በኮንሶ ዞን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ መሥመር ተመርቆ መከፈቱ ተገለጸ

በኮንሶ ዞን የመብራት ችግር ኅብረተሰቡ ለአመታት ቅሬታ ከሚያቀርብባቸው አገልግሎቶች አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በወር መብራት ከሚበራባቸው ቀናት ይልቅ የማይበራባቸው ቀናት እንደሚበዙ፣ በየጊዜው ከማህበረሰቡ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች ለማወቅ ተችሏል። ይህም ኅብረተሰቡንና በዞኑ የሚገኙ ተቋማትን ለከፍተኛ ኪሣራ ሲዳርግ ኖሯል።

ከዚህም የተነሳ የመብራት አገልግሎት የሚፈልጉ እንደ ባንክ ቤቶችና ሌሎችም አነስተኛ እኝዱስትሪዎች ጄነሬተር ለመጠቀም በመገደዳቸው ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረጉም መቆየታቸው፣ ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ባንኮችም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት የአርባምንጭ ዲስትሪክት ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸው፣ ከዚህ በፊት መዘገባችን አይዘነጋም።

ይሁንና በትላንትናው ዕለት ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ መሥመር፣ የመብራት መቆራረጡን ችግር ይቀርፋ ተብሎ፣ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት ሆኗል።

ይህ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል መሥመር፣ ከዚህ በፊት ለመብራት መቆራረጡ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሲገለጽ የነበረውን የብዙ አካባቢዎች የኤሌክሪክ መሥመር አንድ ላይ መሆን ችግርን የቀረፈ መሆኑን፣ የአርባምንጭ ዲስትሪክት የኤሌክሪት አገልግሎት ኃላፊዎችን ጠቅሶ የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል።

ከዚህ በፊት የኮንሶ ዞንና በጋሞ ዞን የከንባ ወረዳ የመብራት ኃይል በአንድ መሥመር የሚጓዝ መሆኑ፣ ለተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ ችግሮች እንደ ምክንያትነት ሲጠቀስ ኖሯል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአርባምንጭ ዲስትሪክት ጽ/ቤት በራሱ አቅም በ42 ሚሊዮን ብር ወጪ የኮንሶ ዞንንና የከንባ ወረዳን የመብራት ኅይል መሥመሮች የመለየት ሥራ መሥራቱ ተገልጿል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የካራት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍሬዘር ኮርባይዶ፣ የካራት ከተማና ብሎም የኮንሶ ዞን የመብራት ችግር ከሚገለጸው በላይ ኅብረተሰቡ የተማረረበት የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመቅረፍ የአርባምንጭ ዲስትሪክት ጽ/ቤት ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል። “ዲስትሪክቱ የጀመራቸውን ተግባራት በማጠናከርና የመብራት መቆራረጡን ችግር ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የኮንሶን ህዝብ መካስ ይገባል”ም ብለዋል።

የአርባምንጭ ዲስትሪክት ጽ/ቤት የምሥክር ወረቀት ሲቀበል

የኮንሶ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት በበኩሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አርባምንጭ ዲስትሪክት ጽ/ቤት ላደረገው ችግር ፈቺ ተግባር የምስክር ወረቀት እንደባረከተለት፣ በኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ ዘገባ ተመልክቷል።

የኮንሶ ዞን የኤሌክሪክ ኃይል መሥመር ከከንባ ወረዳ ተለይቶ ለብቻው መደረግ ዜና ብዙዎች እንደመልካም ዜና የተቀበሉት ቢሆንም፣ የመብራት ችግር በኮንሶ ዞን ዘመናትን ያስቆጠረና በአንዳንድ ተቋማት መካከል ውዝግቦችን ያስከተለ እንደመሆኑ “ውጤቱን በተግባር ማየት ይሻላል” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አልታጡም።

ከ50 በላይ ሰፋፊ ቀበሌያትና የከተማ አስተዳደሮች ባሉበት የኮንሶ ዞን የመብራት ጉዳይ ገና ብዙ መጤን ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመብራት ዝርጋታ ጉዳይ ምኑም እንዳልተነካ በመግለጽ አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖችም አሉ።

እንደ ደቡብ ራድዮና ቴሌቪዥን ዘገባ፣ በመላው የደቡብ ብሔር ብሔርሰቦችና ህዝቦች ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን 42% ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ሽፋንም ከግማሽ በላይ መሥመሮቹ ያረጁና የተበላሹ ናቸው።   

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *