በታጠቁ ኃይሎች በኩሱሜ ብሔረሰብ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰ ነው

በታጠቁ ኃይሎች በኩሱሜ ብሔረሰብ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰ ነው

“የዲራሼ ልዩ ወረዳ የሚሊሻ አልባሳት ልብሰዋል” በተባሉ ታጣቂዎች የወደመ የኩሱሜ ተወላጆች የሙዝ እርሻ

በዲራሼ ልዩ ወረዳ ሥር የሚተዳደረው የኩሱሜ ብሔረሰብ፣ የዲራሼ ልዩ ወረዳ ሚሊሻ አልባሳት በታጠቁና ነፍጥ ባነገቡ ታጣቂዎች ከፍተኛ እንግልትና የንብረት ውድመት እየደረሰበት መሆኑን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለኮንሶ ዜና ገለጹ።

የታጠቁ የአካባቢው ሚሊሻዎች አካባቢው ላይ መረጋጋት እንዳይፈጠር፣ በየቤቱ እየገቡና ዜጎችን እየደበደቡ መሆናቸውንና ማህበረሰቡም በታጣቂዎቹ ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ በመማረር ላይ መሆኑን ነዋሪው ተናግረዋል። ከእንግልቱ የተነሳ የኩሱሜ ወንዶች ወደ ጫካ መሰዳደቸውና በቤታቸው ማደር እስከማይችሉ ድረስ መድረሳቸውንና ነው የመረጃ ምንጩ የገለጹት።

ባለፈው ወር በእነዚሁ ታጣቂዎች አንድ ሰው ተገድሎ ተጥሎ የተገኘ ሲሆን፣ ካለፉት 2 ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ታጣቂዎቹ በህዝብ ላይ የሚያደርሱት እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ታውቋል።

“የዲራሼ ልዩ ወረዳ የሚሊሻ አልባሳት ልብሰዋል” በተባሉ ታጣቂዎች የወደመ የኩሱሜ ተወላጆች የደርሰ የሙዝ አዝመራ

ባለፈው ቅዳሜ የደቡብ ልዩ ኃይል በአካባቢው ላይ እያለ ህዝቡን ያንገላታሉ የተባሉት ታጣቂዎች፣ የዲራሼ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አብራቸው ሆኖ፣ የአቶ ዳዋታ ጋርቢቼና የአቶ መሰለ ኦርካይዶ እርሻዎች ላይ የደረሰን የሙዝ አዝመራ በመንጫ መጨፍጨፋቸው፣ እኚው የመረጃ ምንጭ ተናግረዋል።

የኩሱሜ ማህበረሰብን ግራ እያጋባ ያለው፣ እነዚህ ታጣቂ ሚሊሻዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት – ማለትም የደቡብ ክልል ልዩ ኃይልና የዲራሼ ፖሊስ አባላት ባሉበት ይህን ግፍ እየፈጸሙ መሆናቸውን ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ፣ “እያስጨፈጨፈን ያለው መንግሥት ነው” የሚል ግንዛቤ በመፈጠሩ፣ “አቤት!” የሚሉበት አካል መጥፋቱም እየተነገረ ነው። “የሚሰማን የበላይ መንግሥት አካል ካለ ይድረስልን!” ሲሉም አቤቱታቸውን ያሰማሉ።  

የኩሱሜ ብሔረሰብ ከ30 ሺህ የማይበልጥ የህዝብ ቁጥር ያለውና በዲራሼ ልዩ ወረዳ ሥር ከሚተዳደሩ አራት ብሔሮች አንዱ ሲሆን፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ ከዲራሼ ልዩ ወረዳ መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ጭፍጨፋን ጨምሮ ብዙ ግፎችን እያስተናገደ ይገኛል።

በ2011 ዓ.ም በብሔረሰቡ ላይ በአካባቢው መንግሥት በደረሰ ጭፍጨፋ፣ የብሔረሰቡ መኖሪያ መንደሮች ወደ አመድነት መለወጣቸውንና ከ8 የማያንሱ መሸሽ ያልቻሉ አቅመ ደካሞች ሳይቀሩ ከነመኖሪያ ቤቶቹ መቃጠላቸው በወቅቱ ከሚወጡ መረጃዎችና ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች ለመረዳት ተችሏል። በወቅቱም አንዳንድ የብሔረሰቡ ተወላጆች በአካባቢው መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው፣ ወደ እሥር ቤት በመወሰድ ላይ ሳሉ በመንገድ ላይ ስለመገደላቸው፣ በወቅቱ ከወጡ መረጃዎች መታወቁ አይዘነጋም።  

የዲራሼ ልዩ ወረዳ የሚሊሻ አልባሳትን የለበሱት ታጣቂዎች በስብሰባ ላይ፣ “አካባቢው ላይ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ በመውሰድ አካባቢውን አደብ ማስገዛት አለባችሁ” የሚል ትዕዛዝ ከአካባቢው መንግሥት መቀበላቸውን ይናገራሉ ሲሉም፣ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈገው የአካባቢው ነዋሪ ጨምረው ተናግረዋል።  

የዲራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ የመሸጉ ጽንፈኛ ኃይሎች የዲራሼ ልዩ ወረዳ አመራርን ጨምሮ ብዙ የደቡብ ክልል የጸጥታ ኃይሎችን መጨፍጨፋቸውን ተከትሎ፣ ከሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢው በኮማንድ ፖስት የሚተዳደር መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና ከዚህ በፊት በኩሱሜ ህዝብ ላይ በልዩ ወረዳው አመራር ሲደርስ የነበረው ግፍ አሁንም በኮማንድ ፖስቱ አስተዳደር ጊዜም መቀጠሉ፣ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *