
የአውስትራሊያ ተማሪዎች በኤሌክትሪክ መኪና ታሪክ አዲስ ከብረ ወሰን ማስመዝገባቸው ተነግሯል።
የአውስትራሊያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰሩት አዲሱ መኪና ያለ ማቋረጥ ለ12 ሰዓታት 1000 ኪሎ ሜትር መጓዝ መቻሉም ተነግሯል።
“ዘ ስዊፍት 7” የሚል መጠሪያ የተሰጠው መኪናው በኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራ መሆኑ ተነግሯል።
መኪናው በሰዓት 85 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ የሚችል ሲሆን፤ ይህም በአንድ ጊዜ ቻርጅ ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የቻለ ፈጣኑ የኤሌክትሪክ መኪና አስብሎታል።

በዚህም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰሩት መኪና፣ አዲስ ክብረ ወሰን የሆነ ርቀት ተጉዟል የተባለ ሲሆን፤ ፍጥነቱ ከተረጋገጠ በኋላ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ እንደሚሰፍርም ተነግሯል።
በኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው የስዊፍት ፕሮጄክት ቡድን መሪ፣ “በዓለም ምርጥ የተባለን ነገር መስራት መቻል የተለየ ስሜት አለው” ብሏል።
“መኪናውን መስራት በጀመርንበት ከ2 ዓመት በፊት ሁሉም ነገር በኮሮና ምክንያት የተዘጋጋበት እና አስቸጋሪ ወቅት ነበር” ያለው ተማሪው፤ “በርካታ ሰዓታትን በሥራ አሳልፈናል፤ ዋጋም አግኝተንበታል” ብሏል።

ከዚህ ቀደም የኔዘርላንድስ ኤንድሆቨን ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በፀሃይ ኃይል የሚሰራ መኪና መሥራታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የኢንጂነሪንግ ተማሪዎቹ የሰሩት ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም ያለው መኪናው ወደ ቤትነት ተቀይሮ እንደ መኖሪያም የሚያገለግል ሲሆን፣ በፀሃያማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በቀን እስከ 740 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል መባሉም አይዘነጋም።