<strong>በምስራቅ ወለጋ ዞን በተፈጸም ጥቃት በርካቶች በአስቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ነዋሪዎችገለጹ </strong>

በምስራቅ ወለጋ ዞን በተፈጸም ጥቃት በርካቶች በአስቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ነዋሪዎችገለጹ

በኪረሙ የሚገኘው አንገር ጉትን ከተማ በካርታ ላይ

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት በተለይ በኪረሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ብሄራቸው እየተለየ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ተጨማሪ እልቂትን ሽሽት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅተዋል።

የሰሞኑ ግጭት መንስኤ በኪረሙ በእሥር ላይ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ግድያ መሆኑን፣ ከአንገር ጉትን ሸሽተው ስቡንሱሬ ቀበሌ የሚገኙ ስማቸው እንዳይጠቅሰ የፈለጉ ነዋሪ አል አይን አማርኛ ለተሰኘ ሚድያ ተናግረዋል።

“‘የመንግስት አካላት ሸኔ ይገድላችኋል ኑ ወደ ካምፕ ግቡ’ በማለት የአማራ ገበሬዎችን ስብስበው ኪረሙ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ አስረዋቸው ነበር፤ የአገር ሽማግሌዎች የታሰሩት እንዲፈቱ ጥረት ቢያደርጉም ኦሮሞዎች እየተለቀቁ አማራዎች ግን እንዳይወጡ ተደርጓል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው የሰሞኑ ችግር መንስኤም ከዚሁ ጋር ይያያዛል ብለዋል።

 እኝህ ነዋሪ፣ “በእሥር ላይ የነበሩትን የአማራ ተወላጆች ጊዳ ወደተባለ ቦታ አግቶ ለመውሰድ የተደረገው ጥረት የአማራ ተወላጆች ከኦሮሚያ ልዩ ሃይል ጋር እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

ቅዳሜ ህዳር 24፣ 2015 ማለዳ ላይ የተጀመረው ጥቃትም ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን ህይወት መቅጠፉንና በርካቶችም መቁሰላቸውን ተናግረዋል ነዋሪው።

“ከነቀምቴ በርካታ የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይል ወደ ጉትን እየመጣ ነው” መባሉም በከተማዋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የመኖሪያ ቤታቸውን ለቀው በጫካ ውስጥ እንዲደበቁ ምክንያት ሆኗል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኪረሙን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ “አማራው ለቆ ወደ ሃሮ፤ ኦሮሞው ደግሞ ወደ ጊዳ አያና ሸሽቷል” የሚሉት የአይን እማኙ፤ “ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ህይወታችንን ለማትረፍ በመሰደዳችን ጉትን ሰው አልባ ሆናለች” ብለዋል።

ነዋሪው አንገር ጉትን ላይ ብቻ 56 ሰዎች መቀበራቸውን እና በየጫካው የሟቾች ፍለጋው ስለቀጠለም ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።

ሌላኛው የአንገር ጉትን ከተማ ነዋሪ፣ በነበረው ችግር የኦሮሞ ተወላጆችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ለአል አይን ገልጸዋል።

“እስካሁን ሁለት ኦሮሞዎች መገደላቸውን አውቃለሁ” የሚሉት የአይን እማኙ፣ “ግድያን ሽሽት የአንገር ጉትን ከተማ የኦሮሞ ተወላጆችም ወደ ነቀምትና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው ከተማዋ ባዶ ሆናለች” ብለዋል።

“ፋኖ ተደራጅቶ ሊወጋችሁ እየመጣ ነው” የሚል መረጃ መሰራጨቱም ህዝቡን ሽብር ውስጥ መክተቱን ገልጸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በጊዳ አያና ተፈናቅለው እንደሚገኙና ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል የአይን እማኙ።

ለሰሞኑ ጥቃት የአማራ ተወላጆች የኦሮሚያ ልዩ ሃይልን፣ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ የአማራ ታጣቂዎችን ተጠያቂ እያደረጉ ይገኛሉ።

“የአማራና የኦሮሞ ህዝብን እያራራቅ ያለው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ነው” የሚሉት አል አይን በስልክ ያነጋገራቸው የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪ፣ “የሰሞኑን ጥቃት ሸኔ ላይ ለማላከክ ጥረት ይደረጋል እንጂ ዋነኛ ተጠያቂው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ነው” ብለዋል።

“ሸኔ ከገበሬው አቅም አይበልጥም፤ ልዩ ሃይል ከሌለ ሸኔ የለም፤ ተዋልዶ ተዛምዶ የኖረ ህዝብን እያባላ ያለው ልዩ ሃይሉ ነው” ብለዋል።

 የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት የአንገር ጉትን ነዋሪ ስር ያሲን በበኩላቸው፣ “ሸኔ ወደ ጉቴ አንድም ቀን መጥቶ አያውቅም። ውጊያው በኦሮሚያ ልዩ ሃይልና በአማራ ታጣቂዎች መካከል ነው” ይላሉ። ለሰሞኑ ጥቃት ግን የታጠቁና በብር የተገዙ “ፋኖዎች” ዋነኛ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።

አንገር ጉትን እና ጊዳ መካከል ያሉ የአማራ ታጣቂዎች ችግር መፍጠር ከጀመሩ ወራት መቆጠሩን በማንሳትም፣ ህዝቡን እያማረሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። “ይህም የዜጎችን እንቅስቃሴ እና ደህንነት አደጋ ላይ መጣል በመጀመሩ፣ ከኦሮሚያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል” ይላሉ።

የአማራ ተወላጁ ነዋሪ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። “ሰውን የሚገድልም ሆነ የሚዘርፍ የአማራ ሃይል በአካባቢው የለም፤ ሆን ተብሎ በአማራ ላይ የተከፈተ ዘመቻ ነው” ብለዋል።

የሰሞኑ ግጭትም አማራውን ትጥቅ ለማስፈታት የተያዘው እንቅስቃሴ አካል እንደሚሆን በማመን፣ ጉዳዩ እልቂቱን እንዳያባብሰው ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ነዋሪው ለአል ዐይን አማርኛ እንተናገሩት አሁን ላይ መረጋጋት እየታየ ቢሆንም የቀጣይ ደህንነታቸው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስትም አፋጣኝ መፍትሄን እንዲያበጅም ጠይቀዋል።

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግድያውን በተመለከተ እስካሁን ያወጡት መግለጫ አለመኖሩ እያነገረ ይገኛል።

Comments

No comments yet. Why don’t you start the discussion?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *