በኮንሶ ዞን ለአሽከርካሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

በኮንሶ ዞን ለአሽከርካሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

አቶ መሳይ አሰፋ – የኮንሶ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ

የኮንሶ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ፣ ለህዝብ ማመላለሻና ለታክሲ አሽከርካሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና መሰጠቱን የዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

የተሃድሶ ስልጠናው ሰኞ ህዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች የተሰጠ ሲሆን ትላንት ህዳር 13፣ 2015 ዓ.ም ደግሞ ለታክሲና ለባለ ሦስት እግር ባጃጅ አሸካርካሪዎች መሰጠቱ ተገልጿል። ሥልጠናው አደጋን መከላከልና ሥነ ባህሪ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል። በተጨማሪም በተሽከርካሪዎች ቴክኒክ ብቃት አፈታተሽ ዙሪያም ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶች መቅረባቸው ተገልጿል።

በኮንሶ ዞን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የትራፊክ አደጋዎች እየጨመሩና የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፉ መምጣታቸው ይታወቃል። የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት አለመሟላት፣ የፍጥነት ወሰንን አለማክበር፣ ከልክ በላይ ጭነት መጫን፣ እንዲሁም ጠጥቶ ወይም የተለያዩ አነቃቂና አደንዛዥ ዕጾችን ተጠቅሞ ማሽከርከር ለመኪና አደጋ አጋላጭ ከሆኑ ሁኔታዎች መካከል መሆናቸው በሥልጠናው ወቅት መገለጹ በዘገባው ተመላክቷል።

የአሽከርካሪዎች የተሃድሶ ስልጠና ላይ የተሳተፉ አሽከርካሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶች

በሥልጠናው ላይ የተገኙት የዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ አሰፋ ለአሽከርካሪዎች በሰጡት ማሳሰቢያ፣ “በሥነ ምግባር የታነጹና ብቁ አሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም ሁሌም ሲያስከረክሩ የፍጥነት ወሰን የሚያከብሩ፣ እንዲሁም የትራፊክ ህግና ደንብ የሚያከብሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎች መሆን ይኖርባችኋል” ብለዋል።

በሥልጠናው ወቅት የነዳጅ ድጎማና የታሪፍ ጉዳዮችም መነሳታቸው ተገልጿል። የታሪፍ ጉዳይ ሌላኛው የህዝብ ቅሬታ ሲቀርብበት የኖሬ ችግር መሆኑ ይታወቃል።

በስልጠናው ማብቂያ ላይ፣ በሥነ ምግባር የታነጹና ህግና ደንብን አክብረው ለሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች የማበረታቻና የዕውቅና የምሥክር ወረቀት መሰጠቱ፣ በኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ ዘገባ ተመልክቷል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *