በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ላለፉት 10 ቀናት ሲደረግ የነበረው ድርድር በስምምነት ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ላለፉት 10 ቀናት ሲደረግ የነበረው ድርድር በስምምነት ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ንግግር ዛሬ በስምምነት ተቋጭቷል።

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦልሴጎን ኦባሳንጆ የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት የሰላም ንግግርን ይዘት ይፋ አድርገዋል። በመግለጫቸውም አሁን በኢትዮጵያ የሰላም ንግግር ወደ ሰላም ትግበራ የሚሸጋገርበት ምእራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ኦልሴጎን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ በጦርነት ላይ የነበሩት የፌደራል መንስት እና ህወሓት በዘላቂነት ግጭት ለማቆም መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ለተቸገሩ ወገኖች ሁሉ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ማረጋጋጥና አገልግሎቶችን ማስጀመር ስምምነት ላይ ከተደረሱባቸው ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰዉን የሰላም ስምምነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የህወሓቱ ተወካይ አቶ ጌታቸዉ ረዳ በፊርማቸዉ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋንና አቶ ጌታቸዉ ረዳ ስምምነት ላይ የተደረሱባቸዉን ነጥቦች በጋራ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ልኡክ የመሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱን ከመፈረም ባሻገር ለተግባራዊነቱ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን በማድነቅም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የውጭ ሃይላት ሲያደርሱት የነበረውን ጫና በማንሳትም፣ ከዚህ በኋላ ግን ይህ እንደሚስተካከልና የሰላም ጥረቱ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ህጎችን መሠረት አድርጋ የውጭ ግንኙነቷን እንደምታሻሽልም ነው አምባሳደር ሬድዋን ያነሱት።

ሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአትን ለመትከል የጀመረቻቸው የተቋማት ግንባታ ተስፋ ሰጪነትን በመጥቀስም ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ ቁርሾዎችን ሊፈታ እንደሚችል አብራርተዋል። ስምምነቱ እንዲደረስ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ተሳትፎ ያደረጉ ተቋማትና ሀገራትንም አመስግነዋል።

የህወሃትን ቡድን ልኡክ የመሩት አቶ ጌታቸው ረዳም በበኩላቸው ስምምነቱን፣  “የአዲስ ነገ ጅማሬ ነው” ብለውታል። ከመንግስት ጋር የተደረሰው ስምምነት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሰላም ናፋቂ ኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት መሆኑንም አንስዋል።

ይሁን እንጂ ሁለቱም የስምምነቱ ፈራሚዎች ስምምነቱን አክብረው ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህወሃት ስምምነቱን የፈረመው ለትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣትና የመልሶ ማቋቋም ስራውም በፍጥነት እንዲካሄድ በማሰብ ነውም ብለዋል። የትግራይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፤ በመድሃኒት እጦት ለሚሰቃዩትም መድሃኒት እንዲደርሳቸው በአጠቃላይ ሰላም እንዲረጋገጥ ህወሃት ተኩስ ለማቆም መስማማቱንም አክለዋል።

ሆኖም ባለፉት 10 ቀናት ድርድሩም እየተካሄደ ጦርነቱ መቀጠሉን ጠቅሰው፥ በዚህም በሁለቱም ወገን ዜጎች እየረገፉ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ከረጅም ሂደት በኋላ የተደረሰው ስምምነት የሰላም አየርን እንዲያመጣ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ ሊያቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ህብረትን የአደሬዳሪነት ሚና በማድነቅም አጋር ሲሉ የገለጿቸው አለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ክትትላቸው እንዳይለይ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ገጥሞ የነበረው ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን የኢትዮጵያ ተደራዳሪ አምባሳር ሬድዋን ሁሴን ከስምምነቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡

ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር ሙከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱ አይዘነጋም። ለሶስት ዙር በድጋሚ የተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አስከትሏል።

ይህን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ህብረት ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ መዲና የተጀመረው ድርድር ዛሬ ተጠናቋል።

የድርድሩን መጠናቀቅ ተከትሎ የፌደራል መንግሥትን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት የደረሱበትን ስምምነት ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም የሚጠቅም ነውም ብለዋል። ህወሓትም ስምምነቱ ለትግራይ እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት ነው ብሏል። ሁለቱ አካላት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባደረጉት ድርድር ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል የህወሀት ትጥቅ መፍታት እና በትግራይ ክልል የሚደረጉ ቀጣይ ስራዎች ናቸው።ከስምምነቶቹ መካከልም በኢትዮጵያ አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ብቻ እንዲኖር፣ ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ፣ ጦርነቱን በዘላቂነት ማቆም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲደረግ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች ማድረስ ዋነኞቹ ናቸው።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *