
በኮንሶ ዞን በቀጠናው በተደጋጋሚ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከተፈናቀሉና በአካባቢው ባጋጠመ ድርቅ ምክንያት ለረሃብ ከተጋለጡ ወገኖች መካከል 84% ለሚሆኑ የዕርዳታ ድጋፍ መደረጉን፣ የዞኑን የአደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠቀቂያ ጽ/ቤት ኃላፊን ጠቅሶ፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
ለእነዚህ ወገኖች የተደረጉ የምግብ እህል፣ የገንዘብና የቁሳቀስ ድጋፎች የተገኙት ከፌዴራል መንግሥት፣ከክልል መንግሥት፣ ከዞኑ ኅብረተሰብ፣ ከአጎራባችን ዞኖችና ከተለያዩ አጋር የዕርዳታ ድርጅቶች መሆኑንም የዞኑ የአደጋ ሥጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገደኖ ካዋይታ መናገራቸው ተገልጿል።
በጸጥታ ችግሮቹ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አብዛኛዎቹ ወገኖች ወደቀዬያቸው መመለሳቸው በዘገባው የተገለጸ ቢሆንም አሁንም ያልተመለሱና በየጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ መኖራቸውም ታውቋል። በተለይ አሁንም በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ እና በተመሳሳይ ከመኖሪያ ቀዬያቸው ከተፈናቀሉ በኋላ በካራት ከተማና በተለያዩ የኮንሶ አካባቢዎች ዘመዶቻቸውን ተጠግተው ያሉ ወገኖች፣ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በኃላፊው ማብራሪያ ተገልጿል።
በአጠቃላይ በግጭቶቹ የተፈናቀሉ ወገኖች፣ በድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳታቸው ታውቋል። በበኮንሶና ዙሪያው ባሉ ቀጠናዎች በተደደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መፈናቀላቸውንና በተመሳሳይ በተደጋጋሚ በዞኑና አጎራባች አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ ከ190 ሺህ በላይ ዘጎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን አይዘነጋም። የዞኑ መንግሥት 84% ተፈናቃዮችና ለረሃብ አደጋ የተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ማግኘታቸው በደፈናው ከመገለጹ በስተቀር፣ ምን ያህል አባወራዎች ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውና ምን ያህል የድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ ስለማግኘታቸው በአሃዝ የተገለጸ ነገር የለም።