በኮንሶ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

በኮንሶ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

በኮንሶ የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የመማር ማስተማር ግብዓቶች እጥረት እንዳለባቸውና ከዚህም የተነሳ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደተፈጠረ የኮንሶ ዜና የመረጃ ምንጮች ገለጹ።

ትምህርት ቤቶቹ የቤተ መጻሕፍትና የተማሪዎች መጻሕፍት እጥረት ያለባቸውና ከመሆናቸው የተነሳ፣ መምህር በጥቁር ሰሌዳ ላይ ከሚጽፉላቸው ማስታወሻ ውጭ ምንም የመማሪያ ግብዓቶች እያገኙ እንዳልሆነና ከዚህም የተነሳ የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ መሆኑ ተገልጿል።

ከነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል የአንዳንዶቹ ርዕሳነ መምህራን ለኮንሶ ዜና ምንጮች እንደገለጹት፣ ችግሩን እንዲቀረፍላቸው በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው ተቋማትንና ሌሎችም ሊያግዙ ይችላሉ ብለው ያሰቧቸውን ተቋማት ደጅ ለዕርዳታ ብያንኳኩም ምንም የተለወጠ ነገር የለም ብለዋል።

ከነሐሴ 26-28 ቀን 2014 ዓ.ም በተደረገው የኮንሶ ምሁራን የምክክር ጉባኤ ወቅት በዞን ደረጃ እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የዞኑ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በአገር አቀፍ ተወዳዳሪና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሚታወቁ ተማሪዎችን ሲያፈራ ለኖረ የኮንሶ ዞን አይመጥንም ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ሰኞ መስከረም 3 ቀን 2015 የተደረገውን የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከትሎ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሆነው በካራት ዙሪያ ወረዳ የበዓይዴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንና በካራት ከተማ አስተዳደር የድታታ ባናና የኮሪያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መጎብኘታቸው ተገልጿል። ባለፈው ሰኞ በደቡብ ክልል በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የኮንሶ ተወላጅ ምሁራን በተገኙት የዞኑ መንግሥት የትምህርት ዘመኑን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ማስጀመሩ አይዘነጋም።

የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት፣ ስለጉብኝቱ ዓላማም ሆነ ከፍተኛ አመራሩ በጉብኝቱ ወቅት ስላስተዋሏቸው የትምህርት ቤቶቹ ችግሮች ምንም የገለጸው ነገር የለም። ነገር ግን አመራሩ ያደረጓቸውን ንግግሮችና ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ምክር ስለመለገሳቸው፣ እንዲሁም መልካም የትምህርት ዘመን መመኘታቸው ተዘግቧል።

ተማሪዎች ከባለፈው አመት የተሻለ ውጤት እንዲያመጡም ጠንክረው እንዲሠሩ ከመምከራቸው በስተቀር፣ ስለግብዓት አቅርቦት ያነሱት ነገር ስለመኖሩ የኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ የዘገበው ነገር የለም።

ማስታወሻ፡ ከዜናው ጋር ተያይዞ የምትመለከቱት የመጻሕፍት ክፍል ፎቶግራፍ፣ ከተወሰነ ጊዜ በፊት የተነሳ በኮንሶ ዞን የሚገኝ የአንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት ምስል መሆኑን መግለጽ እንወዳለን።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *