
ከዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቆይና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ለአሠልጣኞች ሥልጠና ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተሰበሰቡ መምህራን ሊሰጥ መሆኑን፣ የእንፑርሻ አነቃቂ እንቅስቃሴ መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑትና የልዩ ሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ለኮንሶ ዜና ተናግረዋል።
ሥልጠናው ናታን የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ድርጅት፣ እንፑርሻ አነቃቂ እንቅስቃሴና የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።

ሥልጠናው አንጋፋ በሆነው የኮንሶ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከሚያስተምሩ በመላው የኮንሶ ዞን ከሚገኙ መለስተኛና ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ፣ ርዕሳነ መምህራንና የተማሪዎች አማካሪ መምህራን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማና ትኩረት መምህራን የተማሪዎችን ተፈጥሯዊ ዝንባሌና ክህሎት በመለየት በዚያው የዝንባሌ መሥመር “ተማሪዎችን ለወደፊት ህይወታቸው እንዲያዘጋጁና የአልህቆት ሥራ እንዲሠሩ ለማስቻል ያለመ ነው” ተብሏል።
የአሠልጣኞቹን ሥልጠና የሚሰጡት የሥነ ልቦና ባለሙያ ዶ/ር ሙላቱ በላይነህ በትላንትናው ዕለት ኮንሶ ካራት ከተማ መግባቸው የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ለኮንሶ ዜና ገልጸዋል።

ባለሙያው በሥልጠናው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚሠራ አማካሪ ድርጅት ያላቸው፣ በዘርፉም የ28 አመታት የሙያ ልምድ ያላቸውና በተለይም የተማሪዎችን ውስጣዊ ዝንባሌን ለይቶ በዚያው ዝንባሌ መሠረት እንዲያድጉ፣ የአልህቆት ሥራ ለመሥራት መንገድ የሚጠቁም “ትምህርት ቤቶችን መሠረት ያደረገ ተግባረ አልህቆት” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍንም የጻፉ በሙያው አንጋፋና በአገር አቀፍ ደረጃ የታወቁ ደራሲም መሆናቸው ይታወቃል።
ናታን የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ድርጅት መቀመጫውን በአሜሪካዋ ዳላስ ግዛት ያደረገና ቤተሰብን ማከም፣ ማበልጸግና ልጆችን ለተፈጠሩበት ዓላማ እንዲዘጋጁ ለመርዳት፣ ወላጆችንና ትምህርት ቤቶችን የሚያሰለጥን ድርጅት ሲሆን፣ የድርጅቱ መሥራችም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ሥልጠናዎች ለመምህራን እየሰጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ በሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይም እየቀረቡ በልጆችና በቤተሰብ ጉዳዮች በማስተማር የሚታወቁ የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸው።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ እሑድ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሰጠው ሥልጠና የሚካፈሉ ርዕሳነ መምህራንና የተማሪዎች አማካሪ መምህራን ወደየመጡበት ትምህርት ቤቶች ሲመለሱ፣ እነሱም በተራቸው የሥራ ባልደርቦቻቸው የሆኑ መምህራንንም ያሰለጥናሉ ተብሎ ይጠበቃል።