎች፣ መረጃዎችን በኃላፊነትና በጥንቃቄ የማደራጀት ችግር ቢኖርባቸውም፣ የኮንሶውንም ረሃብ በተዛባ ሁኔታም ቢሆን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ። የኮንሶ ዞን የግብርና መምሪያ፣ “8ሺህ 303 ተማሪዎች በቤታቸው ባጋጠማቸው የምግብ እጥረት ምክንያት በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እየቻሉ አይደለም” ብሉ ያቀረበውን መረጃ በማዛባት፣ “በኮንሶ ዞን 800ሺህ በላይ የኮንሶ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል” በሚል የተዛባ መረጃ በመዘገብ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው የኮንሶ ህዝብ ጠቅላላ ብዛት 302 ሺህ ገደማ ነው። የነዚህ ሚድያዎች ዘገባ፣ መሬት ላይ ካለው ዕውነታ ፈጽሞ የራቀ ነው።

ለድርቁ ድምጽ መሆናቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ሚድያዎች ላይ ተቀጥረው በጋዜጠኝነት የሚሠሩ ባለሙያዎች ከፍተኛ የአቅምና መረጃን በኃላፊነት ስሜትና በጥንቃቄ የማደረጀት ውስንነት እንደሚስተዋልባቸው ማሳያ ሆኗል።

ወደ ጉዳያችን ስንመለስ፣ ድርቁ ያስከተለው ረሃብ በኮንሶ ዞን እየተባባሰ ስለመሄዱ ዘገባዎች መውጣት  ከጀመሩ ወዲህ፣ ከመንግሥትም ቀድሞ ለሰብዓዊነት ድጋፍ ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሆኖለች።

በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ (የካቲት 3፣ 2015 ዓ.ም) በካርድናል ብርሃነ ኢየሱስ ደብረ ሱራፌል የተመራ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የልዑካን ቡድን እስከ ኮንሶ ዞን ድረስ በአካል በመገኘት ለህዝቡ አጋሪነታቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መግለጻቸው ተዘግቧል። በአካል በተገኙበት ጊዜ ከ50 ኩንታል የማያንስ የምግብ እህል ግብዓቶችን መለገሳቸው በዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በኩል የተዘገበ ሲሆን፣ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ፕሮጀክት ነድፋ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ዘግቧል። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እናመሰግናለን! ይሁንና አሁንም ከችግሩ ስፋት አንጻር በጣም ትንሽ ነው። ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም ሊረባረቡ ይገባል።

ካርድናል ብርሃነ ኢየሱስ ከኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ጋር

አሁንስ ለመፍትሔ ምን ይደረግ?

ችግሩ ይህን ያህል ሰፊ ከሆነና ችግሩን ከመቅረፍ አንጻር ከፍ ያለ አቅም ያላቸው ድርጅቶች ገና መንቀሳቀስ ካልጀመሩ፣ በዚህ መሃል የብዙ ዜጎች ህይወት እንዳይጠፋ የተለያዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

በመጀመሪያ በዞን ደረጃ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አሁን እያደረጉ እንዳሉ ሁሉ፣ በቂና ዘላቂነት ያለው ዕርዳታ እስኪገኝ ድረስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የህዝባችንን ሰቆቃ በተገኙበት መድረክ ሁሉ ለማስረዳት ይሞክሩ። የደቡብ ክልል መንግሥት በመፍረስ ሂደት ላይ ያለና በሌሎች ጉዳዮች የተወጠረ ከመሆኑ አንጻር በዚህ ጉዳይ ዕገዛ ለማድረግ ብዙም አቅም ወይም ትኩረት ላይኖረው ስለሚችል፣ በተቻለ መጠን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንን ጭምር በመጠቀም ፌዴራል መንግሥት አካባቢ ድጋፍ እንዲገኝ በአመራር በኩል ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት። መንግሥት ለድጋፍ ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር፣ ይህ ችግር በጥቂት ረጅ ድርጅቶችና በአካባቢው ተወላጆች ወይም በማህበረሰቡ እርስ በርስ መደጋገፍ የሚገፋ አይደለም።

የኮንሶ ልማት ማህበር፣ ቀደም ሲል ከኮንሶ ምሁራንና ተወላጆች ጋር በመተባበር ዕርዳታ በማሰባሰብ ረገድ ታሪካዊ ሚና እንደተጫተ ይታወቃል። የኮንሶ ህዝብ የበለጠ የሚያምነው ብቸኛ ኮንሶ በቀል ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ በቂ ረጅ ድርጅቶች መርዳት እስኪጀምሩ ድረስ፣ ከዞን መንግሥትና ከኮንሶ ምሁራን ጋር በመወያያት ዕርዳታ የማሰባሰብ ዕርምጃ ውስጥ እንዲገባና ሁላችንም እንደከዚህ በፊቱ ተረባርበን ጉዳት በመቀነሱ ሂደት የበኩላችንን ሚና ብንወጣ መልካም ነው።

በመጨረሻም፣ ችግሩ ከተፈጥሮ መዛባት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን እግዚአብሔር ምድራችንን እንድታረቃትና በልምላሜ እንዲጎበኛት ሰውም ሆነ እንስሳትም በዚህ ጉስቁልና እንዳይቀጥሉ፣ ሁሉም ሰው ስለኮንሶና ድርቅ ስለሚያቸግራቸው ሌሎች አካባቢዎች ወደ ፈጣሪያችን ወደ እግዚአብሔር ቢጸልይ መልካም ነው እንላለን።

እግዚአብሔር ህዝባችንን ከዚህ ረሃብና ጉስቁልና ይታደግልን!

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *