ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ12ኛውን ክልል ህዝበ ውሳኔ የድምፅ መስጫ ቀን አሳወቀ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ12ኛውን ክልል ህዝበ ውሳኔ የድምፅ መስጫ ቀን አሳወቀ

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለተነሳው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚል ሊካሄድ በታሰበው የህዝበ ውሳኔ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በዚህ ውይይት ላይ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቦርዱ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ የወሰነውን ውሳኔ ማስፈጸም የሚችልበትን እቅድ ይፋ አድርጓል።

በቦርዱ እቅድ መሰረት በደቡብ ክልል ስር ባሉት ስድስት ዞኖች እና አምስት ወረዳዎች ላይ የህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ ቀን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚሆን አስታውቋል።

የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦና የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ደግሞ ህዝበ ውሳኔው የሚካሄድባቸው አስተዳደራዊ መዋቅሮች ናቸው። ቦርዱ በህዝበ ውሳኔው 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ ድምጽ እንደሚሰጥም አስታውቋል።

አርባ ምንጭ ከተማ የህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ማዕከል ይሆናል የተባለ ሲሆን የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንደሚቀጥሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፍነው ነሀሴ መወሰኑ ይታወሳል።

በውይይት መድረኩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በቦርዱ ጊዜያዊ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ ቀን ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የጉራጌ ዞን ከሀዲያ፤ ከስልጤ፣ ከከንባታ ጠንባሮ ዞኖችና ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በክላስተር ተደራጅቶ ክልል እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *