
በኮንሶ ዞን በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ የተነገረለት አገር በቀል የአካል ጉዳተኞች ማበልጸጊያ ተቋም መቋቋሙን፣ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ሰንበቶ ለኮንሶ ዜና በላኩት መረጃ አስታወቁ።
“ሰሊሆም የአካል ጉዳተኞች ማበልጸጊያ ማህበር” የሚል መጠሪያ እንዳለው ኃላፊው የተናገሩ ሲሆን፣ መንግሥታዊ ያልሆነ፣ ለንግድ ያልተቋቋመ፣ ሃይማኖታዊ ተቋም ያልሆነና ዓላማውን የአካል ጉዳተኞች ህይወት መለወጥ ላይ ብቻ ያደረገ የበጎ አድራጎት ማህበር መሆኑን በመረጃው አብራርተዋል።
ማህበሩ በዞን ደረጃ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ የምዝገባ ሂደቱን እንደሚያከናውን አቶ ዘነበ ለኮንሶ ዜና በላኩት መረጃ ገልጸዋል። ማህበሩ እስከ አሁን ባደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የኮንሶ አካባቢ ለሚገኙና የተለያዩ የአካል ጉዳት ላለባቸው ወገኖች፣ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥልጠናዎችን መስጠቱንና ብዙዎችን ከተደበቁበት ለመጀመሪያ ጊዜ መውጣት በመቻላቸው እጅግ መበረታታቸውን ተገልጿል።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ሰንበቶ፣ የማህበሩ አባል መሆን ያለ ልዩነት ለሁሉም ባለቅን ልብ ዜጎች ሁሉ መሆኑን ተናግረው፣ መሳተፍ የሚፈልግ ሁሉ የማህበሩ አባል በመሆን አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት የሚደረገውን ርብርብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

