
ራስን መሆን!
ዛሬ ራስን ስለመሆን አጭር ጽሑፍ አቀርብላችኋለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ለሚከተሉት ጥያቄዎች ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠትና እግረ መንገድ እናንተን ስለራሳችሁ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ እንዲሁም ራሳችሁን ፈልጋችሁ በማግኘት በቀሪው ዘመናችሁ እራችሁን በመሆን እንድታሳልፉ ለመጋበዝ ነው። ጥያቄዎቹም፣ ራስን መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ራስን መሆንስ ምን ፋይዳ አለው? ራሳችንን እንዳንሆን እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮችስ ምንድን ናቸው? እንቅፋቶቹንስ እንዴት ማስወገድ እንችላለን? ራሳችንን ሆነን ለመገኘትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል የሚሉ ናቸው።
ራስን የመሆን ምንነት
ራስን መሆን የሚለውን ሐረግ ከመመልከታችን በፊት ሐረጉ የተዋቀረበትን ሁለት ቃላት፣ ማለትም “ራስ” እና “መሆን” የሚሉትን ቃላት ትክክለኛ ብያኔ ለመመከት እንሞክር። ነገርን ከሥር መሠረቱ ለመመልከት መሞከር አጠቃላይ አንድምታውን ለመገንዘብ ይረዳል። ስለዚህ በመጀመሪያ ራስ በሚለው እንጀምር። “ራስ” ስንል ምን ማለታችን ነው። ራስ ስንል አንድም አንጎላችን የሚገኝበትንና ጭንቅላት ብለን የምንጠራውን የሰውነታችን ክፍል የሚወክል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሁለመናችንን፣ እኛነታችንን የሚወክል ቃል ነው። ይህም ሲባል ሙሉ ስብዕናችንን ማለቴ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በተምሳሌትነት የዋና ነገር ትዕምርትም ነው። ሰው፣ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ስለስብዕናው ግንዛቤ ያለው ብቸኛው ፍጡር ነው። ስለዚህ ራሱን የበለጠ ለማወቅም ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቃል። ጥያቄዎቹንም ለመመለስ በተሰጠው አዕምሮ ያስባል፤ ያሰላስላል፤ ይመራመራል፤ አሳብን ያብሰለስላል። “ራስ” የሚለው ቃል እኛን በመሠረታዊነት ከሌሎች ሰዎች የሚለየው ዋና ግለ ግንዛቤያችንና ማንነታችን ነው። እንደ እኛው ከሆኑ ሌሎች [ሰዎች] ለብቻው የሆነ ቁሳዊና ሰብዕናዊ ምንነት መሆናችንን የመገንዘብ እውነት ነው። እኛን ከሌሎች ሰዎች የሚለየን የህልውና ዕውቀት ነው።
ስለራስ ይህን ያህል በአጭሩ ካልን፣ እስቲ አሁን ደግሞ ስለመሆን አጭር ብያኔያዊ ገለጻ ለማየት እንሞክር። “መሆን” ምድን ነው? በቃል ደረጃ ስንመለከት “መሆን” ግሥ ነው፤ ድርጊትን አመላካች ነው፤ ከድርጊትም ደግሞ የተጠናቀቀን ወይም የተቋጨን ድርጊት ሳይሆን፣ በቀጣይነት በመከናወን ላይ ያለን ድርጊት ያመለክታል። ስለዚህ ህልውናን አመላካች ነው።
ስለዚህ አሁን ደግሞ ሁለቱን ቃላቶች በአንድነት እንመልከታቸው። “ራስን መሆን” ማለት ለብቻው ልዩ ሆነን የተፈጠርን ፍጥረት መሆናችንን መገንዘብና በህልውናችን ቆይታ ሁሉ ያንኑ የተደረግነውን ማንነት እየገለጥን መኖር መቀጠል ማለት ነው። ራስን መሆን ማለት በመጀመሪያ ደረጃ ስብዕናችንን መረዳት ቀጥሎም በዚያ ስብዕናችን መገለጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠርን ይናገራል (ዘፍ. 1፡26-28፣ 2፡7)። ራስን መሆን፣ “በተሰጠን ስብዕናችን ውስጥ ያ የእግዚአብሔር መልክ ምን ይመስላል? እንዴትስ ይገለጣል?” የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እነዚያኑ ጥያቄዎች በዕለተ ዕለት የህይወት ጉዞ መመለስ ማለት ነው።
አንዳንዶቻችን ስብዕናችን ወንድ መሆንን ሲያካትት ለሌሎች ደግሞ ስብዕናቸው ሴት መሆንን ያካተተ ነው። ስለዚህ ወንድ ለሆንን፣ ራስን መሆን ማለት “እግዚአብሔርን በተሰጠን የወንድነት ስብዕና ውስጥ እንዴት መግለጽ ይቻላል?” የሚልን ጥያቄ ራሳችንን በመጠየቅ ምላሹን በመሻት ውስጥ የመኖር ሁኔታ ሊሆን ይችላል። በምሳሌ ለማሳየት እግዚአብሔር ጠባቂና [ከጥቃት] ተከላካይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል(ኢሳ. 27፡3፣ 2ኛ ሳሙ. 22፡3)። የእግዚአብሔርን ጠባቂነትና ደካሞችን ከጥቃት ተከላካይነት እንዴት በወንድነት ስብዕናዬ ውስጥ መግለጥ ይቻላል? በማለት ራስን በመጠየቅ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎችና ፍጥረታት ከአደጋ በመጠበቅና ከጥቃት በመከላከል የእግዚአብሔርን መልክ በዕለተ ተለት ኑሮ መግለጥ ነው። ለስብዕናችን ቅርበት ያላቸውን የእግዚአብሔርን ባህሪያት በየዕለት ኑሯችን በመለማመድና እግዚአብሔርን በመምሰል ራሳችንን መሆን እንችላለን።
ሴት ለሆኑት ደግሞ እንደዚሁ ራስን መሆን ማለት፣ “እግዚአብሔርን በተሰጣቸው የሴትነት ስብዕና ውስጥ እንዴት መግለጥ ይቻላል?” የሚልን ጥያቄ ራሳቸውን በመጠየቅ ከተፈጥሯቸው ጋር የሚስማሙትን የእግዚአብሔርን ባህሪያት በዕለተ ዕለት ኑሯቸው በማጉላት መኖር ነው። ለወንድነት ስብዕና እንዳደረግነው ሁሉ አሁንም በምሳሌ ለማሳየት ያህል፣ እግዚአብሔር ርሁሩህና መሐሪ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (መዝ. 145፡8)። ስለዚህ ከሴትነት ስብዕና ጋር የተቆራኙትን ርህራሄና መሃሪነትን በየዕለት ኑሯችን በመተግበርና እግዚአብሔርን በመምሰል ራሳችንን መሆን እንችላለን። ራስን ስለመሆን የተወሰነ ግንዛቤ ከያዝን፣ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ራስን የመሆንን ፋይዳዎች እንመልከት።
ራስን የመሆን ፋይዳዎች
ራስን መሆን ብዙ ፋይዳዎች እንዳሉት እሙን ነው። ከብዙዎቹም መካከል የተገነዘብኳቸውን አራቱን ፋይዳዎች ላቅርብ። የመጀመሪያው የዓላማ ከንቱነትን/ብክነትን ይከላከላል። ራሳችንን መሆን ስንችል የተፈጠርንበትን ዓላማ መከወን እንችላለን። ሁላንችም እንደምንገነዘበው፣ ምንም እንኳን እንደ እኛው ሰው ሆነው የተፈጠሩ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢኖሩም እያንዳንዳችን አንዲያና ብቸኛ መሆናችን እሙን ነው። ለእያንዳንዳችን የብቻ የሆኑ አካላዊና ስብዕናዊ ባህሪያት አሉን። ለምሳሌ የጣታችን አሻራ፣ የአይን ብሌናችን አሻራ፣ የድምጻችን አሻራና የመሳሰሉት ይመሳሰሉ ይሆናል እንጂ የእያንዳንዱ ሰው ለየብቻ የሆኑ ባህሪያት ናቸው። ይህ የተፈጠርንበት ዓላማ ወይም በዚህ ምድር ላይ ለመከወን የተፈጠርባቸው ዝርዝር ምክንያቶች እንደዚሁ ለየብቻ መሆናቸውን አመላካች ነው። ምንም እንኳን በጥቅሉ እግዚአብሔርን ለመግለጥ የተፈጠርን ቢሆንም፣ በዝርዝር ደረጃ እያንዳዱ ሰው የእግዚአብሔርን ህልውና ለማሳየት የተፈጠረበት የራሱ የሆነ አካሄድ አለው። ይህ ለሰው ሁሉ በየግሉ የተሰጠው የህይወቱ ዓላማ ጋር የተቆራኘ ነው። እያንዳንዱ ሰው ይህን የግል ወይም የብቻ የህልውና ዓላማውን ተረድቶ እራሱን በመሆን ህይወቱን መኖር ከቻለ፣ ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዓላማ አይባክንም ወይም በሌላ አገላለጽ ከንቱ አይሆንም።
ራስን የመሆን ሁለተኛው ፋይዳ የጊዜንና የጉልበትን ብክነት ይከላከላል። ሁሉም ሰው የህይወት ዓላማውን ከጨበጠና ራሱን ለመሆን ከወሰነ፣ ያለ ዓላማው ሌላን ሰው ለመሆን በሚያደርገው ጥረት የሚያጠፋውን ጊዜና ጉልበቱን በሚገባ መቆጠብ ይችላል። ብዙዎች ራሳቸውን መሆን የማይችሉት ራሳቸውን ስላልተገነዘቡና የመኖራቸውን ዓላማ ስላልጨበጡ ነው። ይህ ከኪሳራዎች ሁሉ ከባዱ ኪሳራ ይመስለኛል። ሁሉም ሰው በምድር የምንኖረው ዘመን ውስንና የተገደበ ነው። ስለዚህ ቢቻል አስፈላጊ የህይወት ጉዳዮች ላይ መዋል አለበት። ራስን መሆን አለመቻልና በግራ መጋባት ውስጥ መኖር፣ አለዚያም ደግሞ በሌሎች ሰዎች ውስጥ የራስን ማንነት መፈለግ ለከፍተኛ የጊዜና የጉልበት ብክነትና ኪሳራ ይዳርጋል። ራሳችንን መሆን እስካልቻልን ድረስ በርግጥ ለተፈጠርለት ዓላማ መኖር አይቻለንም። ይህም ማለት በምድር የተሰጠንን ጊዜ በማባከን ለመጨረስ ልንገደድ እንችላለን። ምንም እንኳን ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ በወል ከሌሎች ጋር የሚያደርጋቸው ብዙ የህይወት ተግባራት ቢኖሩም፣ የተፈጠርንበት ዓላማ የወል ሊሆን አይችልም።
ሰው የመሆናችን ዓላማ በጥቅሉ “እግዚአብሔርን/ክርስቶስን መምሰል” ተብሎ የተገለጸ ቢሆንም ለእያንዳንችን፣ ይህ የመምሰል ተግባር እንደየጾታችንና ዕድሜያችን እንዲሁም የኑሮ ወይም የትምህርት ሁኔታችን ወይም እንደ ዕውቀታችን መጠን አውዳዊ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። እግዚአብሔር የምንመስለው በተረዳነው መረዳትና በተገለጠልን መገለጥ ልክ ብቻ ነው። ብዙ ከተሰጠው ሰው ብዙ እደሚፈለግ፣ እንደዚሁም ደግሞ ሰው ሁሉ በተጠራበት መጠራት ልክ መመላለስ እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ሉቃ. 12፡48፣ 1ቆሮ. 7፡20)። ይህ የእያንዳንዳችን የህይወት ዓላማ ዝርዝር የተለያየ መሆኑን አመላካች ነው። ዓላማውን አውቆ እንደሌሎች ለመሆን በመጣር ጊዜ ሳያባክኑ ለዚያ ለተሰጠን ዓላማ መኖር ትልቅ መታደል ነው። ዕድሜያችንንና ጉልበታችንን በከንቱ ከመፍጀት ይታደገናል።
ራስን መሆን በሦስተኛ ደረጃ ግራ መጋባትና ግጭቶችን ይቀንሳል። ራሳችንን መሆን ሲያቅተን ግራ ቀኝ እያየን እንደሌሎች ሰዎች ለመሆን ይዳርገናል። በሂደቱም ራሳችንም ግራ እየተጋባን ሌሎችንም ግራ ማጋባታችን አይቀርም። እሱ ብቻም ሳሆን ያለሥፍራችን የመገኘት ዕድላችንም ሰፊ እንደመሆኑ ለሥፍራው ከተገቡ ሰዎች ጋር ግጭቶች ውስጥ ከመግባት አንተርፍም። ራሳችንን መሆን ከቻልን ግን የራሳችን የህይወት መሥመር ላይ ስለምናተኩር ግራ መጋባትም፤ ግራ ማጋባትም ሆነ ከሌሎች ጋር ከሚገባው በላይ መገጫጨት ይቀንስልናል። ይህን ስንል ግጭት በግንኙነቶች ውስጥ አይቀረ ስለሆነ ነው። ሆኖም ግን ሁሉም ሰው በራሱ መንገድ ላይ ካተኮረ መገጫጨቱና ተያይዞ መውደቅ፣ ከዚያም የተነሳ ከጉዞ መገታት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ራሳችንን መሆን ስንጀምር መጽሐፍ እንደምናገር በጸጥታ መኖርና በራሳችን ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር እንጀምራለን (1ተሰ. 4፡11)። ራስን መሆን ማለት ይሄው ነው። የወል ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በራስ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር።
በአራተኛ ደረጃ ራስን መሆን፣ እርካታ የተሞላ ህይወት እንድኖረን ይረዳናል። ይህ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው። በምድር ህይወታችን እርካታ እንዲኖረን ካስፈለገ፣ ይህንን ያንንም ከማድረግ ይልቅ በትክክል ማድረግ የሚገባንን ብቻ መርጠን ማድረግ ስንጀምር ነው። ይህ ደግሞ ማድረግ በሚገባንና ማድረግ በምንችለው መካከል መለየትን ይጠይቃል። ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ማለት አይደለም። ማድረግ እንችላለን ማለት፣ እሱኑ ለማድረግ ተፈጠርን ወይም ይጠቅመናል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም የተፈቀደ ሁሉ እንደማይጠቅም ይናገራል (1ቆሮ. 6፡12)። የሚገባንን ብቻ ማድረግ ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለህይወታችን ትርጉም ያለውን ሥራ መሥራት የእርካታ ምንጭ ነው። እርካታ ብዙ በመሥራት ውስጥ ሳይሆን የሚገባንን ተግባር በመፈጸም ውስጥ ነው። እራሳችንን አውቀን በስብዕናችን መሠረት ራሳንን መሆን ስንጀምር እግዚአብሔር በሰጠን ህይወት ያለን እርካታም እየጨመረ ይሄዳል። ራስንን መሆን ብዙ የህይወት ኮቴቶችን ያራግፍልናል። በዚህም በአንጻራዊነት ቀለል ያለና ትርጉም ያለው ህይወት እንድንኖር ይረዳናል።
ራሳችንን እንዳንሆን የሚያግዱን እንቅፋቶች
ራስን መሆን ይህን ያህል ጠቃሚ ከሆነ ራሳችንን እንዳንሆንን የሚያደርገን ምንድን ነው? ራስን መሆን የሚጀምረው ከላይ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ራስን በማወቅ ይጀምራል። ከሌሎች ስዎች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ማንነት እንዳለን በመረዳት ይጀመራል። ለተወሰነ ዓላማና ለተወሰነ የጊዜ መጠን ወደዚህ ምድር መምጣታችንን ማወቅ ይጠይቃል። የህይወትን ትርጉም መረዳት ይጠይቃል። ስለዚህ ራስን በሚገባ አለማወቅ ራሳችንን እንዳንሆን እንቅፋት ከሚሆኑብን ምክኒያቶች አንዱ ነው ማለት እንችላለን።
ሌላኛው፣ “ለምንድን ነው የሚኖረው?” የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ያለመመለስ ችግር ነው። ወይም የመኖርን ዓላማ/ምክንያት አለመለየት ነው። እነዚህ ሁለቱ ራሳችንን እንዳንሆን የሚያደርጉን ዋናዎቹ እንቅፋቶች ናቸው። ለምን እንደምንኖር የማንገነዘብ ከሆነ ሌሎች ሰዎች የሚሆኑትን ሁሉ በመሞከር ህይወት እንጠመዳለን። ሌላን ሰው ለመሆን በምናደርገው ጥረትም ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ውድቀቶች ሊገጥሙን ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ያው ያልሆነውን መሆን አስቸጋሪ በመሆኑም ነው። ቢሳካልን እንኳን እርካታ አናገኝበትም። ውስጣችን እኛነታችንን ፍለጋ አያቆምም። ስለዚህ ህይወት በብዙ ሙከራዎችና ውድቆት የተሞላችና እርካታ አልባ ልትሆንብን ትችላለች።
ራሳችንን ስናውቅ ደካማ ጎናችንንም ሆነ ጠንካራ ጎናችንን እናውቃለን። በዚህም መሠረት በጠንካራ ጎናችን ለህይወታችን የተሰጠንን ልዩ ዓላማ ለማከናወን ጥረት እናደርጋለን። ደካማ ጎናችንን ደግሞ የሚሸፍንልን ሰው ወደ ህይወታችን እንፈቅዳለን። በዚህም በጋርዮሽ የሰው ልጆች ህይወት ውስጥ የራሳችንን አስተዋጽዖ በማበርከትና እገዛ በመቀበል በምድር ህይወታችን ውጤታማ እንሆናለን። በህይወት ከሌሎች ሰዎች ጋር ውድድር ውስጥ ከመግባት አባዜ ወጥተን ተመጋጋቢ ሚና እንዳለን ወደ መረዳት እንመጣለን። የምንረዳው እንዳለ ሁሉ የሚረዳንም እንደዚሁ እንዳለ ወደ መረዳት እንመጣለን። የህይወት ቁልፉ እርስ በርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ውስጥ ያለ ኅብረትና አብሮነት መሆኑንም እንገነዘባለን።
ራስን ለመሆን ምን እናድርግ?
በመደምደሚያዬ ላይ ራሳችንን መሆን እንዴት እንደሚቻለን አንዳንድ አሳቦችን በማንሳት ልቋጭ። ራስን መሆን ምን እንደሆነ ከተረዳን፣ ፋይዳዎቹንም ሆነ እንቅፋቶቹንም ካስተዋልን የቀረን “እንዴት ራሳችንን እንሁን?” የሚለው ብቻ ይሆናል። እኛ ሠሪ አለን። ሰው ለሚሠራቸው ነገሮች ሁሉ የአጠቃቀምና የአያያዝ መመሪያ አብሮ ያቀርባል። እግዚአብሔር የህወታችን ሠሪ እንደመሆኑ ህይወታችንን እንዴት ማስኬድና መያዝ እንዳለብ በመጽሐፉ በኩል መመሪያ ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።” ብሉ ይናገራል (መዝ. 100፡3)።
ስለዚህ ራሳችንን ለመሆን የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት ሠሪያችንን ማወቅ፣ የተፈጠርንበትን ዓላማ መረዳት፣ የተፈጠርንበትን ዓላማ ለመከወን ልዩ ብቃትና ባህሪያት እንደተቀበልን ማመንና በመጨረሻም በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ በመታመን እንድንሆን የተፈጠርነውን ማንነት ለመሆን የእምነት እርምጃ መውሰድ ነው። ራስን ለመሆን የእምነት እርምጃ መወሰድ ነው። ቀጥሎም ማድረግ ያለብን ሌሎችን ለመሆን በመሞከር ዕድሜና ዘመናችንን ማባከን ሳይሆን፣ በዘመናችን የተሰጠንን ልዩ የእግዚአብሔር አሳብ አገልግለን ለማለፍ መወሰን ነው። ቀሪ ዘመናችንን ራሳችንን በመሆን እንድንኖር ላበረታታችሁ ይህን አጭር ጽሑፍ እነሆ ብያለሁ። ራሳችንን ሆነን እንድንኖር እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን። አሜን!