
[ጽሑፉ ዘለግ ያለ ነውና ጊዜ ወስደው በኃላፊነት ያንብቡት፣ አለበለዚያ ግን ባይጀምሩ ይመረጣል!]
1) ለመሆኑ የኮንሶ ልማት ማህበር የማን ነው?
“ምን ዓይነት ጥያቄ ነው? ያው የኮንሶ ነዋ!” የሚል አይጠፋም። እውነት ነው። በርግጥ ስሙም “የኮንሶ ልማት ማህበር” የሚል ነው። ነገር ግን ልማት ማህበሩ የኮንሶ ቢሆንም፣ ማህበር እንደመሆኑ መጠን በመጀመሪያ ደረጃ የአባላቱ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ የተቋቋመለት የኮንሶ ህዝብም፣ እንደገና ሲቀጥልም የኮንሶን ህዝብ ልማትና ብልጽግና ማየት የሚፈልጉና ማህበሩን የሚደግፉ የኮንሶ ህዝብ ወዳጆች፣ ተቋማትና ድርጅቶች ሁሉ ነው።
ስንቶቻችሁ የልማት ማህበር ትዝታ አላችሁ? ድሮ ድሮ ከኮንሶ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚወጣ ተማሪ ሁሉ ወደ ዩኒቨርስቲ ከማቅናቱ በፊት የልማት ማህበሩ አባል በመሆን፣ አረንጓዴ ቀለም ያለው የልማት ማህበሩ መታወቂያ ይሰጠው ነበር። ይህም የተማሩ የኮንሶ ልጆች ገና ወደ ሥራ ዓለም እንኳን ሳይገቡ፣ ስለህዝባቸው ማሰብ እንዲጀምሩና ሥራ ሲኖራቸው በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን ማህበራቸውን በመደገፍ በህዝባቸው ልማት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ የማሳረፍ ዕድል እንዲኖራቸው ዕድል ለመስጠት ታስቦ እንደሆነ ይታመናል።
2) የኮንሶ ልማት ማህበር ሥራ የሚሠራበትን ጥሪት ከየት ያገኛል?
የኮንሶ ልማት ማህበር ከተቋቋመበት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 30 አመታት በነበረው የሥራ ጉዞው፣ የኮንሶን ህዝብ ለመደገፍ በየዘመናቱ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል፣ እያደረገም ይገኛል። ታዲያ እንደ ልማት ማህበርነቱ፣ “ከየት በሚያመጣው ሀብት ወይም ገንዘብ ነው የልማት ሥራዎችን የሚሠራው?” አትሉም?! ይህ ተገቢ ጥያቄ ነው። የልማት ማህበር ነውና ብዙ የልማት ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል። ለዚህም ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሪት ያስፈልገዋል።
የኮንሶ ልማት ማህበር ሥራውን ለመከወን ከ3 ምንጮች ገቢን ያገኛል። እነዚህም 1ኛ) የማህበሩ አባላት የሚያዋጡት የገንዘብ መዋጮ፣ 2ኛ) ከአሸዋ ሽያጭና ሌሎች የማህበሩ ንብረቶች ኪራይ የሚገኝ ገቢና 3ኛ) ከለጋሾች የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ናቸው። ልማት ማህበሩ ሲቋቋም ስለማህበሩ ብዙም ግንዛቤ በማህበረሰባችን ውስጥ ስላልነበረና በጊዜው ብዙም የተማረ የሰው ኃይልም ስላልነበረ ከአባላት መዋጮ የሚገኘው ገቢ ለብዙ አመታት አነስተኛና ብዙም ሥራ መሥራት የሚያስችል አልነበረም። ከዚህም የተነሳ ማህበሩ በተቋቋመበት ዘመን የነበሩ ቀደምት አባቶቻችን (የማህበሩ መሥራቾችና በዘመኑ ህዝባችንን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎቻችን) ይህንን ችግር በመገንዘብ፣ “ማህበሩ አንዳች ፋይዳ ያለው የልማት ሥራ ለኮንሶ ህዝብ መሥራት ካለበት፣ ሌላ የገቢ ምንጭ ያስፈልገዋል” በማለት ታሪካዊ ሊባል የሚችልና ለማህበሩ የገቢ ምንጭ ምሰሶ የሆነ ውሳኔ ወስነው ነበር። ይኸውም፣ በኮንሶ ውስጥ ከሚገኙ ወንዞች ከኻይሌ ወንዝ ለግንባታ ግብዓትነት የሚጫነው አሸዋ፣ ለልማት ማህበሩ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ተወስኖ ነበር። በዚሁ አግባብ፣ አልፎ አልፎ እንደታሰበው ባይሆንም ላለፉት ሩብ ምዕተ አመት በላይ አመታት፣ የአሸዋው ሽያጭ የልማት ማህበሩ ገቢ የጀርባ አጥንት ሆኖ ሲያገለግል ኖሯል። ልማት ማህበሩ ከአካባቢውና ከአባላቱ ከሚያገኛቸው ገቢዎች በተጨማሪ በየዘመናቱ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ለጋሾች ጋር ትሥሥት በመፍጠርና ተጨማሪ ጥሪቶችን በማግኘት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ኖሯል። ከለጋሶች የሚገኘው የገቢ መጠን በየዘመናቱ ማህበሩን ባስተዳደሩ የዳይሬክተሮች ቦርድና ሥራ አስኪያጆች ታታሪነት፣ እንዲሁም አካባቢው ላይ ሥራ በሚሠሩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ብዛትና አቅም ይወሰን ነበር።
3) ልማት ማህበሩ ምን ምን ሥራዎችን ይሠራል?
ልማት ማህበሩ እስከ አሁን የሠራቸውና አሁንም በመሥራት ላይ የሚገኛቸው ፕሮጅክቶቹ የሚከተሉትን ዘርፎች የሚነኩ ናቸው፡- ትምህርት፣ ጤና፣ የምግብ ዋስትናና መጠለያ፣ አካባቢን መልሶ ማልማትና መጠበቅ፣ ውሃ፣ የአከባቢና የግል ንጽና፣ የቱሪዝም ልማት … ወዘተ።
በአሁኑ ጊዜ ልማት ማህበሩ በመላው ኮንሶ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ሁሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል አሁን በዚህ ጊዜ በመሥራት ላይ ያሉትን፣ የካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ማዕከልና የፋሻ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ቤተ መጻሕፍት ግንባታን ጨምሮ፣ የተለያዩ የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፊያ ፕሮክቶች፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀቶች፣ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ፕሮጀክቶች፣ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎች ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ እና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች በማከናወን ላይ ይገኛል። ማህበሩ ከኮንሶ ዞንም አልፎ፣ እንደ አማሮ ልዩ ወረዳና ደቡብ ኦሞ ዞን ባሉ አጎራባች አካባቢዎችም ፕሮጀክቶችን ሠርቷል ወይም እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ከዚህ የመኸር አመት በፊት በነበሩት 4 አመታት በኮንሶ ዞንና አካባቢው ላይ የተከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮችን ተከትሎ ህዝባችን ላይ የመጣውን የረሃብ አደጋ በመቀልበስ ረገድ፣ ፊት አውራሪ በመሆንና የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራዎችን በቀዳሚነት በመሥራት እውነተኛ በኮንሶ ልጆች ለኮንሶ ህዝብ የተቋቋመ ማህበር መሆኑን አስመስክሯል።
4) ማህበሩን የሚያስተዳድረው ማን ነው?
ስለማህበሩ የአስተዳደር አካላት ከመነጋገራችን በፊት፣ ማህበሩ የመንግሥት ተቋም ያልሆነ፣ ከፖለቲካና ከኃይማኖት ተጽዕኖ ነጻና በአባላቱ የሚተዳደር ድርጅት መሆኑን መግለጽ ያስፈልጋል። ይሁንና ግን መሠረታዊ ተግባሩ ህዝብንና መንግሥትን ማገዝ እንደመሆኑ መጠን፣ ከመንግሥትና ከመንግሥት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በትብብር የሚሠራ ተቋም ነው።
እንደማንኛውም የሲቭክ (በዜጎች የተቋቋመ) ማህበር፣ በፌዴራል ደረጃ ማህበራቱን በሚገዛው አዋጅና ህግጋት ይተዳደራል። ኮንሶ ልማት ማህበር አካባቢ በቀል የልማት ማህበር ሆኖ በፌዴራል ደራጃ በሚመለከተው ባለሥልጣን በመዝገብ ቁጥር 1338 ተመዝግቧል።
ልማት ማህበሩ በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚተዳደር ሲሆን፣ በየበጀት አመቱ መጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ሥራዎቹን ይገመግማል። የዳይሬክተሮች ቦርድ በጠቅላላ ጉባኤው የሚመረጥ ሲሆን፣ ቦርዱ ደግሞ የማህበሩን ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳደራል፣ ይቆጣጠራል። ጠቅላላ ጉባኤው የማህበሩ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ሲሆን፣ የማህበሩን አጠቃላይ አባላት የሚወክል አካል ነው። የቦርድ አባላትን የመሾምና የመሻር ስልጣን አለው።
5) የማህበሩ መጪ ጊዜ ብሩህ ነውን?
ምንም እንኳን ማህበሩ ከምንጊዜውም ይልቅ፣ በተነቃቃ መንፈስ ለኮንሶ ህዝብ በተጨባጭ ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ ያለ ቢሆንም፣ “መጪው ጊዜው ብሩህ ነው!” ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር የማያስደፍሩ ተግዳሮቶች ማህበሩን እየገጠሙ ይገኛሉ።
ከላይ የተዘረዘሩ መረጃዎች ሁሉ ስለማህበሩ ለአንባቢ ግንዛቤ ለመስጠት ያህል ቀረቡ እንጂ፣ የጽሑፉ ዋና ዓላማ ማህበሩ ላይ የተደቀኑ ተግዳሮችን ለአባላቱና ለአንባቢያን ይፋ ማድረግ ነው።
5 . 1 የወቅቱ የዞን መንግሥት ለማህበሩ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል?
ማህበሩ ላይ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ ያለው ማህበሩን መቆጣጠር የሚፈገው የኮንሶ ዞን አስተዳደር ወይም አንዳንድ የአስተዳደሩ አካላት ስለመሆናቸው ብዙ ማሳያዎችን መዘርዝር ይቻላል። በተጨማሪም ከህወሃት መራሽ ኢህአዲግ ዘመን በውርስ ወደ ብልጽግና ዘመን የተሻገሩ በአስተዳዳሪው የመንግሥት አካል ባለማወቅም ሆነ በማንአለብኝነት የሚደረጉ የህግ ጥሰቶች ናቸው። ከሚስተዋሉ የዞን መንግሥት አካሄዶች፣ በተለይ አንዳንድ የዞን አመራር አካላት ልማት ማህበሩ ለማህበረሰባችን በሚያደርጋቸው በጎ ተግባራት የህዝቡን ትኩረት ሲያገኝ፣ በእነሱ ዘንድ የሚወደድ አይመስልም። ይህንንም በሚከተሉት ነጥቦች ለማሳየት እንሞክራለን።
5.2 የዞን መንግሥት አንዳንድ አመራሮች ለልማት ማህበሩ ሥራዎች አዎንታዊ ዕይታ ያላቸው አይመስሉም!
የኮንሶ ህዝብ ባሳለፋቸው ተደጋጋሚ የድርቅና የግጭት አመታት፣ ረሃብ ሲከሰት በመጀመሪያ የዞን መንግሥት ጉዳዩን በይፋ እንዳይታወቅ ለመደበቅ ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁንና የልማት ማህበሩ ኃላፊነት ወስዶ ዕርዳታ ወደ ማሰባሰብ ሲገባ፣ ሁሉም የኮንሶ ምሁራንና የኮንሶ ወዳጆች ለልማት ማህበሩ ቀኝ እጃቸውን በመስጠት ለህዝባቸው የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ አለኝታነታቸውንና አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
በዚያን ጊዜ የልማት ማህበሩ የህይወት አድን ሥራ በህዝቡ ዘንድ ትኩረት ማግኘቱን የተመለከቱ አንዳንድ የዞን አመራር አካላት፣ የዕርዳታውን ማሰባሰብ ሥራ ለመጥለፍና የህዝቡን ትኩረት ከልማት ማህበሩ ሥራ ለማንሳት በዞን መንግሥት በኩል ይፋዊ መግለጫዎችን ጨምሮ፣ በተለያዩ መንገዶች ልማት ማህበሩ ላይ ተደጋጋሚ ጫና ለማሳደር መሞከራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው። በወቅቱም ኮንሶ ዜና ሚዲያ በተደጋጋሚ ሲዘግበው ነበር።
እሱም ብቻም ሳይሆን፣ የኮንሶ ዞን መንግሥት የኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ከዞን አስተዳደር ማስጠንቀቂያ የተሰጠው በሚመስል ሁኔታ፣ አንዳችንም በልማት ማህበሩ የተደረገን የዕርዳታ ማሰባሰባና ሥርጭት ሥራን አልዘገቡም፣ ትኩረትም አልሰጡም። የፖለቲካ አመራሩ በየሥፍራው የሚያደጋቸውን ንግግሮች ከማስተጋባት ውጭ፣ የልማት ማህበርን ሥራዎች ቀርቶ በመንግሥት ስለሚሠሩ ሥራዎችም በአግባቡ መረጃን ለህዝቡ አያደርሱም። ልማት ማህበሩ ስለሚሠራው ሥራ፣ “ምንም ዘገባ እንዳትሠሩ!” ተብሎ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ይመስል፣ ልማት ማህበሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንኳን ሲያስጀምር ሲዘግቡ አይተን አናውቅም።
5.3 የኮንሶ ዞን መንግሥት የልማት ማህበሩን የገቢ አቅም በመምታት ማህበሩን ለማዳከም እየሠራ ነውን?
አሁን አሁን ደግሞ የዞን መንግሥት አስተዳደር፣ ልማት ማህበሩን ለመጉዳት ታሪካዊ ውሳኔዎችን ጭምር በመቀልበስ ታሪካዊ ስህተት እስከ መሥራት የጨከነ ይመስላል።በዚህ ጊዜ ማህበሩ የበለጠ ገቢ እንዲያገኝ በመርዳት፣ ተጨማሪ ትልልቅ ሥራዎችን በሞራል እንዲሠራ ማድረግ ሲገባ፣ በቀደም አባቶች የተወሰኑ ማህበሩን የመደገፍ ሥራዎችን ጭምር ለመቀልበስ፣ የዞን አመራሩ ውሳኔዎች እያስተላለፈ ይገኛል።
ከላይ ስለማህበሩ የገቢ ምንጮች ባነሳንበት ክፍል ሥር እንደገለጽነው፣ ከጅምሩ የማህበሩን ገቢ ለመደገፍ ተብሎ ማህበሩ እንዲያስተዳድረው የተሰጠው የአሸዋ ሽያጭ፣ ሰሞኑን በዞን አስተዳደር ውሳኔ ተቀልብሶ ከልማት ማህበሩ እንዲነጠቅ የተወሰነበት ደብዳቤ ተመልክተናል። የዞን አስተዳደር ምክር ቤቱ ውሳኔ እንደሚያሳየው ላለፉት 30 አመታት የኮንሶ ልማት ማህበር የገቢ ምንጭ የጀርባ አጥንት የነበረው የኻይሌ ወንዝ አሸዋ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ የሚተዳደር ሆኖ ከሽያጩ ለልማት ማህበሩ 30% ብቻ ይሰጠዋል።
ደብዳቤው፣ የአሸዋ ሽያጩን አስተዳደሩ ለምን ከልማት ማህበሩ መንጠቅ እንዳስፈለገው በግልጽ አይናገርም። ይህ ታሪካዊ ስህተት ነውና የዞን መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት ቶሎ እርማት እንዲያደርግ ግፊት ማድረግ የሁሉም የማህበሩ አባላት ድርሻ ሊሆን ይገባል።
የዞን አስተዳደር ምክር ቤቱ ውሳኔ፣ የልማት ማህበሩን ሥራ ከአሁኑ ሽባ እያደረገው ይገኛል። ልማት ማህበሩ በእጁ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ለካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እያሠራ የሚገኘው የድንገተኛ ህክምና ማዕከል በአባላት መዋጮ ብቻ ሲሆን፣ ለፋሻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሠራ የሚገኘው ቤተ መጻሕፍት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከአሸዋ በሚገኝ ገቢ ነበር። የዞን አስተዳደር ምክር ቤቱ ልማት ማህበሩን ለማዳከም አሸዋውን የመንጠቅ ውሳኔ ከወሰነበት ከባለፈው ሳምንት ወዲህ፣ ልማት ማህበሩ የቤተ መጻሕፍቱን ግንባታ ሥራ ለማቋረጥ ተገዷል።
በነገራችን ላይ የልማት ማህበሩ የገቢ ምንጭ የጀርባ አጥንት የሆነውን የአሸዋ ገቢ የመንጠቅ ተግባር፣ በልማት ማህበሩ ታሪክ በተደጋጋሚ የተከሰተ ነው። አንድ አጋጣሚ ብቻ ለማስታወስ ያህል፣ የኮንሶ ህዝብ የዞን ጥያቄ ባነሳበት ወቅት ምሁራን ሙሉ በሙሉ ከህዝቡ ጎን መቆማቸውን ተከትሎ በጊዜው የነበረውን የመንግሥት መዋቅር ሲያስተዳድሩ የነበሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሸዋ ሽያጩን ከልማት ማህበሩ በመንጠቃቸው ምክንያት፣ ከታህሣሥ ወር 2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ በነበረው ጊዜ ብቻ 6 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ብር ገደማ ከአሸዋ ሽያጭ የተሰበሰበ ገንዘብ መድረሻው በትክክል አለመታወቁን ኮንሶ ዜና ሚድያ የተመለከታቸው የኦዲት መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁንም የአሸዋው ሽያጭ ገቢ ግልጽ የሆነ አሠራር ባለው የኮንሶ ልማት ማህበር መተዳደሩ ቀርቶ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቁጥጥር ሥር መዋሉ፣ የልማት ሥራዎችን ከማደናቀፍ ባለፈ፣ ለሙስናና ብልሹ አሠራሮች በር የሚከፍት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
5. 4 የዞን መንግሥት ከህግ አግባብ ውጪ ለልማት ማህበሩ የአስተዳደር አካላትን እየሾመ ነውን?
በኢትዮጵያ ማንኛውም በህግ የተመዘገበ ማህበር፣ በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በሚሰየሙ የቦርድ አባላት እንደሚተዳደር በህግ የተደነገገ ነው። ይሁንና የቀድሞ የህወሃት መራሽ ኢህአዲግ ለብልጽግና ፓርቲ ካወረሳቸው የህገወጥነት ትሩፋቶች አንዱ የሆነው ነጻ ማህበራትን በፖለቲካ ሰዎች የመጠርነፍ አባዜ ዘንድሮም በኮንሶ ዞን እየተስተዋለ ይገኛል። የኮንሶ ዞን አስተዳደር ራሱ ብቻ በሚያውቀው አሠራር የዞኑ የመንግሥት ተጠሪ (ለዚያውም የፖለቲካ ድርጅት ኃላፊ) የሆነን ሰው የልማት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቤ አድርጎ፣ ልማት ማህበሩ እንዲያውቀው ያደረገበትንም ደብዳቤ ተመልክተናል።
ይህ አሠራር ኢህአዲግ ምርጫ 97ን በኢትዮጵያ ከተሞች ከተሸነፈ በኋላ ሁሉንም የህዝብ መዋቅሮችን ለመቆጣጠር ከዘረጋቸው ህገ ወጥ ሥርዓቶች አንዱ እንደሆነ የሚጠረጠረው ነጻ የሆኑ የሲቭክ ማህበራት እንዳይኖሩ የፖለቲካ አመራሩን በማስረግ መቆጣጠር ነበር። ይህም የ5 ለ1 ጥርነፋ አካሄዱ ሌላኛው ግልባጭ የሚመስል አካሄድ ነበር። በኮንሶ ዞንም ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አካሄድ በብልጽግና ዘመንም ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል ማለት ነው።
የዞን መንግሥት አስተዳደር ከቀድሞ ሥርዓት የወረሳቸውን ጤናማ ያልሆኑ አካሄዶችና ህገ-ወጥ ተግባራትን ለይቶ ማቆም መቻል አለበት። የኮንሶ ልማት ማህበር የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። በፖለቲከኞች ሊተዳደርም አይገባም። ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ አዋጁና ህጉ በሚያዘው መሠረት፣ ፖለቲከኞች ከማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ። ይህ አካሄድ፣ “ከዚህ በፊት የነበረን አሠራር ነው!” ሊሉን ብችሉም፣ መስተካከል ያለበት ህገ-ወጥነት ነውና ሁላችንም የማህበሩ አባላት የሆንንና ይህንን ጽሑፍ የምናነብ ልናወግዘው ይገባል። ልማት ማህበራችን የሚተዳደረው፣ ጠቅላላ ጉባኤያችን በሚሰይማቸው የቦርድ አባላት እንጂ፣ የዞን መንግሥት አስተዳደር ወይም ብልጽግና ፓርቲ በሚሾምልን የቦርድ አባላት አይደለም። ይህንን የዞን አስተዳደሩን ውሳኔ አጥብቀን እንቃወማለን። የዞን አመራሮቻችንም ታሪክን የሚያርሙና የራሳቸው አዲስ ታሪክ የሚጽፉ እንጂ፣ የቀደሙትን ሥርዓቶች ህገ ወጥ ታሪክ በደመ ነፍስ የሚያስቀጥሉ እንዳይሆኑ ልናበረታታቸው እንወዳለን።
6) ታዲያ የልማት ማህበሩን መጪ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ምን ማድረግ ይቻላል?
የልማት ማህበራችንን መጪ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን፣ ብሩህ እንዲሆን ከፈለግን፣ የማህበሩ አባላት የሆንን ሁላችን ለማህበራችን እንደራሴዎች መሆን ይኖርብናል። የማህበራችንን አሠራር፣ ሥራዎችና የሚደረጉበትን ጫናዎች መከታተልና ጫናዎችንም የማክሸፍ የጋራ ሥራ መሥራት ይኖርብናል።
የዞን አመራሮችም የእኛው ወንድሞች እህቶችና ለህዝባችን የሚሠሩ እንደመሆናቸው፣ በልማትና ማህበሩና በፖለቲካ አመራሩና መካከል ያለው ድንበር መጠ’በቁ ያለውን ፋይዳ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊናስረዳቸው ይገባል። በተጨማሪም ልማት ማህበሩ የህዝብ ትኩረት በሚያገኝበት ጊዜ፣ የአመራሩን ተግባር ከማሳነስ ጋር ምንም ግንኙት እንደሌለው ይልቁንም ማህበሩ በግልሰብ ደረጃ የአመራሩም ማህበር እንደመሆኑ መጠን ልቀኑበትና አቅሙን ለማዳከም ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ የበለጠ አቅሙን ለመገንባት እንዲሠሩና እንዲኮሩበት አመራሩን ማበረታታት እንወዳለን።
በቅርቡ በኮንሶ ምሁራን የተቋቋመው የምሁራን ማህበርም፣ የኮንሶ ልማት ማህበር አጋርና የኮንሶን ማህበረሰብ ኑሮና ህይወት ለማሻሻል የተቋቋም እንደመሆኑ መጠን፣ በዞን መንግሥት አስተዳደርና በልማት ማህበሩ መካከል ድልድይ በመሆን፣ አስተዳደሩ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ልማት ማህበሩን ከመደገፍ ይልቅ ማህበሩን የሚጎዳ ሊሆን እንደማይገባ፣ በምሁራዊ ትንታኔ ማሳየትና ሁለቱንም ወገኖች የመርዳት ሚናን መጫወት ይችላል ብለን እናምናለን። በቅርቡ ከነሐሴ 26-28 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የምሁራን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የዞን መንግሥት አስተዳደር አመራርም ስለሚገኙ፣ ጉዳዩ በግልጽነት መወያየትና ታሪካዊ ስህተቶችንና ታሪካዊ ስህተት ሊሆኑ የሚችሉ ውሳኔዎችን መቀልበስ ያስፈልጋል።
በተለይ በዞን መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ያሉና ልማት ማህበሩን እንደተቀናቃኝ የሚመለከቱ አንዳንድ አመራሮች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለልማት ማህበሩ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ አጋር የምሁራን ማህበር፣ የልማት ማህበሩ አባላትና የልማት ማህበሩ አመራሮችና ሠራተኞች ከዞን መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር የትሥሥርና የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን አቅደው ቢሠሩ፣ በተባበረ ክንድና አንድነት ለማህበረሰባችን በየፊናችንን በጎ አስተዋጽዖ እናደርጋለን ብለን እናምናለን።
ጽሑፍን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ካነበቡ፣ ስለኮንሶ ልማት ማህበር የገዶታልና፣ የእርስዎንም አስተያየት እንስማ። እርሶስ ምን ይላሉ? የልማት ማህበራችንን መጪ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ፣ ከልማት ማህበሩ አባላት፣ ከልማት ማህበሩ አመራር፣ ከዞን መንግስት አስተዳደርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ከአጋር የምሁራን ማህበር ምን ይጠበቃል ይላሉ? አስተያየቶን ያጋሩን።
“ሚዛናዊ መረጃ ለማህበረሰብ ለውጥ!” – ኮንሶ ዜና ሚድያ