
በሚጎራበቱባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች በኮንሶ ህዝብና በአሌ ህዝብ መካከል በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶችንና የጸጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠረውን የመጠራጠርና የመፈራራት መንፈስን ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ፣ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የሰላም ኮንፍረንስ መካሄዱን የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታዉቋል።
በተለይ ኮልሜ በሚባለው የኮንሶ አካባቢና ገዋዳ በሚባለው የአሌ ልዩ ወረዳ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸውና ይህንንም ተከትሎ ብዙም ውጤታማ ያልሆኑ የዕርቀ ሰላም ኮንፍረንሶችም መካሄቸውን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
በባልህና በደም በተሳሰሩ፣ ነገር ግን በቋንቋ በተለያዩ በኮንሶና በአሌ ህዝቦች መካከል በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶችም የብዙ ሰዎች ህይወትና ከፍተኛ ግምት ያለው የአርሶ አደሮች ንብረትም መውደሙ ይታወቃል። ግጭቶቹንም ተከትሎ በተፈጠረ መፈራራት፣ እርስ በርስ መገበያየት በመቀዛቀዙ የአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጫናም ፈጥሮ ነበር።
ባለፈው ቅዳሜ በተከናወነው የዕርቀ ሰላም ኮንፍረንስ ከኮንሶና ከአሌ በኩል የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሁለቱም የአካባቢ መንግሥታት አመራሮችም መገኘታቸው በኮሚኒኬሽን መሥሪያ ቤት ዘገባ ተመልክቷል።

በዕርቀ ሰላም ኮንፍረንሱ ላይ ለታደሙ ሰዎች፣ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ ለመመለስ በሁለቱም መዋቅር የጸጥታ አካላት በኩል የተሠሩ ሥራዎችም በሰላምና ጸጥታ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች በኩል መቅረቡ ተገልጿል።
በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ከዚህ በፊት የተደረጉት ተደጋጋሚ ዕርቆች ከንግግር ባለፈ በተግባር አለመገለጻቸውንና ይህም ለተደጋጋሚ የጸጥታ መደፈርስ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። ይሁንና ከዚህ በኋላ በኅብረተሰቡ መካከል ወንጀል የሚፈጽሙትን አካላት በማጋለጥና ለህግ አካላት አሳልፎ በመስጠት፣ ሰላምን በጋራ ለመጠበቅ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም፣ የሁለቱም መዋቅር መሪዎች፣ የቀበሌ መሪዎችና በኮንፍረንሱ ላይ ከሁለቱም ወገን የተገኙ ታዳሚዎች እጅ ለእጅ በመያያዝ “አንድ ነን!” በማለትና ይቅር በመባባል ስብሰባው መጠናቀቁን የኮንሶ ዞን ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት መረጃ ያመለክታል። ከሳምንት በፊት ተመሳሳይ የዕርቀ ሰላም ኮንፍረንስ በኮንሶ ዞንና በዲራሼ ልዩ ወረዳ ህዝቦች መካከል መደረጉ ይታወሳል።

በሌላ ዜና፣ የኮንሶ ዞን አመራር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውይይት ማካሄዱ ተገልጿል።
ውይይቱም ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ሰላምና ጸጥታን ማጠናከር፣ እንዲሁም ስለመጪው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” መመሥረቻ ህዝበ ውሳኔ አካሄድ መሆኑ፣ በኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ ዘገባ ተገልጿል።
“ነጭ ርግብ” የአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጫ ምልክት ሆኖ እንደተመረጠ በዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ የተገለጸ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ነጯን ርግብ በመምረጥ የአዲሱን ክልል ምሥረታ እንዲደግፍ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29፣ 2015 ዓ.ም በሚያካሂደው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምልክቶች ለመወሰን ህዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፣ “የ6ቱ ዞኖችና የ5ቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን እደግፋለሁ” የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉ ወገኖች በህዝበ ውሳኔው ወቅት፣ ነጭ ርግብ ለመጠቀም በአስተዳደር ምክር ቤቶቻቸው መመረጡን ምርጫ ቦርድ ከሳምንት በፊት ማስታወቁ ይታወቃል።

በሌላ በኩል፣ “የ6ቱ ዞኖችና 5ቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን አልደግፍም!” የሚል ሐሳብ የሚያራምዱና “ህዝበ ውሳኔውን በመቃወም እንከራከራለን” በማለት ለቦርዱ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ያቀረቡ 6 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቦርዱ አማራጭ ምልክት እንዲመርጡ ቢጠየቁም ፓርቲዎቹ አማራጭ ምልክት መምረጥ እንደማይፈልጉ መግለጻቸውን ምርጫ ቦርድ ጨምሮ አስታውቋል። በዚህም መሠረት፣ የ6ቱን ዞኖችና የ5ቱን ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን ለማይደግፉ ወገኖች በምርጫ ምልክትነት እንዲያገለግል፣ ከዚህ በፊት ለአገራዊ ምርጫ ከተዘጋጁ ምልክቶች መካከል “ነጭ ላም” በምልክትነት ጥቅም ላይ እንዲውል በምርጫ ቦርድ ተወስኗል።