በኮንሶ ዞን ለአዲሱ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው

በኮንሶ ዞን ለአዲሱ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው

ለህዝበ ውሳኔው የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን የሚያሳይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፖስተር

የኮንሶ ዞንን ጨምሮ በ6 ዞኖችና በ5 ልዩ ወርዳዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለማካሄድ ላቀደው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን፣  የኮንሶ ዜና የመረጃ ምንጮች ገለጹ።

የኮንሶ ዞን፣ የወላይታ ዞን፣ የደቡብ ኦሞ ዞን፣ የጋሞ ዞን፣ የዴዴኦ ዞንና የጎፋ ዞን፣ እንዲሁም የቡርጂ ልዩ ወረዳ፣ የባስኬቶ ልዩ ወረዳ፣ የአሌ ልዩ ወረዳ፣ የአማሮ ልዩ ወረዳና የዲራሼ ልዩ ወረዳ ከቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወጥተው አዲስና “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል መጠሪያ ያለው ክልል ለማቋቋም ማመልከታቸውን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የህዝበ ውሳኔው የመራጮች ምዝገባ በትላንትናው ዕለት መጀመሩን፣ በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በኩልም ይፋ ተደርጓል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት በማህበራዊ ትሥሥር ገጹ በኩል ባሠራጨው መግለጫ፣ “በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ ዛሬ ታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም የመራጮች ምዝገባ ተጀምሯል” ሲል ትላንት አስታውቋል።

እንደ መረጃ ምንጮቻችን ከሆነ፣ በኮንሶ ዞን 150 ሺህ ያህል ህዝበ ውሳኔ ሰጪዎች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል። ምዝገባው በ131 የምርጫ ጣቢያዎች በመከናወን ላይ መሆኑም ተገልጿል። ከዚህ በፊት በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ፣ በኮንሶ ዞን 121 የምርጫ ጣቢያዎች በሂደቱ መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ጥሪ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚከናወነው ህዝበ ውሳኔ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጣቢያዎች በተጨማሪ 10 የምርጫ ጣቢያዎች በመከፈታቸው ቁጥራቸው 131 ሊደርስ ችሏል።

በኮንሶ ዞን በተለያዩ እርከን የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ኅብረተሰቡ ተመዝግቦ በህዝበ ውሳኔው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን፣ በርብርብ በመሥራት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ከላይ በስም የተገለጹ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች “በአንድ አዲስ ክልል ይደራጁ!” የሚለው ሐሳብ “በነጭ ርግብ” ተወክሎ ለምርጫ የሚቀርብ ሲሆን፣ ከላይ በስም የተገለጹ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች “በአንድ አዲስ ክልል አይደራጁ!” የሚለው ሐሳብ ደግሞ “በጎጆ ቤት” ተወክሎ ለምርጫ እንደሚቀርብ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ለውጥ የተደረገበት የህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክቶችን የሚያሳይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፖስተር

ከዚህ በፊት “አይደራጁ!” የሚለው ተቃርኗዊ ሐሳብ በነጭ ላም እንደሚወከል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል የተገለጸ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ፣ “የህዝበ ውሳኔ ምልክት ስለመቀየር” በሚል በማህበራዊ ትሥሥር ገጹ ባሰፈረው አጭር መግለጫ፣ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለቦርዱ የዚህ ሕዝበ ውሣኔ አማራጭ ምልክት ነጭ ላም መሆኑ ቀርቶ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ዐርማ የሆነው ጎጆ ቤት እንዲሆን ጥያቄ በማቅረቡ፤ ቦርዱም የምክር ቤቱን ጥያቄ ተቀብሎ ከላይ የተጠቀሱትን ስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀታቸውን አልደግፍም ለሚለው የሕዝበ ውሣኔ አማራጭ ሃሣብ ምልክት ጎጆ ቤት እንዲሆን መወሠኑን ያሳውቃል” ሲል የምልክት ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *