በድርቅ ለተጎዱት እርዳታ ተደረገ

በድርቅ ለተጎዱት እርዳታ ተደረገ

በሐዋሳ የሚኖሩ የኮንሶ ተወላጆች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 18 ኩንታል የበቆሎ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ

በሐሳዋ ከተማ የሚኖሩ የኮንሶ ምሁራንና ተወላጆች በድርቅና በግጭቶች ምክንያት ለረሃብ ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ የሚሆን፣ 18 ኩንታል በቆሎ መለገሳቸውን የዞኑ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

የእህል ድጋፉ በአቶ ኩሲያ በቀለና በአቶ ገረሱ ካውሶ እጅ ለዞን አደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት መድረሱ፣ በዘገባው ተገልጿል። ድጋፍ በሐሳዋ ከተማ የሚኖሩ የኮንሶ ተወላጆች ለድጋፉ ባሰባሰቡት 52 ሺህ 200 ብር የተገዛ ነው ተብሏል።

ከ190 ሺህ በላይ ዜጎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን፣ የአደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት መረጃን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። የኮንሶ ምሁራን ከኮንሶ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በ2 ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ ተግባት መፈጸማቸውም አይዘነጋም።

በመጀመሪያ ዙር በምሁራንና በልማት ማህበር የጋራ ርብርብ ከ445 ኩታል በላይ የእህል ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም፣ የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤትም ሆነ የዞን አስተዳደሩ ጽ/ቤት ድጋፉን ዕውቅና በመንፈጋቸው ከፍተኛ ትችት ሲደስባቸው እንደነበርም አይዘነጋም።

የዞኑ የአደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገደኖ ካዋይታ የሐዋሳውን ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት፣ ከተለያዩ ተቋማት የተሰበሰበውና ለጽ/ቤታቸው የደረሱ ዕርዳታዎች አሁንም በቂ አለመሆናቸውንና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።

በድጋፍ እህሉ ርክክብ ወቅት፣ ሌሎችም የዞን መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች መገኘታቸውና ድጋፍ ላደረጉ የሀዋሳ ምሁራን ምሥጋና ማቅረባቸው ተገልጿል።