በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ በእንስሳትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ

በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ በእንስሳትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ

በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ በዓይዴ ቀበሌ ሰሞኑን የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በእንስሳትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን፣ የወረዳውን የአደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ኃላፊን ጠቅሶ የዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

የካራት ዙሪያ ወረዳ አደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገሠሠ ኦላታ ለኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት እንዳስታወቁት፣ ዝናቡ ያስከተለው ጎርፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳትን፣ የችርቻሮ ሱቆችንና የእህል ወፍጮ ማሽኖችን ጭምር ጠራርጎ መውሰዱ ተገልጿል።

ከዕሮብ መጋቢት 13 ቀን ምሽት መጣል እንደጀመረ የተገለጸው ይኸው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ 250 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ማውደሙንና 165 አባወራዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀሉም ተገልጿል።

በተለይም ጎርፉ የተከሰተው ሌሊት ላይ መሆኑ፣ ንብረቱን ማዳን እንዳይቻል ማድረጉንና የአካባቢውንም ማህበረሰብ ለከፍተኛ የስነ ልቦና ጉዳት መዳረጉም ታውቋል። ጉዳቱም ድንገተኛ በመሆኑም በዚህ የጎርፍ አደጋ ንብረታቸውን ያጡና ከቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ለከፋ ችግር ከመጋለጣቸው በፊት፣ መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ከብዙ አመታት የዝናብ መቆራረጥና ድርቅ በኋላ ሰሞኑን በኮንሶና በአጎራባችን የደቡብና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከፍተኛ ዝናብ ጎርፍ በማስከተልና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርድ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 5 ሰዎችን ጨምሮ፣ የ12 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉንና ብዙ ከብቶችንም መውሰዱ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *