
የቀድሞው የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን መፍረስን ተከትሎ በኮንሶና በዲራሼ ወንድማማች ህዝቦች መካከል በጽንፈኞች ተቀስቅሰው የነበሩ ግጭቶችን ተከትሎ በአጎራባች አካባቢዎች በህዝቦቹ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት፣ የሰላም ኮንፍረስ መካሄዱን የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
በግጭቶቹ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ማህበረሰቦች መካከል በዴራሼ ልዩ ወረዳ ሥር የሚተዳደረው የኩሱሜ ብሔረሰብ አንዱ ሲሆን፣ መንደር አንድ እና መንደር ሁለት በመባል የሚታወቁት የብሔረሰቡ የመኖሪያ አካባቢ ላይ ያሉ የማህበረሰቡ አካላት በህዝቡ መካከል በተፈጠረ የመጠራጠርና መጉዳዳት ስሜት ላለፉት 5 አመታት መቀራረብ አለመቻላቸውም ተገልጿል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ የተደረገው የዕርቅና ህዝባዊ ትሥሥር መርሃ ግብሩ፣ ኩሱሜ ላይ የተደረገ መሆኑን ተከተሎ ከአመታት በኋላ የሁለቱ መንደራት ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ መቀመጣቸው ታውቋል። ይህንንም እንደ ትልቅ ዕድልና ድል እንደሚያዩትም በዘገባው ተገልጿል።
የኮንሶ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገልገሎ ገልሾና የዲራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኪታንቦን ጨምሮ ሌሎችም የሁለቱ መዋቅሮች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣በዕርቅና ህዝባዊ ትሥሥር ኮንፍረሱ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።

የጸጥታ ችግሮችን ከምንጫቸው ለማድረቅ፣ ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር ውይይቶችን በማድረግ ህዝባዊ ትሥሥሮችን ማጠናከር እንደሚገባም በሰላም ኮንፍረንሱ ወቅት ተጠቁሟል። ኅብረሰተሱም ህገ ወጥ ተግባራትን በመፈጸም ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ግለሰቦችን አጋልጦ ለጸጥታና ለህግ አካላት አሳልፎ ሊሰጥ ይገባልም ተብሏል።
ከሁለቱ የኩሱሜ መንደራት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደየቀዬአቸው በመመለሱ ሥራ፣ የቤተ እምነት መሪዎችና ሽማግሌዎች አደራ መቀበላቸውም ታውቋል።በሰላም ኮንፍረሱ ላይ፣ “ሰላምን የሚጠላውና የሰውን ደም የሚጠጣው ሰይጣን ብቻ ነው!” እና “እኛ አንድ ህዝብ ነን!” የሚሉ አስተያየቶች በኮንፍረንሱ ወቅት ተደምጠዋል።
የሰላም ኮንፍረንሱ በኃይማኖትና በባህል አባቶች ቡራኬና ጸሎት መጀመሩን፣ በመጨረሻም በህዝቦቹ እጅ ለእጅ መያያዝ መጠናቀቁን በኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ ዘገባ ተመልክቷል።