
በኮንሶ ዞን ኮልሜ ክላስተር፣ በቀጠናዊ ሰላምና አንድነት ዙሪያ ከቀበሌ አመራርና ከሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች ለኮንሶ ዜና ገለጹ።
ውይይቱ በዋናነት በኮልሜ ህዝብና በአጎራባችን የአሌ ማህብረሰብ መካከል ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም በውይይቱ መነሳታቸው ተገልጿል።
ውይይቱ የተካሄደው የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁና ሌሎች የዞን አመራር ጭምር በተገኙበት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የቀጠናውን ሰላም በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በቅርቡ በኮልሜና በገዋዳ መካከል የዕርቀ ሰላም ኮንፍረንስ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል። የትላንትናው ውይይትም በኮልሜና በገዋዳ ህዝቦች መካከል ሰላምና አንድነትን በዘላቂነት ለማስፈን መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራት በሰፊው መነሳቱ ታውቋል።
በየጊዜው የግጭት መነሻ ተደርጎ የሚነሳው የኩኩፓ ሳላ መሬትና ሌሎችም የወሰን አካባቢ የግጦሽ መሬቶች በውይይቱ የተነሱ ሲሆን፣ ለዚህም መንግሥት የሁለቱንም አካባቢ ህዝቦች ባሳተፈና መሬት ላይ ያለን ነባራዊ ሁኔታን በትክክል ከግምት ባስገባ መልኩ መፍትሔ እንዲያበጅለት ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህ በፊት እንደ አንድ ህዝብ አብረው የኖሩ፣ በደምና በባህል የተጋመዱ ህዝቦች ተገቢ ባልሆነና በመንግሥት መፍትሔ ሊያገኝ በሚችል ምክንያት አንድነታቸውና ሰላማቸው ሊደፈርስ አይገባምም ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሐሳብ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ ኮልሜ ክላስተር ወረዳ አለመሆኑና ትክክለኛ የአስተዳደር መዋቅር አለማግኘቱ ጋር ተያይዞ፣ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡን አንድ አድርጎ የሚሰብሰብ አመራር አለመኖሩ፣ በህዝብ ጥረት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት እየተንቀሳቀሰ አለመሆኑና በክላስተር ደረጃ ህዝብን የሚመራ አካል ባለመኖሩ አንዳንድ አላስፈላጊ የዘረፋ አዝማሚያዎችም በአንዳንድ አካባቢዎች በመታየት ላይ መሆናቸው ተነስቷል።
ከዚህ በፊት ሙሉው የኮልሜ አካባቢ “ኮልሜ ክላስተር” በሚልና ፖለቲካዊ ፋይዳው በግልጽ በማይታወቅ አወቃቀር አመራር በኮሚቴ ደረጃ ተዋቅሮለት ሲተዳደር የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክላስተር ደረጃ ያለው አመራር መፍረሱንና የመንግሥት አስተዳደር በቀበሌያትና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ብቻ እንደሚገኝ ተገልጿል። ይህ ሁኔታ ለህገ ወጦችም ዕድል እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ይፈልጋልም ተብሏል።
በትላንትናው ስብሰባ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ አላስፈላጊ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ በኮልሜ ክላስተር ውስጥ የሚገኙ ቀበሌያት ሊቀመናብርት ከኮልሜ ከተማ አስተዳደር ጋር እንዲተሳሰሩና እንዲናበቡ መደረጉንም፣ የመረጃ ምንጮቻችን ተናግረዋል።
ሰላምንና አንድነትን የማስጠበቅ ውይይቱም በሁሉም ቀበሌያት ደረጃም እንዲወርድ ውሳኔ ላይ መደረሱን፣ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለመረዳት ተችሏል።