
በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ የጸጥታ ሥጋቶች ተቀርፈው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ከአጎራባችን ልዩ ወረዳዎች ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑን፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ አስታወቁ።
አስተዳዳሪው ይህንን የተናገሩት በገና ዋዜማ ወረዳውን በጎበኙበትና በወቅታዊ አካባቢያዊ ጉዳዮችና በመጪው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ ዙሪያ ከወረዳው አመራርና ነዋሪዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።
የሰገን ዙሪያ ወረዳ፣ አከባቢው ላይ በመሸጉና ከአጎራባችን የዲራሼ ልዩ ወረዳ በሚነሱ ጸረ ሰላም ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና በተደጋጋሚ በተደረጉ ህግ የማስከበር ተግባራትና በቅርቡም ከአጎራባች የዲራሼ ልዩ ወረዳ ህዝብና አመራር ጋር የሰላም ኮንፍራንሶች መደረጋቸውን ተከትሎ፣ የአከባቢው ሰላም እየተመለሰ ይገኛል።

ዋና አስተዳዳሪው ከሰገን ዙሪያ ወረዳ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ በቀደሙት ግጭቶች ወቅት ከቀዬያቸው ተፈናቅለው እስከ አሁንም ድረስ ወደ መኖሪያቸው ያልተመለሱና ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ስለመኖራቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በርሻ ኦላታ አስታውቀዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የወረዳው ነዋሪዎች፣ ባለፉት ጊዜያት ባለማወቅ የጠፉ ጥፋቶች ከእንግዲህ እንዳለፉ በማሰብና ይቅር በመባባል፣ አሁን የተገኘውን ሰላም በማስቀጠል ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ቃል ገብተዋል።
በዚህ ሁሉ ችግርና ግጭቶች መሃል የአብሮነት እሴቶችን በማጉላት፣ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ ሰላም በቀጠናው እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ግለሰቦች የምሥጋና የምስክር ወረቀት መበርከቱን፣ የዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤት አስታውቋል።
