<strong>በኮንሶ ዞን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ዙሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው </strong>

በኮንሶ ዞን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ዙሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው

የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኩሴ ጭሎ

የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ኤስ አይ ኤል ከተባለ ቋንቋ ላይ የሚሠራ ተቋም ጋር በመተባበር ለ1ኛ ክፍል በሚሰጠው የኮንሰኛ ቋንቋ ትምህርት ፊደላት ወይም ኦርቶግራፊ ዙሪያ ለሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የመምሪያውን ኃላፊ ጠቅሶ የኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

እንደ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኩሴ ጭሎ ገለጻ፣ “በአፍ መፍቻ ቋንቋው ትምህርት ዙሪያ ብዙ የተዛቡ አመለካከቶች ይስተዋላሉ። ሥልጠናውም ይህን የተዛባ ትርክት በተወሰነ መልኩ ይቀርፋልም” ብለዋል። ኃላፊው በመክፈቻ ንግግራቸው የኮንሰኛ ቋንቋ መምህራን እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

ስልጠናው ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰልጣኞች ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ፣ስለቋንቋው ትምህርት በማህበረሰቡ መካከል የሚስተዋለውን የተዛባ ትርክት በማስተካከል በኩል የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኤስ አይ ኤል የቋንቋ ባለሙያ አቶ እንግዳ ኩሲያ

ሥልጣውን በመስጠት ከዞን ትምህርት መምሪያ ጋር እየሠራ የሚገኘው ኤስ አይ ኤል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ98 አገራት ቋንቋዎችን ማበልጸግ ላይ የሚሠራ ክርስቲያናዊና ለትርፍ ያልተቋቋመ ምግባረ ሰናይ ተቋም ነው። በኮንሶ ዞን የመማሪያ መጻፍትን በኮንሰኛ ቋንቋ በማዘጋጀት ሂደት ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎችን በማበልጸግ በፊረንጆቹ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጋር መሥራት በኢትዮጵያ ብቻ ከ40 በላይ ቋንቋዎችን በማበልጸግ ሥራ ላይ የተሳተፈ ተቋም ነው።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ንቅናቄ ተሳታፊዎች

በሌላ ዜና በኮንሶ ዞን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ዙሪያ የተሠራው ሥራ በተፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳልነበር ተገለጸ። በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ዙሪያ የተሠራው ሥራ በቂ ውጤት አለማስገኘቱ በዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደይጋንቶ ኡርማሌ የተገለጸው፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ከማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመሆን በዛሬው ዕለት የአባላት ምዝገባና የአባልነት ዕድሳት ንቅናቄ ባደረጉበት ወቅት ነው።

የጸጥታ ችግር፣ የሰው ሀብት እጥረት፣ የኦዲት ሥራዎች አለመሠራት፣ ለአባላት መታወቂያ አለማዘጋጀት፣ በአባልነት ክፍያ ወቅት ደረሰኝ አለመስጠትና ሪፖርቶችን በጊዜ አለማቅረብ፣ በ2014 ዓ.ም ለተሠሩ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥራዎች ውጤታማ አለመሆን ተጠያቂ ተደርጓል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ንቅናቄ ተሳታፊዎች

በንቅናቄው ስብሰባ ወቅት የተለያዩ የወረዳና የዞን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች አመራር በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም ዕቅድ መሠረት ለውጥ እንዲመጣ መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች ጠቁመዋል። ከእነዚህም መካከል የጤና መድኅኑን አስፈላጊነት በመረዳት ባለድርሻ አካላት ለውጤታማነቱ መረባረብና በትኩረት መሥራት አለባቸው ተብሏል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *